You are here: HomeOpinionsምን እንብላ?

ምን እንብላ?

Written by  Tuesday, 16 December 2014 00:00

በየቦታው የታጠፈ አንጀት አለ ፤ ጠኔ እያላጋ ከየምናምኑ ጋር የሚያጋጨው ክልውስ ፍጡር መንገዱን ሞልቶታል ፤ ርቦት ነው፡፡ የክት ልብሱን ለብሶ ቢወጣም የሰረጎደ ዓይኑ ችጋሩን ያጋልጥበታል፡፡ ከጥውልግ ባልጀሮቹ ጋር ለማቅራራት ቢሞክርም ምላሱ እየተሳሰረ ቁና ቁና ይተነፍሳል ፤ የመሬት እንጀራ ሳይሆን የሰማይ መና ርቆታል፡፡

 

ቤተክርስቲያን መጋቢት ልትሆን ሲገባት ሌማትዋ ተራቆተ፡፡ የልጆችዋን ዓይኖች መንከራተት እያየች ከየጎዳናው የለቃቀመችውን ሳር ፤ ገለባ በመሶቡ ላይ ትከምራለች፡፡ መብል መስሏቸው ሲስገበገቡ አፋቸው አሰር ይሞላል፡፡ ባእዱ ሠርዶ ያሰክራቸው ካልሆነ ያጠግባቸው ዘንድ እንዴት ይችላል?

 

እውነተኛውና ኃያሉ ቃለ እግዚአብሔር በመድረኮቻችን ላይ በሰፊውና በሥርዓቱ አልቀረበም፡፡ በየግል ሕይወታችንም የቅዱስ ቃሉ በረከት የሩቅ ትዝታ እየሆነብን በያለንበት እያዛጋን አለን፡፡ ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት መለገሙ አሁን ግልጥ ሆነ፡፡ በየምዕራፉ ፥ በየቀኑ ፥ ዳውላ ዳውላ እንተነፍሳለን፡፡ የጽድቅን ዳገት መውጣት አቃተን ፤ የወንጌልን ብርቱ ሩጫ ገና ሳንጀምረው እናለከልካለን ፤ የፍቅርን ዐቀበት ፥ የሰላምን ጉብታ መውጣት ተሳነን፡፡ ለምን ዓቅም አነሰን ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

 

“የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል፡፡” i ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረው ፥ ጉልበት ለራቀው ህዝብ ድጋፍና ምሰሶ የሚሆነው ታላቅ ጸጋ የሞላበት የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያሳየናል፡፡

 

በሌላ ወሬ ፥ አሉባልታና ፥ ትዕይንት የሰው ነፍስ ቀና ሊል አይችልም፡፡ በግል አስተያየታችን ፥ በካበተ ባሕላችን ወይም እኛው በቀመምነው ፍልስፍና የማንም ልብ አይቃናም፡፡

 

ተንኮል የሌለበትን የቃሉን ወተት ስንጠጣ ፥ ከማርና ከወለላውም ይልቅ የሚጣፍጠውን ሕገ እግዚአብሔር ስንመገብ እንለመልማለን ፤ የተስለመለመው ዓይናችን ቦግ ብሎ ይከፈታል ፤ የተጣበቀ ምላሳችን ለጤና ንግግር ይፈታል፡፡ የዛሉ እጆች ለሥራ ይቀለጥፋሉ፡፡ ነብዩ “የተማረ የሠለጠነ ምላስ ሰጥቶኛል” እያለ ስለ እግዚአብሔር ባሪያ ይናገራል፡፡ እንግዲያው የቃሉ ሠንጋ በስልጡን ቢላዋ ሊበለት ይገባዋል ማለት ነው፡፡ “የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል የሚናገር የማያሳፍር ሠራተኛ” ii እንዲሆን ጢሞቴዎስ ተመከረ፡፡ መጽሐፉ በእጃችን መኖሩ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምናጠናው ፤ እንዴት እንደምንተረጉመው ፤ እንዴት እንደምናቀርበው ማወቅ ፥ መሠልጠን ፥ መልመድ ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡ ከሁሉ በላይና በፊት ይህ ሥልጠና በመጽሐፉ ደራሲ ወደ ሰዎችም እንዲደርስ ቀስቅሶ የሚልከን በዚያ የጥበብ ሁሉ ባለቤት በመንፈስ ቅዱስ የሚካሄድ ሥልጠና ነው፡፡ ወዳጆች ሆይ ከቅዱሱ መንፈስ በርጋታ ከተማርን ‘ያላዋቂ ሳሚ’ አንሆንም፡፡ ያ መንፈስ ለአገሩ ሁሉ ከመናገራችን በፊት ለየልባችን ጆሮ እያስተነተነ ሊነግረን ያሻል፡፡ እንዲያውም የተማረ ምላስ በሠለጠነ ጆሮ በኩል ነው የሚገኝ ፤ ነቢዩ እንደተናገረ “… ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል ፥ እኔም አመጸኛ አልነበርኩም” iii የሚል የዘወትር ተማሪነት ብቻ ነው የሚያዋጣን፡፡

 

ሜዳውን የሞላው ሳርና ሥራስር አብዛኛው ገዳይ መርዝ ነው ፣ ያልገደለም እንደሆነ ፥ ዐቅም እያሟሰሰ ፥ አጥመልምሎ ቤት የሚያውል ፣ ወይም ልቦና እያናወዘ የሚያስቀባዥር ክፉ ሥራይ ነው፡፡

“መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞ ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል” iv 

ለመሆኑ ምን ዐይነት ቅጠል ነው አሁን በየሜዳው ያለው? ለጊዜው አምስት ያህል እንጥቀስ፡-

 

  1. መስኩን የሞሉት የክርስቶስን መስቀል ትሩፋቱን እንጂ አርአያውን የማያነሱ ትምህርቶች ናቸው፡፡ ስሙን እያነሱ ፥ ያስገኘልንን ጥቅም እየዘከሩ ነገር ግን መስቀሉ የህይወት ዘይቤ የአካሄድ ፋና የሌለው ይመስል በረከቱን ዘርፎ የራሱን ሩጫ ሰው ሁሉ እንዲሮጥ የሚያበረታቱ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ሲሞት ያስገኘልን የኃጢአት ስርየት ፥ ዕርቅና አፅድቆት የዘለዓለም መዝሙራችን ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በዚሁ ሞቱ እንዴት እንደምንኖርም አሳይቶናል፡፡ ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዛዥነትን ፥ ወንድምን በማስቀደም የትህትናን አረማመድ ፥ ሌሎችን ሁሉ በመውደድ በመሥዋዕታዊ ፍቅር መኖርን ፥ በክፉ ዓለም ውስጥ ጽድቅን ሳያዛንፉ በጽናት መቆምን ፥ ከስግብግብ ራስ ወዳድ መንፈስ ተላቆ ለሌሎች በልግስና ማካፈልን ፥ የማዳን ፥ የማትረፍ መልእክተኛ መሆንን ወዘተርፈ፡፡ እንግዲያው መስቀሉ በታሪክ ውስጥ አንድ ነጥብ ብቻ ሳይሆን ረዥም የሕይወት ጎዳናም ነው፡፡ መስቀሉ የመዳናችን ዐዋጅ ብቻ ሳይሆን የኑሮአችንም አርኣያ ነው፡፡

  2. የእግዚአብሔርን መንግሥት ከመስበክ ይልቅ የሰውን መንግስት ማስፋፋት ፣ ያሁኑንና የዚህን ዕለታዊ ኑሮ ምኞትና ጥማት ለማሟላት ገንዘብ-ንብረታዊ ብልጽግናን እንደ ባንዲራ ማውለብለብ በየመስኩ ላይ የበቀለ ሌላ እንግዳ ዘር ነው፡፡ የወንጌል ርዕሰ ጉዳይ ገንዘባዊ ድኽነትም ሆነ ገንዘባዊ ብልጽግና አይደለም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚገኘው ዘላለማዊ ሕይወት የምሥራች ነው፡፡ ይህን የምሥራች በዓይን ጥቅሻ ብቻ እየነገሩ ዋናው ውትወታ ግን እንዴት ብዙ ገንዘብ ፥ ብዙ ሞቾት ፥ ብዙ ስኬት እንደሚገኝ በሺህ ሃሌሉያና አሜንታ እየታጀቡ ማስተጋባት ከሆነ ከጥሪያችን መስመር ተሳስተን ወጥተናል፡፡ በክርስቶስ ተከታዮች ልቦና ፍቅረንዋ ማራባት ፥ ሃይማኖትን የስግብግብነት ችግኝ ማፍያ መደብ ማድረግ እንዴት አያስጠይቀንም ትላላችሁ? ለተቀደሰው የጌታ አገልግሎት ገንዘብ የመስጠትን የፍቅር ልግስና በአጸፋው በሚገኝ የደለበ ኪስ ተስፋ እንቁልልጬ እንዴት እንቀሰቅሳለን? የዕለት ጉርስ ፥ የዓመት ልብስ እያጡ ወንጌል በሰበኩት ቀዳሚዎቻችን ላይ የምንሳለቀው በምን ድፍረት ነው?

  3. ሰው ክቡር ፍጡር ነው ፤ የመለኮት እንደራሴ ሆኖ በምድር ላይ ተሹሞአል፡፡ ይሁን እንጂ አመጽ ባደፈረሰው ውሃ ስለተጠመቀ ከሰማይ በተላከው ጌታ ንጹህ ደም መታጠብ አለበት፡፡ ታጥቦ ሲያበቃም ግን ፍጡርነቱ አይቀየርም ፥ አበሳው ይወገዳል እንጂ፡፡ አንድ ጌታ ብቻ ባለበት ሁለንታለም ሎሌነቱ አይቀየርም፡፡ ይልቁን አሁን ከዲያብሎስ ባርነት ከራሱም እስራት ተፈትቶ ለሞተለት ጌታ ታማኝ አገልጋይ እንዲሆን ታጭቷል፡፡ ታዲያ በየስብከቱ የሚደመጠው የሰው ልጅ ልዕልና ፥ መለኮት-አከል ግርማና የነገር ሁሉ ማእከል እስኪመስል ድረስ ማንቆለጳጰስ ምን ይባላል? “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና ፤ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን፡፡” v ብሎ የጻፈው ነገሩ በጥልቅ የገባው ሐዋርያው ጳውሎስ አጉል መሞካሸትን እየወረወረ የሚጥል ቆፍጣና ሰው ነበር፡፡

  4.  በየተረተሩ ፥ በየጉብታው አጀፍጅፎ የበቀለው ሸለቆውን ሁሉ የሞላው ሳር ደግሞ ሽለላን ፉከራን ክንብንብ ያደረገ ባዶ ጩኸት ነው፡፡ በድምጽ ብርታት የሚያምን ፣ ጥሞናን እጅግ የሚፈራ በጸጥታ የሚፈሰውን ሰማያዊ ኅብረ ዜማ ለመስማት ጆሮው ያልተቃኘ ፥ የራሱን ድምጽ በመስማት ግን ጮቤ የሚረግጥ የሁካታ እንቅስቃሴ አለ፡: ለሰላምታውም ለአቤቱታውም ፥ በጎዳናውም በጉባኤውም ሁልጊዜ መጮህ፡፡ “ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ”vi ያለው ቅዱስ መጽሃፍ “ምድር ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል” vii ደግሞ ብሏል፡፡ ለመቦረቅ ጊዜ አለው ፣ ለአርምሞም ጊዜ አለው፡፡ የመጽሐፍ ቃል ለማስተጋባት ጊዜ አለው ፣ የመጽሐፍ ቃል ለመመርመርም ጊዜ አለው፡፡ ከነግህ እስከ ሌሊት የመጮህ ዕዳ አልተጣለብንም፡፡ ይህ በየስፍራው የምንሰማው ከባድ ጫጫታ የውስጥ ባዶነት ማባበያ ይሆንን እያልሁ እፈራለሁ ፣ ነገር ግን ከንቱ ጫጫታ ባዶነት ያባብሳል እንጂ አይፈወሰውም፡፡ ዝላይና ግርግር ሊያሳብደን ሲደርስ ልቦናችንን እንዳንስት አንዳንዴ ወደ ምድረበዳ መሸሽ ያሻን ይሆን? ጌታችን እንደዚህ ማድረግ ልማዱ ነበር፡፡ viii

  5. ቤተክርስቲያን የገበያ ሥፍራ ፥ አገልጋዮቿን ሸቀጥ እየደረደሩ የሚነግዱ ባለሱቆች ፣ ምእመናኑንም በነጻው ገበያ እየዞሩ ያሻቸውን የሚገዙ ሸማቾች አደረግናቸው፡፡ ቅዱስ ደሙን አፍስሶ የገነባትን የቤቱን ባለቤት መስደባችን እኮ ነው፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል አለ ix ፣ የመንፈሱ ማደሪያ ለመሆን አብረን የመንሠራ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነን ተባለ፡፡ x  ይህን ሁሉ እየሰማንና እኛም እወራን ርግጡን ስንጠይቅ ግን ቤቱ የሸማችና የሻጭ ዐደባባይ መሆኑን መካድ አልቻልንም፡፡ እኛ አገልጋዮቹ ገበያ እንዳናጣ የማናጤሰው ጢስ የለም፡፡ ሸማቹ ሕብረተሰብም እንደሱቅ የሚያያትን ቤት አዳዲስ እቃ ካልገባ ጥሎ ለመሄድ አያመነታም፡፡ “ክብርት የሆነች ቤተክርስቲያንን ለራሱ ሊያቀርብ” xi ሙሽራው እየተጋ ሳለ የኛ ውሎ ግን ሌላ ጉዳ ላይ መሆኑ እጅግ እንግዳ ዘር ነው፡፡ ከክፉ ዱር ነፋስ ያመጣው ባዕድ ተክል ነው፡፡

 

እና ወገኖቼ የጤና ምግብ ካልበላን ፣ በራብ የጠወለገውንም ሕዝብ ባገኘህበት ቃርም ካልነው ተያይዘን ማለቃችን ነው፡፡ “እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሙያተኞች ስንት ናቸው?” xii ብሎ እንደጠየቀው ጎበዝ ወደልባችን እንመለስ፡፡ ደጉ አባታችን ቆሞ እንዲህ ይለናል፡- “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውሃ ኑ ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ፥ ብሎም ፥ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ፡፡ ገንዘብን እንጀራ ላይደለ ፥ የድካችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡን በረከትንም ብሉ ፤ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው፡፡ ጆሮአችሁንም አዘንብሉ ፣ ወደ እኔም ቅረቡ ፤ ስሙ ፥ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፡፡xiii

 

ጥቅሶች

i ኢሳ 50፡4

ii 2ጢሞ 50፡5

iii ኢሳ 50፡5

iv 1ጢሞ 4፡1-2

Seen 12971 times Last modified on Monday, 22 December 2014 17:11
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 83 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.