You are here: HomeOpinionsየዝማሬና እና የዘማሪ ልኩ

የዝማሬና እና የዘማሪ ልኩ

Written by  Friday, 11 July 2014 00:00

ድሮ ድሮ ትንሽ ጊዜው ቆየት ብሏል ወረቀቶቼን ሳገላብጥ አንድ የፃፍኩትን ግጥም አገኘሁና ዛሬ ልፅፍ ለተሰናዳሁበት ሃሳብ መንደርደሪያ ስለሆነልኝ እንዲህ አሰፈርኩት፤ 

መለኪያ የጨበጠ ግን ልኩን ያጣ ሰው 

እየተለካለት ጠጥቶ ጨረሰው 

እንደወጣ ሳያውቅ መቼ ወዳናቱ 

ተለክቶ የጠጣው አደረገው ከንቱ። 

ይላል ግጥሙ። ግጥሙን የፃፍኩት ዜማ አውጥቼ ልቀኝበት ሳይሆን ምክንያቴን መጨረሻ ላይ እገልፀዋለሁ። ይህን ስል ጓጉታችሁ የመጨረሻውን ክፍል አሁኑኑ እንዳታነቡት አደራ። የመሐሉ አንቀጾች ካልተነበቡ የገደል ጉዞ ይሆንባችኋልና፣ በትዕግስት ንባባችሁን ቀጥሉ። 

 

ለመሆኑ ዝማሬ እና ዘማሪ ልክ አላቸው ወይ? በሚል ሃሳብ ዙሪያ የሁላችን መሠረት ከሆነው ከእግዚአብሔር ቃል እና በግል ሕይወቴ እንዲሁም በሌሎች ወገኖቼም የሕይወት ተሞክሮ እና ልምድ ከተገነዘብኩት የልኬቱን ቁም ነገር ዋና አትኩረቴ በማድረግ ልቀጥል። 

 

የዝማሬ እና የዘማሪ ልኩን በአራት ዋና ዋና መመዘኛዎች ቃኝቼዋለሁ፤ 

  • ከማንነትና ከሕይወት ምስክርነት፣ 
  • ከድምፅ ችሎታ፣ 
  • ከሙዚቃ ጥበብ እንዲሁም 
  • ከሥነ ጽሁፍ ብስለት እና የመልዕክት ጥንካሬ አንፃር ሲሆን ይህንንም እንደሚከተለው ለመዳሰስ እወዳለሁ።

 

መለኪያ (Standard) ሳይኖረን ስለ “ልክ’’ ለማውራት አዳጋች ይሆናል። ስለየትኛውም ጉዳይ ልኩን በተመለከተ ለመነጋገር አስቀድሞ የሚለካውን እና ልኬት ሰጪውን የሚያስማማልን መለኪያ ሊኖር ይገባል። ታዲያ የዝማሬ እና የዘማሪ ልኩ ብለን ብንጠይቅ ቃሉ መለኪያችን እንደሆነ እንረዳለን። ይህንን መነሻ ሃሳብ ይዘን ከብሉይ ኪዳን የንጉሥ ዳዊትን የዝማሬ ዘመን ጥናት ብናደርግ ዛሬ በዚህ ዘመን የተለመደው ሰውኛና ከቃሉ ያፈነገጠ መለኪያ እና መስፈርት ከንቱ መሆኑን እንረዳለን።

 

የዳዊትን የዝማሬ ዘመንና የመዘምራኑን አደረጃጀት፣ በዘመኑ የተገለጠውን ጥበብ ቃሉ ላይ አንብበነው ዝም ብለን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። በሦስቱ መሪዎች በነብዩ ናታን(1ኛ ዜና 29፤29) በዋናው መሪ እና አለቃ በራሱ በንጉሥ ዳዊት እንዲሁም በነዚህ በሁለቱ ሰዎች ሥር በዜማ ሁሉ ላይ በተሾመው ክናንያ (1ኛ ዜና 15፤22) ሃላፊነት የሚመራ የዝማሬ እና የመዘምራን ቡድን የቱን ያህል ግዙፍ እንደሆነ እስቲ አስቡት። በዜማው ሁሉ ላይ በክናንያ ሥር ደግሞ አሳፍ (2ኛ ዜና 29፤30)፤ኤማን (1ኛ ዜና 6፤33) እና ኤዶታም (1ኛ ዜና16፤41- 42) ሃላፊነቱን ይዘው በሥራቸው በሚያገለግሉት በአስራ ሦስት የሙዚቃ ተጫዋቾች እና በነዚሁ መሪዎች ሥር 24 ልጆች(1ኛ ዜና 25፤1) በድምፃቸው ቀዳሚነት የሚመራ መዘምራን ተደራጅቷል። ይህ ብቻ አይደለም እነዚህን 24 ዘማሪያንን የሚያጅቡ ሌሎች 288 የዜማ ብልሐተኞች (1ኛ ዜና 25፤2) ብሎ ቃሉ ያስቀመጣቸው ሲኖሩ እነዚህም በሥራቸው የሚሰለጥኑ ሌሎች 3456 መዘምራን እንደየችሎታቸው በተመደቡበት ቀንና ጊዜ በበላይ በሚመሯቸው 14 በሚደርሱ የዜማ ብልሃተኞች እየተለማመዱ ጠቅላላ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሆነውን የእስራኤል ሕዝብ እንደአንድ ሰው አድርገው ያዘምሩት ነበር። ወደ ሙዚቃው ክፍል ስንሄድ ደግሞ በአስራ ሦስቱ የሙዚቃ ተጫዋቾች ሥር የሚሰለጥኑ 4000 የሚያህሉ ሙዚቀኞች (1ኛ.ዜና 23፤5) የእስራኤልን ሕዝብ ሙዚቃ በማጀብ ያገለግሉ ነበር። 

 

በ1ኛ ዜና 15 እና 16 እንዲሁም በ2ኛ ዜና 29 እንዲሁም እነዚህን መሰል ታሪኮች በተመዘገቡባቸው በሌሎቹም የመጽሐፍ ቅዱሳችን ክፍሎች እያንዳንዱን የመረጃ ቁጥሮች ምንም ሳንጨምር እና ሳናጎድል አጠቃላይ ድምሩን ለማወቅ የጣርን እንደሆነ በእሥራኤል መንግሥት በንጉሱ ዳዊት ዘመን ከነበሩት ከአጠቃላይ 38000 ሌዋውያን ውስጥ 7786 ያህሉ ለዝማሬና ለአምልኮ እንዲሁም ለሙዚቃ ተጫዋችነት አገልግሎት ብቻ የተለዩ እና የተመረጡ መሆናቸውን እናረጋግጣለን። ይህ የሚሳየን ዳዊት ለዚህ አገልግሎትምን ያህል ሥፍራ እንደሰጠው ነው። ምናልባት በትንቢተ አሞጽ 9፤11 እና በሐዋሪያት ሥራ 15፤16-17 ’’የዳዊትን ድንኳን አነሳለሁ’’ የዳዊትን ድንኳን እንደገና እሰራታለሁ’’ የተባለለት የአምልኮ እና የዝማሬ ድንኳን ስለነበር እና ለ24 ሰዓት ሰባቱንም ቀን በመገናኛው ድንኳን እና በቤተመንግሥቱ የአምላኩን ሥም በዜማ ስለሚያወድሰው ይሆንን?ዛሬስ የእኛ ቤት ድንኳን ምን ሞልቶት ይሆን? 

 

በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሉ አገልግሎቶች በሙሉ የከበሩ እና ያለጥሪ እና ያለ ዓላማ የማይገባባቸው እንደሆኑ ብናውቅም ይህንን የዳዊትን ዘመን የዝማሬ አገልግሎት መስፈርት እና ልክ ስናስተውል ግን የዝማሬው አገልግሎት እንደልብ ወይም በዘፈቀደ ከማይገባባቸው አገልግሎቶች አንዱ እንደሆነም እናስተውላለን። 

 

ብዙ ሰዎች ወደ መዝሙር አገልግሎት መግባት ሲያስቡ የሚወዷትና በቃላቸው ሚያውቋት እንዲሁም የሚጠቅሷት አንዲት ጥቅስ አለቻቸው። ’’ደስ ያለው ይዘምር’’ ይህ ጥቅስ የተፃፈበትን ሥፍራ በየትኛውም ትርጓሜ ብታነቡት ቃሉም ሆነ አውዱ እንደሱ አይልም። ያዕቆብ 5፤13 ’’ከናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይፀልይ፤ደስ የሚለውም ማንም ቢኖርእርሱ ይዘምር’’ ይላል። ይህ ቃል በፍፁም ሁሉም ዘማሪ እንዲሆን ወይም ማንም መዘመር ይችላል የሚል ፈቃድን የሚሰጥ ሳይሆን እንደውም ለመዘመር የሚጠየቀውን መስፈርት ወይም ልክ ያስቀምጣል ያም ’’ደሰታ’’ ነው። ምናልባት አዲሱ መደበኛ ትርጉም በተሻለ ሁኔታ አብራርቶልናል ምክንያቱም የሚዘመረው የመዝሙሩ ሃሳብ ’’የምስጋና መዝሙር’’ መሆኑን በግልጽ አስቀምጦልናል። 

 

መዝሙር ማለት ምን ማለት ነው? 

ይህ ትርጓሜ በልባቸው ደስታ ተሞልተው የምሥጋናን መዝሙር በግላቸው ወይም ለሌሎች ለሚዘምሩ ሳይሆን የአምላኬን መንግሥት በዝማሬ አገልግሎት አስፋፋለሁ ይህ የእኔ ጥሪዬ ነው ለዚህም ደግሞ ስጦታውን ሰጥቶኛል ብለው በሰዎች ፊት ቆመው ዝማሬ ለሚያቀርቡ የተሰጠ ትርጓሜ ነው። 

መዝሙር ማለት:- 

መልዕክት ያለው 

በሥነ ግጥም ወይም የየትኛውንም የሥነ ፅሁፍ ሕግን በጠበቀ ዘዴ የሚቀርብ 

ነፍስን በሚሰረስር እና በሚያረሰርስ ዜማ የተሰራ 

ዕውቀቱ ባለው የሙዚቃ ባለሙያ የታጀበ (በሙዚቃም ላይታጀብ ይችላል) 

በየትኛውም የድምፅ ክልል(vocal range) ውስጥ ባለ ሰው የሚቀርብ ሆኖ ነገር ግን ለሚያዳምጠው ሰው ጆሮ ጣዕም ባለው ጉሮሮ እና አንደበት የሚቀርብ ማህሌት ነው። 

 

በመስበክ ወይም በማሰተማር የሚያገለግል ሰው በሚገባ ማወቅና መረዳት ካለበት ከእግዚአብሔር ቃል እውቀቱ ሌላ የማስረዳትና የመናገር ችሎታው እና ስጦታው ያለው ሰው ሊሆን ይገባል እንጂ ድምጹ ምንም አይነት ይሁን በአገልግሎቱና በሰሚዎቹ ላይ የሚያመጣበት ችግር የለም። ዘማሪ ግን በግሩም ሁኔታ ከቃሉ የቀረበ መልዕክት ቢኖረው፣ ሥነ ጽሁፋዊ ህጉን የጠበቀ እና በጥሩ የሙዚቃ ባለሙያ የታጀበ እንዲሁም ነፍስን የሚያረሰርስ ዜማም ቢወጣለት ነገር ግን የዘማሪው ድምጽ የሚዘምርበትን የዜማውን ሕግ ያልጠበቀና በተለምዶ ያልተቃኘ ድምፅን ይዞ ከቀረበ ዝማሬውን ቢያቀርብ ማንም ሊያዳምጠው አይችልም። ከዚህ የተነሳ በዝማሬ አገልግሎት ለአምላኩ መንግሥት ሰዎችን ከመማረክ ይልቅ እንዲርቁ ሊያደርጋቸው የሚያስችል አገልግሎት ውስጥ ሊከተው ይችላል። ሰሚዎቹ ጆሮአቸውን እንዳይሰጡት ያደረገው እንግዲህ መልዕክቱ ሳይሆን ዘማሪው ነው። 

 

አንድ ሰው ለሚወዳት ፍቅረኛው ዋጋው ውድ የሆነ የዳይመንድ ፈርጥ ያለበት ቀለበት በስጦታ ቢሰጣት ያንን የሰጣትን ሰጦታ መልሳ ለፍቅረኛዋ እያሳየች የዳይመንዱን ቀለበት እንዲያደንቅላትና እንዲደነቅበት ማድረግ ሞኝነት እንደሚሆንባት ሁሉ፤እግዚአብሔር የሰጠንን ያማረ ድምፅ ፤የሙዚቃ ችሎታ ወይም ከመዝሙር ጋር የተያያዙ ሥጦታዎቻችንን መልሰን አምላካችንን ልናስገርምበት ወይም (impress) ልናደርገው አንችልም። ሥጦታው የተሰጣት ሴት የአልማዙን ውድ ቀለበት አድርጋውና በወዳጆቿ በሚያውቋትና በማያውቋት ሁሉ ፊት አጊጣበት ስትታይ ቀለበቱን ያዩ ሁሉ ዳይመንዱን የሰጣት ሰው ለእርሷ ያለው ፍቅር የቱን ያህል ትልቅ እንዲያውቁ ወይም ምን ያህል ባለጠጋ መሆኑን እንዲረዱ እንደምታደርግና በዚያ ሥጦታ ምክንያት የማያውቁት ሰውየውን እንደሚወዳጁ የሚያውቁት ዳግም በደንብ በቅርበት እንዲጠጉት እንደምታደርግ ሁሉ ዛሬም ገታ የሰጠንን ሥጦታ እኛው እንድንደምቅበት ሳይሆን ወደ ሥጦታው ባለቤት ሌሎችን ሰዎች የምንስብበት መገልገያችን ሊሆን ይገባል። 

 

የዝማሬ እና የዘማሪ መለኪያዎች 

• አንደኛው የዝማሬን አገልግሎት በግላቸው በጓዳ የሚያገለግሉበት ሳይሆን በአደባባይ ቆመው ሰዎችን ወደ ጌታ ለማምጣት ሊጠቀሙበት የሚገባ መሆኑን ሊያውቁ ይገባል። ከዚህ የተነሳ ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት ለዝማሬው አገልግሎታቸው የተሟላ ማንነት ይዘው መቅረብ ግዴታቸው ነው። ብዙዎች “እኔ ለጌታ ክብር ነው የምዘምረው ሰው ወደደው አልወደደው፤ ገባው አልገባው የራሱ ጉዳይ” ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። ጌታ ኢየሱስ እንደተናገረው (ማቴ 4፤19) ’’በኋላዬ ኑ እና ሰዎችን አጥማጅ አደርጋችኋለሁ’’ እንዳለው ሥጦታዎቻችን የሰዎችን ጆሮ አልፎም ልብ ማጥመጃዎቻችን ናቸው እንጂ የግል መታወቂያዎቻችን አይደሉም።

 

• ሁለተኛው፡- ቀደም ብዬ የንጉሥ ዳዊት የዝማሬ አገልግሎት ምሳሌነት በጠቀስኩት መሠረት መዝሙርና ዝማሬ ልኩ ጥራት እነደሆነም ልንገነዘብ ይገባናል። በዳዊት ዘመን አሁን እኛ ያገኘናቸውን እና ወደፊት የምናገኛቸውን ቴክኖሎጂዎችን ሳያገኙ ምን ያህል ለዚህ አገልግሎት እንደጣሩ ማሰቡ ብቻ ጥራት የተባለውን መለኪያ እንድንጠቀምበት ይረዳናል። እንኳን 4000 ሙዚቀኞች ይቅርና ዛሬ ባለንበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁለት ኪይቦርድ ተጫዋቾችን አስማምተን እንዲጫወቱ ማድረግ ከብዶናል። 

 

በመዝሙር አማካኝነት ሰው ስለ አምላኩ ይዘምራል። በመዝሙር አማካኝነት ሰው በአምላኩ ቃል ይመክራል። በመዝሙር ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይመሰገንበትም። በመዝሙር የሰው ማንነት እና ጀብደኝነት አይታወጅበትም። መዝሙር የአምላክን ፍቅር መግለጫ፤መዝሙር የአምላክን ምህረት ማወጃ፤መዝሙር ያዘኑ ሰዎችን እንደቃሉ በሆነ ቃላት ማጽናኛ ፤መዝሙር ተሰፋ የቆረጡ ሰዎችን በቃሉ ማበረታቻ፤መዝሙር የውስት መንፈስን በቃሉ እምነት ማነቃቂያ ፤መዝሙር ለነፍስ ጉልበት ማቀበያ፤ መዝሙር ሰዎችን ከተሳሳተ መንገዳቸው ውስጥ ዘልቆ በሚገባ ዜማ ኮርኩሮ እና አባብሎ ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ መሣሪያ ነው። አረ ስለ መዝሙር ስንቱን መባል ይቻላል? ብዙዎች በመዝሙር ልባቸው ተነክቶ ወደ ጌታ መጥተዋል፤ ብዙዎች አዝነውና ተክዘው ዝማሬን ሲሰሙ ተጽናንተው አልበረቱምን? ማነው ውስጡ የታፈነውን ደስታ በመዝሙር በጥቂቱም ቢሆን መተንፈስ ያልቻለ?እረ ማነው?መልሱ ማንም ነው። 

 

በተለያዩ ሚዲያዎችና መድረኮቻችን ላይ ስለ ዘፈንና መዝሙር ልዩነት ውይይት ሲደረግ አድምጫለሁ። በዚህች ዓለም ላይ ብዙ ነገሮች ወይ የዛኛው ወይ የዚህኛው ናቸው ተብለው ይመደባሉ። ለምሳሌ ያገባች ሴት የባሏ ናት ወይም አንድ መኪና የእንትና መኪና ነው፣ እንደሚባለው አይነት ማለቴ ነው። ዜማ እና ሙዚቃ ግን መንፈሳዊም ዓለማዊም አይደሉም። መንፈሳዊና ዓለማዊ የሚሆኑት ተጠቃሚው ወይንም በሚሰራባቸው እጅ ውስጥ ሲገቡ ብቻ ነው። ለምሳሌ (ትንቢተ ዳንኤል 3) ንጉሥ ናቡከደነፆር ላዘጋጀው ምስል እንዲሰግድለት የተጠቀመው የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እና የሰዎችን ድምፅ ነበር። ይህ ዛሬም ዓለም ልጆቿን ለማሰገድ የምትጠቀምበት ዘዴዋ እንደሆነ ማየት አያዳግትም። (ዘኁ 10፡6፤እያሱ 6፤13 ራዕይ 8፤6) እግዚአብሔርም የኢያሪኮን ግንብ ለማፍረስ፤ የእስራኤል ሕዝብ ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ ለማንቀሳቀስ የሚያሰማው ድምፅ ሙዚቃ ነው። በራዕይ መጽሐፍ እግዚአብሔር ክፉ ነገሮችን በመጨረሻው ዘመን ለማጥፋት ሆነ የዓለም ፍፃሜ ሂደቶችን ሲያደርግ የሚጠቀመው የሙዚቃ መሣሪያዎችን ነው። መለከቶችና ሌሎችንም የሙዚቃ መሣሪያዎች ለእግዚአብሔር ክብር ውለዋል። ሙዚቃም ሆነ ዜማ መንፈሳዊም ዓለማዊም ሊሆኑ የሚችሉት በተጠቃሚው እጅ ሲገቡ ነው ብለን እንድንናገር የሚያደርገን ይህ ነው። ዛሬ ትውልዱ በዝማሬና በዘፈን ላይ ልኩን ማስመር አቅቶታል። ሌላ ምሳሌ ልስጥ ፤ድሮ ድሮ ረጋ ያሉ ሙዚቃዎች መንፈሳዊ ይመስሉን ነበር። ዛሬ ዛሬ ደግሞ አለማውያን ሲረጋጉ መንፈሳዊያኑ የሙዚቃቸው ምት ተጣደፈ። እንደውም ነፍስ የሚሰረስሩ ዜማዎች እና ሙዚቃዎች በዓለማውያኑ ሙዚቃዎች ላይ በጉልህ መታየት ጀምሯል። ስለዚህ ሙዚቃና ዜማ መንፈሳዊም ዓለማዊም የሚሆኑት በተገልጋዮቻቸው አጅ ውስጥ ሲገቡ ነው። እስቲ ደግሞ በራሴ ልመስል። እኔነቴን እንዲሁም ሕይወቴን በገዛ ፈቃዴ ለእግዚአብሔር መንፈስ በመስጠቴ ምክንያት የዜማንና የሙዚቃ ሥጦታዎቼን በገዛ ፈቃዴ ለእርሱ መንግስት ብቻ አገልግሎት እንዲውሉ መፍቀዴ እስከዛሬ ከውስጤ የፈለቁት የሙዚቃ ሥራዎቼ ለአምላኬ ክብር ብቻ እንዲውሉ ማድረጌ ደግሞ ሌሎች የሚያደምጡኝ ሰዎች ወደ እኔ ሳይሆን ስጦታውን ወደ ሰጠኝ አምላክ እንዲመጡ መንገድን፤አቅጣጫን በማሳየት በዚህ ባሳለፍኳት ዕድሜዬ ጥቂትም ይሁን ብዙ፣ ሰዎችን ወደ እርሱ መንግስት ለማምጣት እየጣርኩ እንደሆነ አስባለሁ። ይህ በእኔ ሕይወት ላይ ብቻ የሆነ ሳይሆን የሙዚቃ፤ የድምፅ የድርሰትና የመሳሰሉትን ሥጦታዎቻቸውን ለአምላካቸው ክብር ብቻ ያዋሉ ሰዎችንም ይጨምራል። ዛሬ ሁላችንም በዚህ ልክ ልንሄድይገባል እላለሁ።ይህንን የዝማሬ አገልግሎት እንደ ናቡከደነፆር ትውልድን ላሰራነው ሐውልት የምናሰግድበት ሳይሆን የኢያሪኮን ግንብ የምናፈርስበት ሕዝቡን እንደ እስራኤል ሕዝብ ካለበት ቦታ ወደ ሌላ ከፍታ የምናሻግርበት እንዲሁም መጪውን ጌታ ዋናውን ንጉስ የምናመልክበት መለከታችን ሊሆን ይገባል። ይህ ነው ልኬቱ። እጃችን ላይ ያለው አገልግሎት እያዘፈንበት ነው ወይስ ታላቁን ጌታ እያመለክንበት? 

 

ለዚህ ፅሁፍ የመጨረሻ ያደረኩት ልኬት ይህንን የመዝሙር አገልግሎት አቅራቢ ስለሆነው “የዘማሪው’’ ማንነት እና ሕይወት ነው። አንድ ወዳጄ ይህንን ጉዳይ ያብራራበት ምሳሌ ልጠቀም። ውሃ ስለጠማን ከሱቅ ሄደን በላሰቲክ የታሸገ ወሃ እንገዛለን። ታዲያ ለባለሱቁ ገንዘብ የከፈልነው ውሃውን ለያዘልን ለላስቲኩ እና ውሃው እንዳይፈስ ለታሸገበት ክዳን ነው? ወይስ ውኃው የት ሃገርና በምን ነጥረ ነገሮች እንደተሰራ ለተፃፈበት እላዩ ላይ ለተለጠፈበት ማስታወቂያ ነው? ወይስ ብዙዎቻችን ውስጡ ላለው ለውሃው ብቻ ነው የከፈልኩት ብለን እናስባለን? እንደ እውነቱ ከሆነ ውኃው የት አገር እና በማን ፋብሪካ እንደተመረተ ፕላስቲኩ ላይ ካልተጻፈ ያንን ውሃ ገዝተን አንጠቀምም። እንደውም ብዙዎቻችን ውሃውን የያዘልን ላስቲክ እንኳን መቆሸሽ ቀርቶ ከዳኑ ትንሽ ላላ ካለ እና የተከፈተ ከመሰለን በፍፁም አንገዛውም። የቱንም ያህል ውኃ ቢጠማን በአቀራረቡ ካልተደሰትን አንጠጣውም። ገንዘባችንን ያወጣነው ለላስቲኩ፤ በላዩ ላይ ለተለጠፈውም ማስታወቂያ፤ ለክዳኑም በዋናነትም ለውሃውም ጭምር ነው። ይህ ምሳሌ በቀጥታ ከዘማሪ ማንነት፤ ባህሪ እንዲሁም ህይወት ጋር ይገናኛል። የፈለገ ድምፁ (ድምጿ) የሚያምርለት ቢሆንም ዘማሪ ዝማሬውን የሚያመጣበት መንፈሱ ካጠራጠረና ነቀፌታ ካለበት የተበላሸ ይሆንበታል። በደንብ ካልተከደነና ክፍት የሆነ ውሃ ምን ተከቶበት እንደሆነ እንደማይታወቅ ይሆናል። ዘማሪም ለዚህች ዓለም ነገር ማንነቱ ክፍት ከሆነ፣ ዓለማዊነት ወይም ሥጋዊ ካደላበት፣ ከዓለም ያልተለየ ባህሪ ካለው፣ የሚወጣውም ዝማሬ እንደዛው ነው። ስለዚህ መለኪያው የዘማሪው ድምፅ ሳይሆን የዘማሪው ሕይወት ነው። ጊዜው ቆየት ብሏል እንጂ ወደ መገናኛ አካባቢ የነበረ አንድ ሕብረት ውስጥ ያሉ ወገኖች የዘማሪ አውታሩን አንድ መዝሙር ግጥሙን ለውጠው እንዲህ ብለው ዘመሩልኝ፤ 

 

“ማንም ዘማሪ የለም በዚህ ምድር ላይ፤ 

ሲዲውን አልገዛም ሕይወቱን ሳላይ’’ 

 

የትኛውን የአውታሩን መዝሙር እንደቀየሩት ሳታውቁት አትቀሩም ብዬ እገምታለሁ። ነገሩ በጊዜው ቢያስቀኝም ግን ታላቅ እውነታ አለበት። ማናችንም በጥሩ ባለሙያ ሴት የተሰራ ዶሮ ወጥ በዛገ ሳህን ቢቀርብልን አንበላም። ስለዚህ የዘማሪ ልኩ ሕይወቱ ነው ብለን ብንደመድመውስ። ግን የህይወት ልኬት ሲባል ምንን ያካትታል? በግል ሕይወቱ ከጌታው ጋር ያለው ታማኝነት፤ ባለትዳር ከሆነ በትዳሩ ደምቆ የሚታየው የጌታ ውበት ገንዘብ፣ ክብርና ዝናው ላይ ያለው አመለካከትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የሚታይበት ውበት፣ ሕይወቱ ከድምፁ፤ ሕይወቱ ከዜማው፤ ሕይወቱ ከግጥሙ ይልቅ ጮሆ የሚሰማለት ዘማሪ ማለታችን ነው። በዚጽሑፍ ጅማሬ ያስነበብኳችሁን ግጥምን አስታወሳችኋት? የሕይወት ልኩና በውስጡ የተቀመጠው የዝማሬ ፀጋው ላልተመጣጠነ ሰው የተገጠመች ናት። ስለዚህ መግጠም ስለቻለ የሚገጥም ዘማሪ ሳይሆን በሕይወቱ የገጠመውን የአምላኩን ተዓምራት ገጣሚ፤ድምፁ ከሙዚቃው ጋር ሕይወቱ ከጌታው ጋር የተቃኘ ዘማሪ፣ የሰሞንኛ ዘማሪ ሳይሆን ትውልድ ተሻጋሪ ዘማሪ ልንሆን ይገባናል። 

 

ይሄ ነው የዘማሪ እና የዝማሬ ልኩ።እኔን ጨምሮ ይህን ካነበባችሁ ጋር ጌታ በደንብ አበጅቶ ልክ ባስገባን? አሜን ልክ ያስገባን። 

Seen 10116 times Last modified on Saturday, 12 July 2014 10:18
Getayawkal Girmay

Website: gandbministry.org Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 94929 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.