You are here: HomeArtPoetryለምን ተጠራሁ?

ለምን ተጠራሁ?

Written by  Wednesday, 07 May 2014 00:00

“ተጠራሽ” አሉኝ! እንደ ተጠራሁ ሰማሁ፡፡ መልዕክተኛ ደግሞ ሰልሶ ተላከብኝ፡፡ ቀድሞውኑ እኔስ መጠራቴ መች ጠፍቶኝ መፈለጌንስ መቼ አጥቼው! እንዴት ልድረስ? እንዴት ልታይ? እንዴት ቀርቤ ልገኝ? የኑሮ መዘውር ሲያባትለኝ፣ ይህን ስጨብጥ - ያኛው እንደ ጎደለ ሲሰማኝ፣ ያኛውን ስይዝ - ሌላ ያላየሁት ሲመጣ . . . አንዱ ቀዳዳ ሲደፈን፣ እልፍ ቀዳዳ ሲከፈት . . . ራስን ማሸነፍ፣ ራስን መቻል፣ መደላደል፣ ሥር መስደድ . . . ሲባል መንገድ ሲቀየስ - መንገድ ሲነደል - ትልም ሲፈርስ - ትልም ሲታደስ፣ የጎበጠው ሲቃና -የተቃናው ሲጎብጥ፣ ሀዘን ላንዱ ዓይን እንባ - ደስታ ላንዱ ዓይን ብርሀን ሲያቀርብ . . . የዘመን ሩጫ የቱጋ የእፎይታ ትንፋሽ አድሎኝ ልቅረብ? እንዴት አድረጌ ልድረስ? እንጂማ መፈለጌ መቼ ጠፍቶኝ! መጠራቴስ መች ተሰውሮኝ . . . መንገዴ ላይ የህይወት ሰልፈኛ ተሰድሮ እርሱን ቦታ ቦታ አስይዞ መጨረስ ዳገት ሆኖብኝ ማለፊያ አጣሁ እንጂ ከአባት እልፍኝ መቅረብ ሳልፈልግ ቀርቼ ነው?

 

ግን . . . ለምን ተፈለግሁ? ለምን ተጠራሁ? ምን ጥፋት አጥፍቼ ይሆን? እርግጥ ነው ስህተት ከእጄ ጠፍቶ አያውቅም! ቢሆንም ምን አጥፍቼ ነው? አባት የሚያስቆጣ፣ ነይ ትፈለጊያለሽ የሚያሰኝ፣ ከራሴ አልፎ መልዕክተኛ የሚያስልክ ምን ሠርቼ ይሆን? የሚያስቀጣኝ ይሆን? ወይስ አንዳች የህይወት አሳዛኝ ድግስ በላዬ ሊከነበል ይሆን? የሚያስነክስ - ልብ የሚሰቅዝ ያልታሰበ ነገር ወደ ህይወት ጎዳናዬ ሊመጣ ስለ ሆነ እንድጠነቀቅ ሊመክረኝ እና ሊያጽናናኝ ይሆን? እንዲህ ያለው ችግር የሚደርሰው በጤናዬ ላይ ነው ወይስ በእጄ ባለ ነገር ላይ? ወይስ በቤተሰቤ ላይ ይሆን? እም . . . አልያም ደግሞ ያ አይደክመው ባላጋራዬ ምን ሊያደርግ አስቦ ይሆን? አንዳች የባላጋራ እጅ ያለበት ሴራ ሲጎነጎን ታይቶት ይሆን ያስጠራኝ አባቴ? ይሆን? ይሆን? ይሆን?

 

ምክንያት ፍለጋ በምናቤ መሬት ሰማዩን ሳስስ፣ የቆጥ የባጡን ሳሰላ፣ መውጣት መግባቴን ስፈትሽ ተጠራሽ መባሌ ትካዜን ጨመረብኝ፡፡ የንስሐ ዝርዝሬን ሳገላብጥ - ሊያስቀጣኝ የሚችል ስፈለግ፣ ለአደጋ ቅሩብ የሆኑ ስስ ብልቶቼን ስዳብስ፣ የባላንጣዬ እግር ማስገቢያ ይሆን ያልሁትን ቀዳዳ ስፈልግ ነፍሴን ፍርሀት ገባት፣ ጭንቅ ሸተተኝ፡፡ ታዲያ ለምን ተጠራሁ? እስቲ ለምን ተፈለግሁ?

 

በለዘብታ የልቤ በር ተንኳኩቶ በለሆሳስ “የልብሽ እና የልቤ ርቀቱ” የሚል ድምጽ ብሰማ ጊዜ ሀሳቤ ፍሰቱን ለወጠ፡፡ አዎን ርቀቱ! አቤት ርቀቱ!!! ርቀት በልቤ የተቀረጸውን ምስል አደብዝዞት . . . የማይያዘውን ሳሳድድ፣ ለቅርብ - ለአሁኑ ስለፋ፣ በማያጠግብ እንጀራ - በማያረካ ወተት ስደለል፤ አሁን ዘላለሜን ተክታ የሩቁን ብትጋርድብኝ የጠሪዬን ማንነት፣ የፈላጊዬን አባትነት ባልረሳውም ረሳሁት፣ ሳልረሳው ረሳሁት፡፡ በዛሬ ውጣ ውረድ መሸሸግ ባህሪይ ማንነቱን ቢያደበዝዝብኝ፣ ደጁን ሳልጠና ቃሉን ሳልሰማ በእኔነት ጫካ መሸፈት በአሁን ስንክሳር ማሳበብ ተለመደኝ፡፡ ርቀት የጠሪዬን ጠረን ቢያጠፋብኝ ተጠራሽ ስባል “እኮ ለምን? በምን?” ሆነ ጥያቄዬ . . . “ምን ሊመጣብኝ ይሆን?” ሆነ ሰቀቀኔ፡፡ የፍቅር፣ የምህረት የርህራሄ፣ የጸጋ፣ አምላክነቱ፣ አባትነቱ፣ ልጅነቴ ተዘንግቶኝ አቤት፣ እሺ ማለት ጠፍቶኝ፣ ከፍቅር ማዕድ በየዕለቱ መጋበዙ ሩቅ ሆኖብኝ ተጠራሽ ስባል እንደ ዳኛ፣ ተጠራሽ ስባል እንደ ከአደጋ ጠባቂ አስቀድሜ አስቤው ተሸበርሁ፡፡ 

 

አሄሄ . . . ልይዘው ያልሁት አሁን፣ ልካንበት ያሰኘኝ ዛሬ እንዳልተገላበጠ ቂጣ እያደበነ እኔኑ ይሸራርፈኝ ጀምሮ ልሆናት ላልሁት ለእኔ ከጥቅም ጉዳቷ መዘነ፡፡ ማለዳ የቀኔን ጅማሬ፣ በቀኑ እኩሌታ፣ ምሽት የቀኑን መቋጫ  ከሠሪው የምሪት የምክር ድምጽ ርቄ የነፍሴ የደስታ ወዝ፣ እርካታዋ ተገፈፈ፡፡ እናም አስቀድሜ ማለት የነበረብኝን በለሆሳስ ድምጹ ሲያነቃኝ አልሁት “እሺ! እገኝልህ ዘንድ እርዳኝ፡፡ ልቤም አስቀድሞ ያንተው ነውና ኑርበት . . . በሰዓት ሁሉ አግኘኝ፣ በመንገዴ ሁሉ አግኘኝ፣ ውሎዬን ሁሉ አብረን እንዋል፡፡” አሁን በእኔነት የሸሸግሁት መልስ ተገልጧል . . . ለፍቅር ተፈልጌያለሁ፣ ለምህረት ተፈልጌያለሁ፣ ለምክር ተፈልጌያለሁ፣ እንድጠቅም በጸሎት መሰዋያዬ ከምደርሰው ከአባቴ እልፍኝ ተጠርቻለሁ!!!

Seen 6644 times Last modified on Wednesday, 07 May 2014 06:57
Hermela Solomon

Hermela Solomon is passionate about God and the Arts. She has written  continuous articles on Addis Admas, worked at Whiz Kids Workshop (tsehay memar twedalech) and contributed 3 books as part of the package to encourage Early Graders reading.

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

.

Right Now

We have 139 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.