You are here: HomeNews/Eventsበተመረጡ መስፈርቶች ልህቀት ላሳዩ መዘምራን ዕውቅና እና ማበረታቻ ሊሰጥ ነው!

በተመረጡ መስፈርቶች ልህቀት ላሳዩ መዘምራን ዕውቅና እና ማበረታቻ ሊሰጥ ነው!

Published in News and Events Wednesday, 24 June 2015 00:00

በ2006/2014 ዓ.ም. በተመረጡ መስፈርቶች ልህቀት ላሳዩ መዘምራን ዕውቅና እና ማበረታቻ ሊሰጥ ነው። ማበረታቻዎቹ ሚሰጡት ለተመረጡ ሶስት ዘማሪያን ሲሆን ፥ ሰጪውም አካል ማህሌት የመዝሙርና የሙዚቃ ፎረም አገልግሎት ይባላል። ስለፕሮግራሙ አላማና ስለ እውቅና ሰጪው አካል ለማወቅ ፥ የህብረቱን አስተባባሪዎች ፕሮፌሰር ጥላሁን አደራ ፥ ፓ/ር መላኩ ይገዙን እና ዘማሪ አዲሱ ወርቁን ዛሬ አንጋግረን ነበር።

 

ፕሮፌሰር ጥላሁን ሲጀምሩ ፥ መዝሙር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ትልቅ ሥፍራ ጠቅሰው፥ በኢትዮጲያ ብቻ ሳይሆን በአለም ዙሪያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ለመዝሙርና ለአምልኮ የሚሠጡት ጊዜ ሲተመን ከ1/3ኛው እስከ ግማሽ እንደሚደርስና ይህም ቤተክርስቲያን ለመዝሙር የሰጠቸውን ስፍራ እንደሚያመላክት ያሳያል ብለዋል፡፡ ታዲያ ይህ ትልቅ አገልግሎት እገዛ የሚያስፈልገውና አንዳንድ ቦታ ላይ ድክመቶች የሚታዩበት እንደመሆኑ መጠን የበለጠ ጠቃሚ እንዲሆን  በማሰብ ማህሌት የመዝሙርና የሙዚቃ ፎረም አገልግሎት እንደተመሰረተ  ገልጸውልናል።

 

ስለአገልግሎቱም ዓላማ ሲነግሩን፥ መዝሙር የማስተማር፣ ክርስቲያኖችን የማበረታታት፣ ለማያምኑ በጣፋጭ ዜማ ወንጌልን እንዲሰሙ የመሳቢያ መንገድ እንደመሆኑ ፤ መዝሙሮች  ሲደረሱና ሲቀናጁ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረቱ፣ ጥሩ ጣዕመ ዜማ ያላቸው፣ የግጥም አጻጻፍ ይዘትን የተከተሉ፣ የሙዚቃ ቅንብሩንም ጨምሮ ብቃት ባለው ሁኔታ በስርአት የተዘጋጁ እንዲሆኑ ማበረታታት መሆኑን ፓ/ር መላኩ አክለው ገልጸውልናል።

 

በአሁኑ ጊዜ መልካምና እጅግ የሚወደዱ መዝሙሮች እየተደረሱ ቢሆንም ፥ በዚያው መጠን ደግሞ አንዳንድ እርዳታና ሲያልፍም መበረታታት የሚያስፈልጋቸው እንዳሉ ግልጽ በመሆኑ፥ ስለዚህም ከስነ ፅሁፍ፣ ከስነ መለኮት፣ ከግጥም አጻጻፍ አንጻር ሥልጠና በመስጠትና ሴሚናር በማዘጋጀት መዝሙር ጥራት ባለው መልክ እንዲቀርብ የሚያግዝ ድጋፍ ማህሌት የመዝሙርና የሙዚቃ ፎረም አገልግሎት እንደሚሰጥም ለመንገዘብ ችለናል።

 

በየአመቱ ለሚካሄደው ዘማሪዎችን የማበረታታትና እውቅና የመስጠት አገልግሎቱ በቦርዱ የተቀመጡ መስፈርቶች ያሉ ሲሆን ፥ ከእነርሱም መሃል

  • መዝሙሩ ዓላማው ምን ላይ ያተኮረ ነው?
  • በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተና አግባብነት ያለው የስነ መለኮት መሰረት አለው ወይ?
  • ጣዕመ ዜማው እንዴት ነው?
  • ዜማውና ግጥሙስ የሚገናኝ ነው ወይ?
  • ዘማሪው በህይወቱ ክርስትናውን ይኖረዋል ወይ?
  • መዝሙሩ ኦርጅናል /ከሌላ ያልተቀዳ/ ነው ወይ? የሚሉት ውስኖቹ ናቸው።

 

ከላይ በተጠቀሱት መስፈርቶች መሠረት ከፍተኛውን ውጤት ላስመዘገቡ ሶስት ዘማሪያን ሽልማት እንደሚሰጥና አገልግሎቱም ከጀመረ አራት አመታት እንደተቆጠሩ ዘማሪ አዲሱ ወርቁ በማከል ፥በነዚህም መስፈርት መሠረት የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓመት በሎስ አንጀለስ ሦስተኛውን በዋሽንግተን ዲሲ ያካሄደ ሲሆን አራተኛውን በኢትዮጲያ ውስጥ በመዲናችን አዲስ አበባ ሰኔ 20, 2007 ዓ.ም. በምስራቅ መሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸውልናል፡፡

 

ስላለፉት ማበረታቻዎችህ ሲገልጹም፥ በመጀመሪያው አመት ዘማሪ ዳዊት ጌታቸው፣ ዘማሪት ቤተልሔም ተዘራ፣ ዘማሪ ዳግማዊ ጥላሁን፤ በሁለተኛው አመት ዘማሪት አዜብ ኃይሉ፣  ዘማሪ ሚልኪያስ አዱኛ፣ ዘማሪ አብነት ግርማ፤ በሦስተኛው ዓመት ዘማሪ መጋቢ ታምራት ኃይሌ፣ ዘማሪት ኢየሩሳሌም ነጊያ፣ ዘማሪ አገኘሁ ይደግ እንደተሸለሙ ገልጸውልናል።

 

በመጨረሻም የዚህን አመት ዝግጅት ካለፉት ለየት የሚያደርገው ከአመቱ ተሸላሚዎች በተጨማሪ ከአንጋፋ ዘማሪዎች ውስጥ ለተመረጡ እውቅናና የህይወት ዘመን ስኬት አዋርድ የሚሰጥበት እንደሆነ ፕሮፌሰር ጥላሁን ነግረውናል፡፡

Seen 4732 times Last modified on Wednesday, 24 June 2015 16:21

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 68 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.