You are here: HomeOpinionsይኼ የኛ ስብከት፦ መታከም ይኖርበት ይኾን? Part One

ይኼ የኛ ስብከት፦ መታከም ይኖርበት ይኾን? Part One

Written by  Tuesday, 25 November 2014 00:00

የዚህ ጽሁፍ ዐላማ እርማት የሚያሻቸውን ልማዶችና ልምምዶች እንዲሁም ግድፈቶች ለመጠቈም እንጂ፣ ገደብ በሌለው ለግጥ በዘመናችን ስብከቶች ላይ ለመሣለቅ ያቄመ አለመኾኑን እገልጻለሁ። ከነጕድለቱም ቢኾን የአባቴ መንጋ ምክረ መለኮትን ለመቀበል በየሰንበቱ የሚታደምበት ማዕድ ላይ አሸዋ ለመነስነስከቶ ምን እጅ አለኝ”?! ይህ ማለት ግን፣ ቀድሞውኑ በማዕዱ ላይ አሸዋው ተሞጅሮ ከቀረበ፣ ወይም ባዶ ገበታ በራበው ሕዝብ ፊት ከተሰደረ፣ ወይም በእንጀራ ተመስሎ ሞት ያለበት የበረሓ ቅልለማኅበረ ኅሩያኑ ሲታደል ባየሁ ጊዜ፣ ልክ አይደለምብዬ መጮኽ አይገባኝም ማለት አይደለም፤ እጮኻለሁ እንጂ!

 

በርግጥ ይህችን ወረወረ ተብዬ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነውልባል እንደምችል አልጠፋኝም። ነገር ግን፣ ጸሓፊው ራሱ ባገኛቸው ዕድሎች ከአትሮንስ ጀርባ መቆምን ለዓመታት ዐልፎበታልና ሰባኪነት ከሩቁ የሚያየው ተግባር አይደለም። አመልካች ጣቱንም ሌሎች ላይ ብቻ ለመቀሰር አቈበቈበም፤ በርካታ ጕድለቶች በገዛ ስብከቱ ውስጥ የመታጐራቸውን ሐቅ ሳያመነታ ይቀበላልና። ይህን ሲጽፍ ሌሎችን ወቅሦ ራሱን ለማጽደቅ በመቋመጥ አይደለም፤ ከስሕተታችንና ከተቃወሱት ስብከቶቻችን ድካም እንድንማማርና እንድንታረም ለማሳሰብ ቢገደው ነው እንጅ።

 

ዛሬ ቃለ እግዚአብሔርን ለማድመጥ ፈልገው፣ የመለኮትን ድምፅ በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፍታቴ በኩል ሽተው ለሚታደሙቱ የእውነት ወዳጆች ስለምናቀርበው መልእክት በወጉ ማሰብ የሚኖርብን ጊዜ ላይ ያለን ይመስላል። በዘመናችን የስብከት አገልግሎት አንዳች እክል ገጥሞታል። ይህ ሞጋች ጕዳይም አስተዋይ ክርስቲያኖች በጥሞና የሚወያዩበት ርእሰ ጕዳይ ከኾነ ከራርሟል፤ ነገር ግን፣ በሚመለከታቸው ሁሉ ዘንድ ተገቢውን ትኵረት አግኝቷል ለማለት አያስደፍርም።

 

ወገኖች ሆይ፣ ስለ ጕዳዩ በየጓዳችን ማጕተምተሙ ብቻ በቂ አይደለም። ስብከትን ተንተርሰው የሚታዩት ቀውሶች በምንም ዐይነት ፍጥነትና ጥልቀት እንዳይቀጥሉ አርምሞአችን መሰበር ይኖርበታል። እኔም ለምክክር የሚፈይድ ሐሳብ ለማጫር ከአገዙ በሚል ጥቂት ነጥቦችን እጠቃቅሳለሁ። እናንተም እስቲ ተወያዩበት። ግን፣ እውነት እንነጋገር ከተባለ ስብከቶቻችን አላነከሱም ትላላችሁ?

የስብከቶቻችን እድፈት ግድፈት፦

ስብከቶቹን ምን አጠየማቸው?

ሁላችንንም ሊያስማማን የሚችለው መድረኮቻችን በስብከት ቀውስ መታመሳቸው አከራካሪ ያለመኾኑ ጕዳይ ነው፤ የኾነ ያወየባቸው ነገር አለ። ይህ ማለት ጤናማ መልእክቶችና መልእክተኞች የሉንም ማለት አይደለም፤ ሞልተዋል። ግን እነዚህ ጤነኞችከአጠቃላዩ ክሥተትና ኹኔታ ጋር ሲነጻጸሩ ኢምንት ናቸው። የኾነ ኾኖ፣ ፀሓይ በሞቀው ገመናችን ላይ ዐይናችንን የምንጨፍንበት ጕልበት ካላገኘን በቀር ስብከቶቻችን ጽኑ ተግዳሮት እንደ ገጠማቸው ማስተዋል ከባድ አይደለም።

 

ሰባኪነት ይሉት ሞያ እንደ በወዝህ እንጀራህን ትበላለህዐይነት የሰብኮ-ዐደርነት መገለጫ በኾነበት ድባብ መልእክቱ የቱን ያህል ሊቀጥን እንደሚችል ዐስቡት። ስብከት ለገበያ እስከ ወጣ ድረስ ዕጣ ፈንታው ምን ሊኾን ጠብቀሃል?” ያሉኝ ሰዎች አሉ፤ በጣም ከባድ ነው። ርግጥ የዚህ ማስረጃ በየጸሎት ቤቱ መድረክ ላይ ሞልቷል። በእኔና በእናንተ ዘመን ከቃሉ ሥልጣን ያፈነገጡ፣ በትምህርተ መለኮት ይዘታቸው የተዳከሙ፣ ከቅዱሱ መጽሐፍ የነጠረ ሐሳብ ጋር የሚጣረሱ፣ በአዕማድ የክርስትና አስተምህሮ ላይ ያመፁና በቋንቋና ተግባቦታዊ ጠገጋቸው የጨረቱ መዓት (መኣት) “ስብከት ነገሮችአየሩን መሙላታቸውን ማን ይጠራጠራል!

 

እገሌ የተባለው አቀንቃኝ ያዜመውን ዘፈን ወደ መዝሙርነት ለውጨዋለሁና ቆመን እናምልክየሚል ዘማሪየምታዩበት መድረክ ቀውስ አልነካውምን? ከአንድ ሰዓት በላይ ሰባኪው ራሱን ሲያሞካሽ የዋለበት ዐውደ ምሕረት ላይ ጌታው፤ እባክህን፣ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን (ዮሐ. 1221 አመት) የሚል ማሳሰቢያ በትልቁ ጽፈን መለጠፍስ አይገባንም? “አሁን ቃሉን የምንሰብክበት ዘመን አይደለም፤ እስከ ዛሬ ተሰብከናል፤ አሁን የድርጊት ጊዜ ነው፤ ዛሬ ዝለሉ ካልኳችሁ ትዘላላችሁ፤ መጮኽ ካስፈለገንም በታላቅ ድምፅ ትጮኻላችሁየሚል ጨካኝ በእግዚአብሔር ቃልና ሕዝብ ላይ ያለ ርኅራኄ ሲቀልድ እያየንና እየሰማን እንዴት ችላ ማለት ይቻለናል?

 

የመስቀሉ ማእከልነት ተዘንግቶ፣ የሰውን ቋጠሮ ሊፈታ ይችላል የተሰኘ ማንኛውም ዐይነት የደፋሮች እንቶ ፈንቶ ሲንበለበል ስንሰማ ልብሳችንን ብንቀድይበዛብን ይኾን (1ቆሮ. 45፤ ሐዋ. 1414)? የማኅበረ ምእመናኑ አባት ነኝበማለት የሚያምን ሐዋርያሰውዬ፣ ራሱ ዘምሮ፣ እሱው መባ ሰብስቦና ራሱ ለሁለት ሰዓት ያህል ስለራሱ ሰብኮ ሕዝብ ሲያሰናብት ዝም ማለት ይቻላል? ሌላውም እንዲሁ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ በአምልኮ መካከል በእግሩ እንዲቆምበማሳሰብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር እንዲዘመር ካዘዘ ይህ መድረክ የማን ነውብላችሁ አትጮኹም? ስብከቶቻችን ራሳቸው ጸድተው ሊያፈኩን ካልቻሉ፣ ጠይመው ሊያጨልሙብን ይችላሉ። የሕይወታችንን እንከን በማየት የኑሮ አረማችንን ከየሕይወታችን ማሳ ውስጥ የምንነቅለው አስቀድሞ የስብከቶቻችን መልእክት ከአስተምህሮ አራሙቻ ሲጸዳ አይደለምን? ከደፈረሰ ወንዝ ውስጥ ንጹሕ ውሃ መጠጣት አይታሰብም! በርግጥ እድፈትና ግድፈት ያልራቃቸው የዘመናችን ስብከቶች ችግር መንሥኢዎች በርካታ ናቸው፤ በዚች ዐጭር ጽሑፍ ተዘርዝረው ያልቁም አይመስለኝም። ቢኾንም ግን ስብከቶቻችንን ቀትረ ቀላልያደረጉትን መንሥኢዎች ከብዙ በጥቂቱ ማጤን ከቻልን መፍትሔውን ለመፈለግ ግማሹን መንገድ እንደ ሄድን ይቈጠራል። ስለዚህ ጥቂቱን ብቻ መጠቃቀስ ሳይኖርብን አይቀርምና እንመልከታቸው።

ቀዳማይ ነገር፦

መልእክት

ዋነኛው የስብከቶቻችን ችግር ምንጭ የትኵረት መዛነፍ ይመስለኛል፤ የይዘት ጕዳይ ለማለት ነው። እዚህም፣ እዚያም ታዳሚዎችን ለማስደሰት ዐልመው የተነሡ ሰው ተኰር መልእክቶች የመለኮትን ማእከልነት ማግለላቸውን ቀጥለዋል። በቀላሉ ቤተ እግዚአብሔር ከትወና ቤትነት በመጠኑ ብቻ ለየት ይል ዘንድ የተገደደ ይመስል ሕዝብ አጫዋችነት በመደዴ እየተንሰራፋ መጥቷል።እናም ስብከት አድማጮችን ወደ ማሣቅና ማዝናናት አገልግሎት ተለውጧል። በየአደባባዩ እንደምናዳምጠው፣ የስብከቱ መርሓ ግብር ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሰባክያን በሣቅ ታፍነው እየተንከተከቱና እያንከተከቱ በሁካታ ድምፅ ድብልቅልቃቸውን የሚያወጧቸውጉባኤያት በየከተማችን ሞልተዋል። ወዘበሬታ በቃለ እግዚአብሔር ምትክ ለሕዝቡ እየቀረበልን ነው።

 

ከቤተ ክርስቲያን ስብሰባ መልስ ሆዴን አመመኝብሎ ሆድ ዕቃውን ደግፎ የመጣ የጓደኛዬን ታናሽ ወንድም ዐውቃለሁ። ጓደኛዬም የወንድሙን የሕመም ምክንያት ለማወቅ ባደረገው ጥረት የተረዳው ነገር አሳዛኝ ነበር። በአንድ ቸርችሲያዳምጥ በቈየውና አንድ ሰዓት ተኩል በፈጀ ስብከት ወቅት ይህ ብላቴና ያለማቋረጥ አንጀቱ እስኪርገፈገፍ ሲሥቅ መዋሉን ለወንድምየው ተናገረ። (በነገራችን ላይ፣ ይህ ሰባኪ ሕዝቡን የማሣቅ ጥሪ እንዳለው በአደባባይ ሲናገር ትንሽም አያመነታም። የዚሁኑ ሰባኪ መልእክት ብትሹ ከአንዱ መዝሙር ቤት ገብታችሁ የሚያሥቀውን ሰባኪ ቪሲዲ ስጡኝማለት ብቻ በቂ ነው አሉ) ኧረ፣ የመልእክት ያለህ!

 

ስብከት እግዚአብሔር ያኔእዚያለነበሩ እኒያሰዎች የተናገረውን መልእክት ዛሬእዚህላለን ለእኛማምጣት ነው። የዚህ አገልግሎት ማእከሉ መለኮት ሲኾን ኀላፊነቱ ታላቅ ነው። መላዓለሙን ከመነገር በሚያልፍ ሉዓላዊ ምጋቤው የሚያስተዳድረውን ምጡቅና ኢውሱን አምላክ ሐሳብ፣ እጅግ በበዙ ውሱንነቶች ለተሞላው የሰው ልጅ ማቅረብ ነውየሰባኪ ኀላፊነት። ይህን ኀላፊነት እንዲወጣም በጸጋ የተመረጠው ያው ውሱን የኾነው የሰው ልጅ ነውሰባኪው። ይህ እውነት ምን ይጠልቅ፣ ይህስ ጥበብ ምን ይረቅ!

 

ድካማችንና ጥረታችን የእግዚአብሔር መልእክት ለማድረስ እንጂ ሮጠን ለመታየት አይደለም። የማራቶን ሩጫ ሲዘክረው የሚኖረው ፊዲፒዲስ 42 .. ያህል ሮጦ የመጨረሻ እስትንፋሱን የሰጠው፣ የጦር ሜዳ ውሎአቸውን ድል ለማብሠር ነው። ሮጦ ቢሞትም፣ መልእክቱን ግን አድርሶ ነበር። እኛስ ተልከን የምንሮጠው ሰማያዊ መልእክት ይዘን አይደለምን? እርሱን ለማድረስ እልህ አስጨራሹን መንገድ በፍቅር እና በትዕግሥት እንሮጣለን። መልእክቱን ከማድረስ በዘለለ ምክንያት ተገፋፍተን የምንራወጥ እንደኾነ ግን፣ Run and die without a messageየተባለው ከንቱነት ይፈጸምብናል፤ ሩጥና ያለ መልእክት ሙት

 

ጆን ስቶት የመስበክ ምስጢሩ ያለው የተወሰኑ የአሰባበክ ዘዴዎችንና ብልኀቶችን በማወቅ ውስጥ ሳይኾን፣ በተወሰኑ ጽኑ እምነቶች ቍጥጥር ሥር በመኾን ነውይላሉ።61 አዎን፣ የስብከት ዘዴዎች አንደበተ ርቱዕ ሊያደርጉን ይችላሉ። ለእውነተኛ ሰባኪነት የሚያስፈልገን ግን ነገረ መለኮት ነው (ትምህርት ቤት ገብቶ ነገረ መለኮት መማር ለማለት ተፈልጎ አይደለም)። የእግዚአብሔርን ዐደራ በታማኝነት በመወጣት የምናስተላልፈው ጤናማ ነገረ መለኮታዊ መልእክት በሰዎች ሕይወት ውስጥ ለውጥ ያመጣል። የክርስቶስ ወንጌል እውነት ከጥፋት በማዳን ሕይወትን ያጐናጽፋልና። ጳውሎስን እንስማው፣ እርሱ ሞትን ሽሮአልና፤ እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል(2 ቆሮ. 110-11) ይላል። እናም የመልእክት ያለህ!” አንላለን። 

ይቀጥላል ... Part Two>>

© ይህ ጽሑፍ የትሩፋን ናፍቆት በሚል ርእስ በታተመው መጽሃፍ ላይ ሰፋ ካለ ማሻሻያ ጋር ተጽፎአል፥ የመልእቱን ጠቃሚነት በመረዳት በድጋሚ በከፊልና በተከታታይ እዚህ ድህረግጽ ላይ ይቀርባል። 

Seen 6923 times Last modified on Friday, 05 December 2014 05:38
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 131 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.