You are here: HomeOpinionsዝማሬና ዘፈን . . . ምንና ምን?

ዝማሬና ዘፈን . . . ምንና ምን?

Written by  Tuesday, 26 August 2014 00:00

ዘፈንና ዘፋኝነትን ጤናማ ድርጊት አድርገው ሊወስዷቸው የሚፈልጉ ክርስቲያኖች አንዳንድ ማመቻመቺያ ሃሳቦችን ሊመዝዙ ይዳዳቸዋል። አንዳንዶች “ዳዊትም እኮ ዘፍኗል።” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “እግዚአብሔርን በዘፈን አመስግኑት ተብሎ ተጽፏል” ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ “መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን በሙሉ ስለወንድና ሴት ፍቅር ነው የሚያወራው እኛስ ተቃራኒ ጾታን እያደነቅን ብናንጎራጉር ምን ይለናል - ፍቅርንስ የፈጠረው እሱ አምላክ አይደል” ብለው ዘፋኝነትነትን ላለመልቀቅ ምክንያታዊ ጥያቄ ያቀርባሉ። 

 

በዘፈንና በዝማሬ መካከል ብዙም ልዩነት እንደሌለ አድርጎ መረዳት ወይንም አንዱን ለሌላው አቀያይሮ መሰየም ከሦስት መረታዊ ምክንያቶች የሚመነጭ መንፈሳዊ መደናበር ነው። የመጀመሪያው ‘ዘፈን’ ወይም ‘ዘፋኝነት’ የሚለው ቃል በአሻሚ ትርጉም ጥቅም ላይ መዋሉ ነው። በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ ምዕራፍ ስድስት ላይ ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ሙሉ ማንነቱን ሰጥቶ ሲያመሰግን ያሳየው ትዕይንት ‘ዘፈን’ ተብሏል። በተመሳሳይ መልኩ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አስራ አራት በገሊላ ላይ ገዢ ተደርጎ የተሾመውና የመጥምቁ ዮሐንስ ገዳይ የሔሮድስ አንቲጳ ልጅ ለአባቷ አቅርባ የደስታው ምክንያት የሆነለት ትዕይንትም ‘ዘፈን’ ተብሏል። በመሆኑም ‘ዘፈን’ ‘ዘፋኝነት’ ተብለው በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመለከቱትን ተግባራት ምንነት ለማወቅ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችንና ማጥኛ ጽሑፎችን መመልከት ግድ ይላል። 

 

“የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”  ገላ 5፡19-21

 

“በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን” ሮሜ 13፡13

 

“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” 1ጴጥ 4፡3

 

ከላይ በተጠቀሱት ሦስት የተለያዩ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ላይ የተገለጹት ዘፈንና ዘፋኝነት ‘Revellings’, ‘Riot’ የተሰኙትን የእንግሊዝኛ ቃላትን ይተካሉ። በዚህ አግባብ ዘፈን ማለት ከድምጽ ጋር በሙሉ መፍቀድና መሰጠት ራስን ለማዝናናትና ለማስደሰት መታደም ሲሆን ለመዝናናትና ለደስታ የሚዘጋጁ የሙዚቃ ዝግጅቶች ተሳትፎዎችና ተያያዥ ተግባራት በሙሉ ዘፋኝነት ውስጥ ይጠቃለላሉ። የምሽት ጭፈራዎችና ዳንስ ቤቶች፤ ‘የሙዚቃ ድግስ’፤ ‘ኮንሰርት’፤ . . . እየተባሉ የሚተዋወቁት ዝግጅቶች በሙሉ በዚህ ጎራ ውስጥ ይፈረጃሉ። እነኚህና መሰል ሥራዎች ለክርስቲያኖች እንዳይሆኑ በእግዚአብሔር ቃል ላይ አጥብቀው ተከልክለዋል። እነዚህ ጥቅሶች ገና ያልዘፈንን ወደ ፊት የመዝፈንና የማዘፈን ሃሳብ እንዳይኖረን፤ ስንዘፍን የከረምን ካለን ዘፈንንና ዘፋኝነትን አቁመን ወደ እግዚአብሔር መንገድ እንድንመለስ፤ በእግዚአብሔር መስመር ላይ የምንመላለስ ደግሞ እዛው ባለንበት የተከበረና የተወደደ ስፍራ ጸንተን እንድንቆም - ዘፋኝነትን ከቶውኑ እንዳናስበው የሚያስጠነቅቁ ክፍሎች ናቸው። እነዚህ መጽሐፍት ዘፋኝነት የእግዚአብሔርን መንግስት የማያስወርስ የሙያ መስክ መሆኑ በማያሻመ መልኩ የተቀመጠባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው። መዝፈናችንን ካላቆምን የእግዚአብሔርን መንግስት ልንወርስ እንደማንችል የሚያስረግጡልን የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ናቸው። 

 

“ስሙን በዘፈን ያመስግኑ፥ በከበሮና በመሰንቆም ይዘምሩለት። በከበሮና በዘፈን አመስግኑት በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት።” መዝ 149፡3፤ 150፡4  

 

“የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፥ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች በልብዋም ናቀችው። . . . ዳዊትም ሜልኮልን፦ በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ።” 2ሳሙ 6፡20፣22

 

በእነኚህ ክፍሎች ‘ዘፈን’ ተብለው የተጠቀሱት ተግባራት ከቀድሞዎቹ የቅርጽ ተመሳሳይነት ሊኖራቸው ይችላል። ይሁንና እንዲህ አይነቶቹ ትዕይንቶች ወንጌል ጨርሶ ከሚከለክላቸው ከቀድሞዎቹ ጋር የሚለያዩባቸው ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች አሏቸው። አንደኛው በእነዚህ ተግባራት ዋናና ማዕከላዊ የክብር ስፍራ ይዞ የሚገኘው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑ ነው። በቀደሙት ‘ዘፈን’ና ‘ዘፋኝነት’ ላይ ሊመሰገን የተገባው የመልካም ነገር ምንጭና አድራጊ እግዚአብሔር ሥፍራ አይሰጠውም። ሁለተኛው የልዩነት ነጥብ የድርጊቶቹ ዓላማ ነው። የንጉስ ዳዊት አላማ እራሱን ወይንም ሌሎችን ማስደሰት አይደለም። የደስታው ሁሉ ምንጭ የሆነውን አምላኩን በሙሉ አቅሙ ማመስገን ነው። እናደርገው ዘንድ የተከለከልነው ‘ዘፈን’ና ‘ዘፋኝነት’ ዓላማው እራስን ማዝናናትና ማስደሰት ነው። ከዚህም በላይ ዳዊት እናደርገው ዘንድ ለሚመክረንና ራሱም አድርጎት ላለፈው አይነት ‘ዘፈን’ የሚለው ተግባር በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ with dance(በዳንስ፤ በመወዝወዝ፤ በማሸብሸብ) በአካል እንቅስቃሴና በመውድቅ በመነሳት የሚደረግን ድርጊት ወክሎ እናገኘዋለን። ይህን ዓይነቱን ‘ዘፈን’ አንድ የአምልኮ ዓይነት ሆኖ በዚህ በእኛም ትውልድ ለእግዚአብሔር ሲቀርብለት እንመለከታለን። ይህኛው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት አምልኮ ነው።

 

ዘፈንና ዘፋኝነትን ከዝማሬና አምልኮ ጋር አምታተን የምንረዳበት ሁለተኛው ምክንያት የመንፈሳዊ ዓይኖቻችን መጥበብ ወይንም ዓይኖቻችን የእይታ ችግር ውስጥ የገቡ እንደሆነ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የተገለጠለት ሰው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ይቀበላል - ዳግም ተወልዶ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል። ለእግዚአብሔር ልጅ የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት የድርጊቶቹ ሁሉ መነሻ ይሆናል። በቃሉ የተቀመጠውና እንታዘዘው ዘንድ የተገባ የእግዚአብሔር ድምጽ እንዲህ ይላል፦ 

 

“የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ። በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።” ቆላ 3፡16

 

“በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ። ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ።” ኤፌ 5፡20

 

መንፈሳዊ ብዥታ ከሌለብን የሚዘመርለት፤ ቅኔ የሚቀርብለት፤ ምስጋና የሚገባው እግዚአብሔር አምላክ ብቻ እንደሆነ እንመለከታለን። በዚህም ምክንያት ለሌሎች ከመቀኘት፤ ለሌሎች ከማዜምና ከመዘመር (በአንድ ቃል ከመዝፈን) እንወጣና ከማንነታችን አንድም ሳናስቀር ለእግዚአብሔር ለክብሩ እንዘምራለን። ዘፈን እግዚአብሔር ከሚከበርበት ቤተ መቅደስ የሚወጣ ድምጽ አይደለም። ከእግዚአብሔር ቃልና ከመንፈሱ ተወልዶ በእግዚአብሔር የልጅነት ስልጣን ከሚመላለስ ሰው፤ ከእግዚአብሔር ጋር የተቆራኘ ህይወት ካለው፤ በጸሎት ጠይቆ በጸሎት ከሚቀበል ሰው፤ በመንፈስ ቅዱስ ከተሞላና በመንፈስ ቅዱስ ከሚመራ ሰው፤ ቃሉን ዘወትር ከሚበላ አገልጋይ . . . ዘፈን ሊቀዳ እንደማይችል በግልጽ ሊታወቅ ይገባዋል። በወንጌል ሚዛን ሲመዘን ዘፈንና ዘፋኝነት አክሳሪ ‘ቢዝነስ’ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ የሚነግስበት ጉባኤ እንጂ የዲያቢሎስና የአቀንቃኙ ሃሳብ የሚስተናገዱበት መድረክ ዘፋኙን ብቻ ሳይሆን ዘፋኙ ዘፈኑን የሚያቀርብለትን ትውልድ ጭምር ኪሳራ ውስጥ ይጥላል። ስካርን፣ ዘማዊነትን፣ መዳራትን . . . ለማጀብ የሚመች የኪነጥበብ ሥራ በእግዚአብሔር አይደገፍም።

 

ሦስተኛው የዚህ ውዥንብር ምክንያት ዘፈንና ዝማሬ ተመሳሳይ ግብአት መጠቀማቸው፤ በሁለቱም ድርጊቶች መሃል የቅርጽ ተመሳሳይነት መኖሩና ተመሳሳይ ስሜትን መነሻ ሊያደርጉ ስለሚችሉ ነው። ሁለቱም ድርጊቶች የሙዚቃ መሳሪያዎችን፣ ግጥምንና ዜማን፣ ድምጻውያንን ባጠቃላይ ሙዚቃን እንደ ዋነኛ ግብአት ይጠቀማሉ። ልዩነቱ ሙያውን፣ መሳሪያወቹንና ባለሙያዎቹን ዋጅቶ ለጌታ ለእግዚአብሔር ክብር ማስገዛትና አለማስገዛቱ ላይ ነው። የምርጫና የፈቃድ ጉዳይ ነው። ምሽት ጭፈራ ቤት ብዙዎችን ሲያሳክርና ሲያጫፍር የሚያድረው ኦርጋን፣ በየአዝማሪ ቤቱ እሸሼ ገዳሜ የሚያስብለው መስንቆና ከበሮ፤ በየጎዳናው “ሀኪሜ ነሽ”ንና “ላፍ አርጋት”ን ጆሮ እእኪቀደድ ድረስ የሚያስደልቀው ሞንታርቦ ድምጽ ማጉያ ለእግዚአብሔር ክብር ሲዋጁት እግዚአብሔር የሚመለክበት የክብር የዜማ እቃ አልሆንም አይልም። ከሁሉ ይበልጥ ግን መዋጀት ያለበት ድምጻዊው፣ የሙዚቃ መሳሪያ አዋቂዎቹ ፤ ዲጄዎቹና በዚህ ንግድ ትርፍ የሚተዳደሩት ሰዎች ናቸው። 

 

“እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል።” 2ጢሞ 2፡21

 

ምክንያቱም ሰዎቹ በክርስቶስ ኢየሱስ ንጹህ ደም፤ በመስቀል ጣር ዋጋ የተከፈለባቸው ክቡር ዕቃዎች ለመሆን የተጠሩ በመሆናቸው ነው። ይህ ክቡር ባለሙያ ከዘፈንና ከዘፋኝነት ራሱን ነጻ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር ይቀርብ ዘንድ የነገስታት ሁሉ ንጉስ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ከልቡ ደጅ ቆሞ ያንኳኳል። 

 

ዘፈንም መንፈሳዊ ዝማሬዎችም ሁለቱም ከመድረክ ጀምሮ ዘመኑ እስካፈራቸው የድምጽና ምስል አውታሮች ድረስ በተመሳሳይ መልኩ መተላለፍ ይችላሉ። ልዩነታቸው ይዘታቸው ላይ ነው። ዘፈን ርኩሰትን የሚያቀነቅን ሲሆን ዝማሬና አምልኮ ደግሞ ቅዱሱን እግዚአብሔር ያወድሳሉ። ዘፈን የዓለምን፣ የሥጋንና የዲያቢሎስን ሥራ ሲያራግብ መንፈሳዊ መዝሙርና አምልኮ ደግሞ ወደ ዘላለም ንጉስ ወደ እግዚአብሔርና ወደ መንግስቱን ያቀርበናል። ዘፈንና ዘፋኝነት ከእግዚአብሔር መንግስት የሚያስተጓጉል፤ እራሱንም ታዳሚዎቹንም ወንዝ የማያሻግር ሙያ ሲሆን መዝሙርና አምልኮ በዚህ በምድርና በሰማያዊውም መንግስትም የማያቋርጥ የዘላለም ተግባር ነው። በእግዚአብሔር እልፍኝ ከፍ ከፍ ብሎ የሚያጥን መስዋዕት ነው።  ዘፈንና ዘፋኝነት ከመንፈሳዊ አምልኮና ዝማሬ ጋር መመሳሰሉ እንዳያታልለንና ከዘላለማዊው ትሩፋታችን እንዳያዘናጋን ልብ ልንል ይገባል - መመሳሰልና መሆን የተለያዩ ናቸውና።  

 

ዘፈንም ይሁን መዝሙር ከተደሰተ ሰው ሊመነጩ ይችላሉ። የደስታችን ምንጭ እግዚአብሔር መሆኑን ማወቅና አለማወቅ የዘፈንና የመዝሙር መለያያ ነጥብ ሊሆን ይችላል። ልዩነቱ ዝማሬ የደስታችን ምንጭ እግዚአብሔርና እሱ ያደረገልን ነገር መሆኑን ማወቅ ላይ ነው። የደስታው ምንጭ እግዚአብሔር መሆኑን ያወቀ ዘማሪ ቀድሞ የደስታው ምንጭ ለሆነው ለአምላኩ ምስጋናን ይሰዋል፤ ቅኔን ይቀኛል ያመልከዋል። የሐዘን እንጉርጉሮና የሰቆቃ ለቅሶዎች የዝማሬም የዘፈንም መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ።  ሐዘንና መከራ በደረሰብን ጊዜ ሐዘናችንና ሰቆቃችንን ይዘን  ከማንጎራጎርና ከማጉረምረም ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት በንስሀና በተሰበረ መንፈስ እንቀርባለን። የደረሰብን ችግር ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን  የደረሰው በራሳችን፣ በቤተሰባችን በአገር፤ በወገን ላይ ወይንም በሌሎች ሕዝቦች ላይ ነው ብለን ብናስብ እግዚአብሔር የመፍትሔ አምላክ ነው ብለን ፊቱን ፍለጋ በአባታችን በእግዚአብሔር እግሮች ሥር የምንወድቅ ከሆነ፤ ይህን ምልጃችንን ሌሎች ተከትለው እንዲተገብሩት ግጥም ብንቋጥር ግጥሙም ዜማ ተቀብቶ በሙዚቃ ተቀናብሮ ወደ ሌሎች ቢደርስ ይህ ከመዝሙር ዘልሎ ዘፈን የሚሆንበት አጋጣሚ እጅግ የጠበበ ነው።

 

ዘፈን በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላበት ምክንያት የሰዎችን ቀልብ ከእግዚአብሔር ይልቅ ወደሚዘፈንለት ወደ ማንኛውም ነገር ዞር የማድረግ አቅም ስላለው ነው። ከእግዚአብሔር ዞር ያሉትንም እዛው ዞር ባሉበት ተሟሙቀው እንዲቆዩ የማድረግ አማላይ ባህሪ አለው - ዘፈን። በኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ 32 ላይ እንደምናጠናው የእግዚአብሔር ሕዝብ ልቡ ከአምላኩ ሸሽቶ ከወርቅ ቀልጦ ወደ ተሰራ ጥጃ ሸፍቶ ነበር። ሕዝቡ ይህንን የጣኦት ጥገኝነት ያጅብበት የነበረበት ድመጽ ዘፈን ነበር። “ኢያሱም እልል ሲሉ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን፦ የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ አለው። እሱም ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ አለው።” ዘጸ 32፡17-18 ሌላ ጣዎት ሸሽጋ ከሚያድናት አምላኳ የራቀች ነፍስ የምታወጣው ድምፅ የዘፈን ድምጽ ነው። ለአርባ ቀን ሲያስጨንቃቸው የነበረውን ፍልስጤማዊ ጀግና በዳዊት እጅ የገደለላቸውን እግዚአብሔርን ከማምለክ የተዘናጉ የእስራኤል ሴቶች  “. . .ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር።” ይህ ዘፈን በንጉስ ሳኦል ዘንድ ክፉ ቅናትን ያጫረ ድርጊት ነበር። ጠላት በዳዊት ላይ በክፋት ይነሳበት ዘንድ ሁነኛ ምክንያትም ነበር። “ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ።. . .የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር።” ሕዝ 28፡12-13 ተብሎ የሙዚቃ አዋቂ እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተነገረለት ሉሲፈር(ዲያቢሎስ) ሰዎች እግዚአብሔርን ወደማወቅ፣ ወደ ማመስገንና ወደማምለክ እንዲሄዱ ፈቃዱ አይደለም። በዚያ ፈንታ ሰዎች በምድር ላይ ጊዚያዊ እርካታና ደስታ የሚያገኙበት የሚመስላቸውን መተኪያ ያዘጋጅላቸዋል። ከእነዚህ መተኪያዎች አንዱ ዘፈን ነው። 

 

መኃልየ መኃልየ ዘሰለሞን የጥበብና የፍቅር መጽሐፍ ነው። ጠልቀው ባነበቡት ቁጥር የፍቅርን ጥልቅ ምስጢራዊ ጓዳ ያስዳስሰናል። ከዚህ የእግዚአብሔር ቃል ክፍል የምንማረው ቁም ነገር ስተን ልንከተለው ለምንወድደው የዘፋኝነት መንገዳችን ማስተባበያ ለመስጠት ከምንጠቅሰው ጥቅስ እጅጉን ያለፈ ነው። ባለ ብዙ ሃብቱና ባለብዙ ሚስቶቹ ዝነኛው ንጉስ ሰለሞን ወደ ሰሜናዊ ግዛቱ በሄደበት ወቅት አንዲት መልከመልካም ሱናማይት ኮረዳ አይቶ በውበቷ ይማረካል። ይህቺን ሴት ወደ ቤተ መንግስቱ ያመጣታል። ይህቺ በጎች የምታግድ ሴት ከብጤዋ ጉብል በግ ጠባቂ ጋር የጠነከረ የፍቅር ቃል ኪዳን ስለነበራት ንጉስ ሰለሞን በገንዘብና በጥበቡ አባብሎ በቤተ መንግስቱ ሊያስቀራት አልተቻለውም። በመጨረሻም ይህቺ ሴት የንጉሱን የጋብቻ ግብዣ ሁሉ ሳትቀበል ወደ መንደሯ መመለስ ችላለች። 

 

በዚህ ታሪክ ውስጥ በገንዘብ ብዛትና በጊዚያዊ ጥቅም ሊደለል ስላልቻለ ሃይለኛ ፍቅር እንማራለን። ታማኝነትን፤ መልካምነትንና የዓላማ ጽናትን አጥንተን የምናደንቅበት የእግዚአብሔር ቃል ክፍል ነው። ለዝናና ለትርፍ ያላደረ እውነተኛ ፍቅር ውበትን እነደ ሸቀጥ ለገበያ ከማያቀርብ መልካም ስብእና ጋር እየተከሸነ የቀረበበት የኪነጥበብ ሥራ ነው - ከመዝሙሮች ሁሉ የበለጠው የሰለሞን መዝሙር። በእነዚህ የቃል ኪዳን እስረኞች ፍቅር መሃል የገባው የንጉስ ሰለሞን የሚያማልል ግብዣና አድናቆት በፍቅረኛሞቹ ጥምረት ላይ የተደቀነ በቀላሉ የሚታለፍ አደጋ አልነበረም። እንዲህ አይነቱን ፈተና ሊወጣው የሚቻለው ጽኑ እምነት፣ በፍቅረኛዋ ላይ ያላት ተስፋና እንደ ብረት የጠነከረው ፍቅራቸው ብቻ መሆኑን የተማርንበት ክፍል ነው። ሌሎች የወንጌል ክፍሎችም ይህንኑ ጭብጥ ያረጋግጡልናል። 

 

“እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” 1ቆሮ13፡13

 

 

ከዚህ እውነታ ውጭ በገና አንስተን የምንደረድርለት፤ ግጥምና ዜማ ሰርተን የምንዘፍንለት ትምህርት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አልተጻፈም - የጠላት ትርጉም የማዛባት ዳርዳርታ ካልሆነ በስተቀር።

 

ሰዎች ሲደሰቱ መጮኽ፣ መዝለል፣ መጨፈር፣ መዝፈን መፈለጋቸው ተፈጥሮአዊ ጥማት ነው። እስራኤላውያን በግብጽ 400 ዓመት በባርነት ከቆዩበት ምድር በወጡ ጊዜ ሙሴና የእግዚአብሔር ልጆች ከባርነት ነጻ ያወጣቸውን አምላክ በመዝሙር ያከብሩት ነበር። ሴቶች ከሙሴ እህት ከነቢይቱ ማርያም ዘንድ ለዘፈን ሲቀርቡ እሷ ቅኝታቸውን ወደ ዝማሬና አምልኮ ትመራው ነበር። “የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።” ዘፀ 15፡21  ቤተክርስቲያን፣ ክርስቲያን የሙዚቃ ባለሙያዎችና መንፈሳዊ ተቋማት ትውልዱን ከዘፋኝነት የሚመልሱ ሥራዎችን እያዘጋጁ በማቅረብ መትጋት ይገባቸዋል። 

Seen 12032 times Last modified on Tuesday, 26 August 2014 08:27
Mihret Massresha

Theatre Arts and Communication Practitioner, Gospel Art Curator and The Ethiopian Full Gospel Believers Church Public Relation Head

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 94744 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.