You are here: HomeOpinionsማምለክ ወይንስ ማድመቅ?

ማምለክ ወይንስ ማድመቅ?

Written by  Friday, 05 December 2014 00:00

መቼም መዘመር መልካም ነው ለጌታ የሚገባውን ማቅረብ ይገባናል መጽሐፍ ቅዱሳዊም ነው። ግን ግን አንዳንዴ ጥያቄ እንድጠይቅ የሚያደርጉኝ፡ ነገሮች አሉ እንደው እንዳላየ ሆኜ ለማለፍ ካልፈለኩ በቀር፡ አምልኮ ጭፈራችን ነው ወይንስ ሕይወታችን? አካሄዳችን ወዴት ነው? ምን እያደረግን ነው? በእኛና በዚያኛው (በዓለማዊው) ሰፈር ያለው ልዩነት ምን መሆን አለበት?


የመገናኛ ብዙኃን (Social network) በሰፊው ግልጋሎት ላይ ከዋለ ጊዜ ጀምሮ እየጨመረ እያደጉ ያሉ ብዙ ጠቃሚ አስተማሪና ግንዛቤ ሰጪ ነገሮች ማግኘት ችለናል። ይሄ እውነት ሆኖ እያለ ግን በዛው መጠን የሚጎዱ ነገሮችም የሞሉበት ሁኔታ አለ። በዚህ ሃሳብ እያለን የምንገለገልበት የዩቱብም ሆነ የፌስ ቡክ ገጾች የሚያስተላልፉት መልእክት ለአድማጫቸው የሚደርሱት የታሰበውንም ሆነ ይልተጠበቀ ውጤት የሚያመጡ ናቸው።


እንደ ክርስቲያንነቴ (ወንጌላዊ አማኝ) እንደመሆኔ በወንጌላዊ አማኞች መካከል “አምልኮ” እየተባለ የሚሆነው ነገር እጅጉን እያሳሰበኝ፡ ከመጣ ሰንብቷል። አምልኮ የሚለው ሃሳብ ከስሜት ያልተለየ የሆነ ይመስላል (ምንም እንኳ አምልኮ ያለ ስሜት ባይሆንም)። ጭፈራ እና ማምለክ ልዩነቱ ብዙ በማይታይበት አንዳንዴ እግዚአብሔርን ለማክበር የተሰበሰበ ጉባኤ ሳይሆን ጥሩ የሆነ ዳንኪራ የሚረገጥበት ቤት እስኪመስል ዘማሪው (አስመላኪው) አምላኪው የሚሆኑትንም የሚያደርጉትንም ለማን? እና ለምን? እንደሚያደርጉት በማይለዩበት መልኩ ሲዘሉ እናያለን። ይሄንን የታዘቡ ብዙዎች አሉ ብዬ እላለሁ ከአንዳንድ አስተያየቶችም እንደሚነበበው ወንጌላውያን አማኞችም ሆኑ ወንጌላውያን አማኝ ያልሆንኑት የሚሉት በርካታ ነገሮች አሉ። የአንዳንዶች ሁኔታ በሚታዩ የተለያዩ “የአምልኮ” ተብለው የተሰየሙ የቪድዮ ክሊፕ ግር ያሰኛል፡ መዘምር አይሉት መዝፈን ውዝዋዜ አይሉት አክብሮት ያሰቅቃል፡ ያሳፍራል፡ በተለይ አንባቢዎቼ እንዲረዱልኝ፡የምፈልገው የሃይማኖተኝነት ወግ ይዞኝ፡አይደለም ነገሩ አሳስቦኝ፡ነው። ወዴት እየሄድን ነው?


ከብዙ በጥቂቱ ይሄንን የዩ ቱብ ቪድዮ ይመልከቱ


ተመልካች አለን ተመልካቾቻችን አይምሮ ያላቸው ማገናዘብ የሚችሉ ናቸው። ክርስትናችን በውስጥ (አማኞች)፡ በውጭ ደግሞ የማያምኑት የሚያዩት ነገር ያለበት ሕይወት ነው። ለዚህም ነው ኢየሱስ “እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።” (ማቴ 5:16) “ብዙ ፍሬ በማፍራት ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብትገልጡ በዚህ አባቴ ይከብራል።” ዮሐ 15:8 ብሎ የተናገረው።


በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ የምናደርገውንም ሆነ የምንኖረውን ኑሮ “ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1 ቆሮ 10:31) እንደሚል ምንም እንኩዋን ነጻነት ያለን ሰዎች ብንሆንም ነጻነታችን ግን ልቅነት እንዳልሆነ ልናስተውል ይገባል “ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር አይጠቅምም…” (1 ቆሮ 6:12) በጸጋው የምንኖር ሰዎች መሆናችን ባይዘነጋም ጸጋው ግን ልቅም አይደለም ሕግም አይደለም የራሱ መጠን አለው በአንዱ ጫፍ የምናጠብቀ ወይም በሌላኛው ጫፍ የምናላላው እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል ባይነኝ።
በዘመናችን ያሉ እውቅና ያገኙ የአሕዛብ ልማድ፡ ባሕሎች ቤተ ክርስቲያንን ዘልቀው እየገቡ ይገኛሉ። እንለያያቸው! የእግዚአብሔርን እውነት ዓለማዊ ቀሚስ አልብሰን በማቅረብ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ መሞከር ካህን የነበረው አሮን ሕዝቡ ባቀረበለት ጥያቄ መሰረት እንዲመለክ የሰራውን ጥጃ እንደማቅረብ ይታያል ብዬ እፈራለሁ፡ (ዘፀ 32:5-6) ከግብጽ የወጣው የእስራኤል ሕዝብ በለመደው መልኩ (በምርኮ ምድር እንደተለማመደው) በልቡ የነበረውን አምላክ ብሎ ለሚለው ሲሰዋ የምናይበት ታሪክ ነው የዚህ ታሪክ ፍጻሜ እጅግ አሳዛኝ፡ እንደነበረ ከታሪኩ ማስተዋል እንችላለን።


ስሜታዊነት (ሁሉንም ባይሆን) ነገር ግን ጎልቶ በሚታይ መልኩ ወጣቶቻችንን የተጠናወተ ይመስላል (እድሜዬ በወጣቱ ክልል እንዳለ ይታወቅልኝ) በእግዚአብሔር ማንነት ያልተ ገራ ያልተያዘ አይምሮ እና ማንነት ለአጓጉል ስሜታዊነት ያጋልጠናል አጓጉል ስሜታዊነት ወደ አጓጉል ስህተተኛነት ይወስደናል፡ በእኛና በዚያኛው ሰፈር (ዓለማዊነት) መካከል መስመር አለ ይሄ መስመር ደምቆ መሰመር አለበት ባይ ነኝ፡ ዳዊት እርቃኑን በእግዚአብሔር ፊት ዘምሮአልና እኛን ማን ይከለክለናል? ባይ እንደማይጠፋ እርግጠኛ ነኝ። ዳዊት እርቃኑን መዘመሩ ሳይሆን ልቡም የሚያመልክ የነበረ ሰው መሆኑ ከውድቀቱም እንኳ የምንማራቸው ነገሮች አሉ (መዝ 51) ሕይወት አምልኮ ነው! እንጂ ዝማሬ ወይም ኅይማኖታዊ ተግባራቶቻችን በራሳቸው ሙሉ አምልኮ መሆን አይችሉም።


ይህንን ሁሉ ማለትህ ጥሩ ነው ታዲያ ምን ይሁን ሒስ ብቻ ነው? ወይንስ መፍትሄ አለህ ወይ? ለሚሉ ይሄንን ለመሰንዘር እሞክራለሁ።


አምልኮ እና መዝናኛን (Entertainment) መለየት


“የማታመልክ ቤተ ክርስቲያን በመዝናኛ መያዝ አለባት። ቤተ ክርስቲያንን ወደ አምልኮ የማይመሩ መሪዎች መዝናኛን የማቅረብ ግዴታ አለባቸው።” ኤ ደብሊው ቶዘር A. W. Tozer


አምልኮ የሆነ ተግባር አይደለም ነገር ግን ማንነት እንጂ።


ባለንበት ዘመን አምልኮአችንን ይዘቱን ልንፈትሽ ከዛም ባለፈ መልኩ ትኩረትልንሰጠው ይገባል እላለሁ ምክንያቱም ትኩረት ካልሰጠነው በቆይታ መጽሐፍቅዱሳዊ መልኩን ይለቅብናልና ነው። አሁንም ቢሆን ያለው ልምምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን አምልኮ ያማከለ ለመሆኑ ምን ያህሎቻችን እርግጠኞች ነን? በመድረኮቻችን የሚንጸባረቁት የተዋናይና የታዳሚ አይነት ይዘት ያላቸው ልምዶች መታየት ከጀመሩ ሰንበት ያሉ ይመስለኛል። የመድረክ አገልጋዮች ሃላፊነትን ከተቀበሉት አደራ አንጻር ምን እያደረጉ እንደሆነ ተረድተው የሚተገብሩት ጥቂቶች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጉባኤውን ሞቅ አድርገን መያዝ ነው ለአብዛኞቻችን የሚታየን በጉባኤው ላይ ሙሉ አክብሮትና ሙሉ መገዛት የሚገባውን ጌታ ወደ ጎን አድርገን በሱ ስም እኛው መሟሟቁ ላይ ነው ትኩረታችን፡፡ ከማልረሳቸው ትዝታዎች መካከል በቤተ ክርስትያን እኔና ሌሎች ወገኖች በምናገለገልበት ፕሮግራም የመምራት ተራው የነበረ አንድ ወንድም ለአገልግሎት ልምምድ ላይ በነበርንበት ሰአት የያዛቸው የአዝማቾች መብዛት ከዛም አልፎ አዝማቾቹ አንድ አይነት የሙዚቃ ቁልፍ እና ሪትም አላቸው እንጂ ያላቸው የመልእክት ይዘት የተለያየ ነበርና አንዲት እህት ምነው? ብትለው የሰጣት መልስ “አየሽ ጉባኤውን ለማግኘት እንዲህ ነው ማድረግ ያለብን። በዚህ ዝማሬ አዝማች እህት እከሊትን በዚህ ዝማሬ አዝማች ደግሞ ወንድም እከሌን በዚህኛው ደግሞ እማማ እክሌን በዚያኛው ደግሞ አባባ እከሌንና ጋሽ እከሌን አገኛቸዋለሁ።” ብሎ እርፍ። እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የአምልኮአችን ይዘት መዝናኛ ነው? ወይንስ እግዚአብሔርን ማክበሪያ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያለብን።


በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ በሆነ መልኩ በአንዳንድ የሕይወት ክልላችን ላይ በዚህ መልኩ ቢሆን ወይንም በዚያ መልኩ የሚል ቀጥተኛ ትእዛዝ ባይሰጠንም: እንደሚባለው አንዳንድ ግራጫማ የሆኑ ክልሎች አሉ፡ እንዴት እናስተናግዳቸው? ምንድን ነው መመዘኛቸው? ከዚህ በታች ባለ ሃሳብ የነገር መመዘኛ ሊሆን የሚችል በጉባኤ የዝማሬ ወይም የአምልኮ ይዘትን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ የሆነ ሃሳብ አነሳለሁ።


ነገር ግን በጉባኤም ሆነ በግል አምልኮአችን ልንከተለው የሚገባ መርህ ይሰጠናል፡ ጳውሎስ ይሄንን በፊሊጵስዩስ መልእክቱ “በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ እውነት የሆነውን ሁሉ ክቡር የሆነውን ሁሉ ትክክል የሆነውን ሁሉ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ መልካም የሆነውን ሁሉ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደነዚህ ስላሉ ነገሮች አስቡ።” (ፊሊ 4:8) ይለናል።


የነገር መመዘኛችን “እውነት የሆነው ነው“ እውነት ለሁሉም አይመችም ብዙዎች አይስማሙበትም ከብዙሃኑጋ ሳይሆን ከማይለወጠው እውነት እሱም ከቃሉ ጋር። ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል (7:18) እውነተኛነት የሚለካው ስለ እኛ ወይም ስለምን ቀበልው ክብርና ማንነት ሳይሆን የተላክንበትን በመፈጸም የላኪውን ሥራ ስንሠራ እንደሆነ ይናገራል፡ እውነት በእኛና በምናመልከው አምላክ (ዮሐ 8:34)፣ በምንኖርበት ዓለም (ኤፌ 5:9) ፣ ጠላትን በምንዋጋበት ጊዜ (ኤፌ 6:14) በዚህ ሁሉ ወሳኝ፡ነው ስለዚህ የነገር መለኪያው እውነት እንደ ቃሉ እንጂ እነደ ሁኔታዎች እንደ ብዙኃኑ መሆን የለበትም። “ቃልህ እውነት ነው በእውነትህ ቀድሳቸው፡” (ዮሐ 17:17) ይሄ እውነት የሚያደርገን ለእግዚአብሔር እንድንለይ የእርሱ እንድን ሆን ያደርገናል፤ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መምህር በዚህ ክፍል የተናገርው ነገር አለ እሱም ሰዎች ባለንበት ዘመን “እውነት ይሆን?” ብለው አይጠይቁም ነገር ግን “ይሰራልኛል ወይ?” እና “ምን ስሜት ይፈጥርልኛል?” የሚለው ነው። ነገር ግን ስሜታችን የሚመቸውን ሳይሆን በእውነተኛ ቃሉ አማካኝነት ልናስተናግደው የሚገባ መሆን አለበት ወይም ልምምዳችን በቃሉ መፈተሽ አለበት እንጂ በሌላ አባባል ልምምዳችን ቃሉን አያረጋግጥልንም ቃሉ ግን ልምምዳችንን ያረጋግጥልናል።


የነገሮች መመዘኛ “ክቡር የሆነውን” በሌላ አባባል ሊከበር የሚገባው ልከነቱ ርካሽ ያልሆነ ክቡር ባልሆነ ነገር ላይ አይምሮአችንን አናስይዝም ምድራዊ የሚያልፍ በእግዚአብሔር ፊት ስፍራ የሌለው ማንኛውም ነገር “ዜግነታችን ሰማያዊ ስለሆነ” (ፊሊ 3:20) ሃሳባችንም በሰማያዊው መመዘኛ የተለካ መሆን አለበት፡ ዘላቂነት የሌለው ቢሆን እንኳ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን “ለጥቂት ይጠቅማልና፡” (1 ጢሞ 4:8) ጳውሎስ እንዳለውና በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አለው ወይ? ለዘላለማዊው መንደርደሪያ ይሆናል ወይ? ዘላለማዊውን ታሳቢ ያደረገ ዋጋ አለው ወይ? ምንም አይደለም ተብሎ የሚታለፍ ጥቂት የሚል ነገር በክርስትና ስለሌለ የተከበረ ነገር ማለት የተከበረ ነው። ምን አደረግን? ሳይሆን ለምንድን ነው የምናደርገው? ለስሜታችን ሳይሆን ለመንፈሳችን ለተቀበልነው ላመንነው እውነት የተከበረ መሆኑ የምናሳይበት ነው መሆን ያለበት። ክቡር የምንለው “ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ” (ፊሊ 2:4) ራሳችንን ያማከለ መሆን የለበትም።


የነገሮች መመዘኛ “ትክክል የሆነውን ሁሉ” የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን ”ትክክል” የሚለው ቃል “ጽድቅ” ከሚለውጋ እንደሚዛመድ ያስረዳሉ። ትክክልን ማየት ያለብን በእግዚአብሔር የቅድስና መስፈርት የሚመጥን ሲሆን ትክክል እንለዋለን። “ትክክለኛውንና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤተ ሰዎቹን እንዲያዝ መርጨዋለሁ፡” (ዘፍ 18:19) በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛ የሆነ ፍትህ ያልተጓደለበት (መዝ 82:2) በእግዚአብሔር ፊት ሚዛኑ ያልተጭበርበረ መለኪያው ትክክል የሆነ (ምሳ 11:1 ፣ 16:11) ይህ ትክክለኛነት በእግዚአብሔር በእርሱ የሚመራ ነው፡ (ኢሳ 26:7) ፈሪሳውያን ራሳቸውን ትክክል እንደ ነበሩ ይቆጥሩ ነበር ነገር ግን በመለኪያው ሲታይ አልነበሩም (ሉቃ 18:9-14) ልንኖረው ልንከተለው የሚገባን የትክክል መስፈርቱ እኛ አይደለንም በአጠቃላይ መብታችንን የምናስከብርበትን ሳይሆን ለትክክለኛው ነገር መብታችንን የምንተውበትነ ነው የሚናገረው (ሮሜ 14:13-17)።


የነገሮች መለኪያ “ንጹሕ የሆነውን ሁሉ” ሞራላዊ ንጽሕና ምንም አይነት ክፋት (ነውር) የሌለበት ሰውነታችንን የማያረክስ በውስጥ ማንነታችንም በውጭውም እንደ ጢሞቴዎስ ለሚያዩን “በእምነትና በንጽሕና አርኣያ ሁንላቸው።” (1 ጢሞ 4:142) ደግሞም ያዕቆብ “በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት” (1:27) እንደሚናገር በኤፌሶን 5:3 “በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ” ብሎ እንደሚላቸው ይሄ ንጽሕና በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለው በተለይ (በፊሊ 1:17) ክርስቶስን ሲሰብኩ በንጽሕና እንዳልነበር እንደሚናገር የራስን ጥቅም ወይም ስውር ሃሳብ ያላነገበ ሆኖ የሚገኝ የእኔነት እርሾ የሌለበት (ማቴ 6:1-2 ፣ 1ቆሮ 5፡6 ፣ ገላ 5:9)


የነገሮች መለኪያ “ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ” እንደ አማኝነታችን ተቀባይነት ያለውን ከውስጥ፡ መነሻ ሃሳቡም ሆነ ለሌሎች ስናደርገው አስደሳች ሆኖ ሲገኝ፡ (በ 1ቆሮ 13፡ 4-7) ባለው መርህ ላይ የተመሰረተ ከላይ ካነሳነው እውነት ጋር የሚሄድ። ይህ ተወዳጅ የምንለው ርህራሄ ያለው ለሌሎች አሳቢ የሆነ፡ ይሄ ተወዳጅ የሆነው ጽድቅ የሞላበትን ሰላም ያመጣል ወይ?


የነገሮች መለኪያ “መልካም የሆነውን ሁሉ” ይሄን አይነቱ መልካምነተ በሌሎች ዘንድ እግዚአብሔርን ባስቀደመ መልኩ በእኛ ሲገለጥ፡የሚከበር ስፍራ የሚሰጠው፡ ነው። ሲደመጥም የሚወደድ በጨው እንደ ተቀመመ እንደሚል፡


“በጎነት ቢሆን ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉ ነገሮች አስቡ”። እንግዲህ በአጠቃላይ ለእግዚአብሔር ክብር ሊሆን የሚገባው “እውነተኛ፥ ክቡር፥ ትክክለኛ፥ ንጹሕ፥ አስደሳችና ምስጉን የሆኑ ነገሮችን ሁሉ አስቡ።” ብሎ ስለሚል ለየትኛውም ነገር መነሻ መስፈርት ይሆነናል በመንፈሳዊው ይሁን ምድራዊው፤ ምንም እንኳ “በእናንተም ሆነ በሰዎች የፍርድ ሸንጎ ቢፈረድብኝ፡ እኔ በበኩሌ ግድ የለኝም…በእኔ ላይ የሚፈርድ ጌታ ነው።” (1ቆ 4:3, 4) ብሎ ጳውሎስ ቢናገርም በሌላ ቦታ ግን በተቀበለው ሃላፊነት አንጻር “በዚህ በምናከናውነው የቸርነት ሥራ አንዳች ነቀፋ እንዳይገኝብን እንጠነቀቃለን። ምክንያቱም ዓላማችን በጌታ ፊት ብቻ ሳይሆን በሰውም ፊት መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ነው።”

(2ቆሮ 8:20-21)

ፍርድ አይደለም ተጠያቂነትና ኅላፊነት ነው!


እንደ ክርስቲያን ነገሮችን እየተጠቀምንባቸው ነው? ወይንስ ነገሮች እኛን እየተጠቀሙብን ነው? ለየትኛውም እርምጃችን ምላሽ እንሰጥበታለንመልካምም ሆነ ክፉ፡ የትኛውም እርምጃችን በልባችን ካለ እውነተኛ ንጽህና የመነጨመሆን አለበት ራስወዳድነት የሌለበት (እኔን ይመቸኝ፡እንጂ ስጋ መብላቴ ማንም አያገባውም) በሚልመንፈስ ሳይሆን ለወንድማችን መልካምነት እና ለእግዚአብሔር ክብር መዋል አለበት።“ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ለምንስ ወንድምህን ትንቃለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና… ስለዚ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ፊትመልስ እንሰጣለን።” (ሮሜ 14:10ና 12)

 

© ይህ ጽሑፍ www.deqemezmur.wordpress.com ከሚባል ብሎግ (Blog) ላይ የተወሰደ ነው።

Seen 5708 times Last modified on Friday, 05 December 2014 04:23

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 79 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.