መግቢያ

Published in የመንፈሳዊ ተሐድሶ ጥሪ አገር አቀፍ አውደ ጥናት Friday, 12 June 2015 00:00
Dr. Simon Mulatu Dr. Simon Mulatu

እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ፤” ሰቆ 5፡21

 

በኢትዮጵያ ያለችው ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ምኅዳሮች ውስጥ እያለፈች እዚህ ደርሳለች፡፡ ያለፈችባቸው ሁኔታዎች በአካሄዷ ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ እንዳሳደሩባት የታወቀ ነው፡፡ በስደት በተጓዘችባቸው ዓመታት በኅብረት መሰብሰብ አስቸጋሪ ሆኖ፣ ብዙ አብያተ የማምለኪያ ቦታቸውን አጥተው በኅቡዕ በመደራጀት በመኖሪያ ቤቶች መሰብሰብ ተገደው ነበር፡፡ የተዘጉት በከፍተኛ ስደት ውስጥ ሲያልፉ አንጻራዊ ነፃነት የነበራቸው ደግሞ በአመዛኙ አገልግሎታቸውን ለማስቀጠልና ወደ እነርሱ ለመገልገል የመጡትን ለማስተናገድ በራቸውን በመክፈት ተጠምደው ቆይተዋል፡፡

 

በወቅቱ በነበረው ስደት የራሱ የሆነ ተጽዕኖ በቤተ ክርስቲያን ላይ ቢያሳድርም በዚያ ጊዜ የነበረው ወንጌላዊው ክርስቲያን ማኅበረ ሰብ በአብዛኛው የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቅ የሚያስቀድም ቁርጠና ወገን ነበር፡፡ ለፍቅር፣ ለአንድነትና ለኅብረት ነፍሱ የነቃች በጉጉት ወደ እግዚአብሔር ማኅበር የሚገሰግስ፣ ለሕይወት ንጽህና ክቡር ስፍራ የሚሰፈጥ ጠንቃቃ ሕዝብ ነበረ፡፡ በዚህም ምክንያት በሚቃወሙት የኅብረተሰብ ክፍሎች እንኳ ስለ ታማኝነትና ትጉህ አገልግሎት በየቦታው የሚፈለግ ማኅበረ ሰብ ነበረ፡፡በስቃይና በመከራ ውስጥም የወንጌልን ብርሃን በየጥቊ ለመለኮሽ ቅንዓት ነበረው፤ በዚያ ሁኔታ የማይጠበቅ ትልቅ ዕድገት በቤተ ክርስቲያን ተከስቷል፡፡ በቤት፣ በሰፈር የቆረጠ በእጦቱ ለመጽናት፣ ሀብት ንብረቱን፣ ሹመት ማዕረጉን እንኳ ስለ ጌታና ስለወንጌሉ ሲል ለማጣት ዝግጁ የሆነ ብርቱ ማኅበረ ሰብ ነበረ፡፡

 

የስደቱ ዘመን አልፎ የነጻነት ወቅት ሲተካ ለቤተ ክርስቲያን ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ፤ ደጆች ተከፈቱ፤ ወንጌል ሥርጭት አደባባይ ወጣ፤ የጀማ ስብሰባዎችና መነቃቂያዎች ቀድሞ በማይታሰቡ እንደ ጃን ሜዳና ብሔራዊ ስታዲየም በመሰሉ መስኮች መካሄድ ጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መመሥረትም በቤተ እምነቶች መካከል መቀራረብን ሲፈጥር የወንጌል ተልእኮን ሥራም በቅንጅት ለማካሄድ ዕድል አመቻቸ፡፡ በአንድ በኩል መተናነጽ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልምድና አገልጋይ መለዋወጥ በአማኞች መካከል የነበረውን ኅብረት በመጥቀም ረገድ የነበረው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነበር፡፡

 

ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድራችን በተከበረው የእምነት ነጻነት የተነሣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት እየሰፋ መምጣት ብቻ ሳይሆን ለበለጠ እድገትና ተሳትፎ ያለው ተስፋ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እነዚህ አመቺ ሁኔታዎች ብዙዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲጨመሩ፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ከእጥፍ በላይ እንዲጨምር፣ በኅብረተ ሰቡም ውስጥ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት እንቅስቃሴና ተሳትፎ የበለጠ ዕውቅና እንዲያገኝ ረድቷል፡፡ ከምንጊዜውም ይልቅ ዛሬ የአገልጋዮችና የአገልግሎቱም መንገድና ዐይነት እየበረከተ መጠቷል፡፡

 

በዚህ ሁሉ መልካም አጋጣሚ መካከል በቁጥር እየጨመረ የሚሄደው የአማኞች ብዛትና ያንንም ተከትሎ የሚከተለው ቤተ ክርስቲያን መበራከት ብዛት ያላቸው አገልጋዮችን ይበልጥ አስፈላጊ እያደረገ ሄደ፡፡

 

ይህንንም ተከትሎ የተጠናከሩትን አዲስ የተከፈቱት የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ለብዙዎች ዐይን ገላጭ በመሆንና ደርዝ ያለው ትምህርት ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው አመለካች መሆን ጀመሩ፡፡ የእነዚህ ተቋማት መብዛትም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና አመራር ላይ የራሱን መልካም አሻራ ማሻረፍ ችሏል፡፡ እየታዩ ላሉት በጎ ሥራዎች ሁሉ ክብሩ ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡

 

እነዚህ በጎ ሁኔታዎች የሚያበረታቱን ቢሆንም እንኳ፣ ነጻነት ካልተከበረበት ዘመን አንጻር እንኳ ሲታይ ዛሬ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ያሉበትን ሁኔታ በአንክሮ ለሚያይ ሰው እጅግ አሳሳቢ ጉዳዮች በፊታችን እንደተደቀኑ በግልጽ የሚታይና በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሣ ነው፡፡

 

 • ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር የሰጠንን ሰፊ የወንጌል አገልግሎት እድል በአግባቡና በብቃት እየተጠቀምንበት ነው ወይ)
 • እግዚአብሔር ከሰጠን ሰፊ የእምነት ነጻነትና ከአገልግሎት እድል አኳያ በኅብረተ ሰቡ ዘንድ የሚጠበቀውን ያህል በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ችለናል ወይ) ኑሮአችን አካሄዳችን ጌታን የሚያስከብር፣ የጌታ መሆናችንን በግልጥ የሚያሳይ መልካም ምስክርነት ያለው ነው ወይ)
 • በብዙ ስፍራና ሁኔታዎች የሚገለጠው አስተምህሯችንስ እውነትን የሚያሳይና የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል የሚገልጥ ነው ወይ) ወይስ ለብዙዎች ግራ የሚያጋባና ሲያልፍም ለስህተት የሚዳርግ ሆኖ ነው የሚታየው)
 • አስተዳደራችን ጽድቅንና ፍትሕን መቀባበልንና መከባበርን ያሳያልን)
 • የቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር መርሃችን ምን ያህል መንፈሳዊና በጎ ሥነ ምግባርን የተከተለ ነው)
 • ችግሮቻችንን በሰከነ አመራር በመንፈሳዊ አካሄድና እግዚአብሔርን በመፍራት መንገድ መፍታትስ ችለናል ወይ)
 • ይቅርታ ማድረግና እርቅን በሚመለከትስ በውስጣችን የሚታየው ገጽታ ምን ይመስላል)

 

የሚሉትና ሌሎችም ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን አጠቃላይ የአመራር፣ የአስተምህሮና የአምልኮ አቅጣጫዎቹን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ደጋግመው እየተነሡ ነው፡፡

 

ስለሆነም ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ መልካሙንም ደካማውንም በተለያየ አቅጣጫ ያጋጠሙንን ቀውሶች በየፈርጁ ማስቀመጥና ማየት የወቅቱ ጥያቄ መሆን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር የጣለብን አደራ መሆኑን እናምናለን፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በመካከላችን እየገዘፉ ለመጡት ተግዳሮቶች ወቅታዊ ምላሽ መስጠት ካልቻልን አገልግሎታችን ሁሉ አሳፋሪና አስከፊ እንደሚሆን፣ አንድነታችንና ኅብረታችን እንደሚደክምና እንደሚፍረከረክ ያገኘናቸውም የአገልግሎት ዕድሎች ሁሉ ሊመክኑ እንደሚችሉ የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡

 

በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን በመምራት በተለያየ ቦታና ኅላፊነት ላይ ያለን ሁላችን ይህንን ሰማያዊ አደራ በቸልተኝነት ልንመለከተው እንዴት እንችላለን) ቃሉ የሚለን “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አደርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ጠንቀቁ” (ሐሥ 20፡28) ነው፡፡ ለዚህ ተግዳሮት መልስ በመስጠት ቤተ ክርስቲያን እየሄደችበት ያለውን ይህንን የቁልቁለት ጉዞ መግታት ካልቻልን በእግዚአብሔርም ዘንድ በትውልድም ተጠያቂ ከመሆን አናመልጠም፡፡

 

ይህን በፊታችን የተጋረጠ አደጋ ለመቋቋምና ለማስወገድ ዛሬ ምን እናስብ) ምን እናድርግ) የአሁኑ ወቅት ይህ ብርቱ ጉዳይ የሚመለከተን ሁሉ በጥሞና ሆነን የምንጠያየቅበት፣ የሕያው አምላክን ፊት የምንሻበት የእድሳት ኅይልና ብርሃን የምንማጠንበት ወሳኝ ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም ጉባኤ የተጠራው በዚህ አሳሳቢ ምክንያት ነው፡፡

 

ይህ ጉባኤ ለመጠራቱ ምክንያት የሆኑ ወገኖች በጊዜው ስላለው የክርስቲያን ማኅበረ ሰብ ጠቅላላ ሁኔታ እየቃኙ፣ እያሰቡ እና እየጸለዩ ለሁለት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ይህንን ሸክም ለብዙዎች የማካፈልን አስፈላጊነት በመገንዘባቸው ሐሳባቸውን ለሌሎች ሲያካፍሉ ቆይተዋል፡፡ አሁን ያለንበት መንፈሳዊ ውደቀት ዋናዎቹ በሦስት አቅጣጫ ተገንዝበዋል፤ ይኸውም፡-

 

 1. በሕይወት ጥራት፣
 2. በአስተምህሮ ጥራት እና
 3. በአመራር ጥራት አኳያ መሆናቸውን ተገንዝበዋል

 

ይህንን ሸክም ሸክማቸው አድርገው የሚያገለግሉ ስድስት የአገልግሎት ድርጅቶች ዓላማ በመቅረጽ፣ ስልት በመንደፍ፣ ግብ በማስቀመጥ ችግሩ የጋራ ችግር ሆኖ በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ በግንባር ቀደምትነት የማነሣሣትና የማትጋት ሚና ለመወጣት ተሰልፈዋል፤ እነርሱም፡-

 

 1. ቢብሊካ ኢትዮጵያ
 2. የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ምሩቃን ማኅበር (
 3. ደወል የወንጌል አገልግሎት
 4. ቃለ እግዚአብሔር አንባብያን ማኅበር
 5. ጎልደን ኦይል አገልግሎት
 6. ኢቫንጀሊካል ቲዮሎጂካል ኮሌጅ() ናቸው፡፡

 

ይህ ጊዜ ከወደቅንበት የመነሣት ከኮበለልንበት የመመለስ የንስሓና የተሐድሶ፣ የለውጥ ወቅት ሊሆን እንደሚገባ በጽኑ እናምናለን፤ ይህም እምነትና ሸክም የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እንደ ሆነ እና የተግባሩም ሂደት እየጨመረ በሁሉ ዘንድ ሊሰርጽ የሚገባ መሆኑም እሙን ነው፡፡

 

ሁላችንም ልብ ልንለው የሚገባው ነገር የዚህ መሰባሰብ ትኩረቱ መልካም መልካም የሆኑ ገጽታዎቻችንን ነቅሰን እያወጣን ለመጽናናትና ራሳችንንም ለማሞካሸት ሳይሆን ራስን ለመፈተሸ፣ ለመመለስና ለመታደስ ነው፡፡ ስለሆነም ሆን ተብሎ አሳሳቢ በሆኑ ገጽታዎቻችን ላይ የምናተኩርበትና የሚለወጡበትን ሁኔታዎች በመቃኘት አዎንታዊ ለውጥን ለማግኘት የምንሻበት ነው፡፡ ድክመቶችም ሲነሡ ሁሉም ድክመቶች ሁላችንንም በእኩል ደረጃ ይመለከታሉ ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ድክመቶች ከእኛ የተወሰነ ክፍልን ብቻ የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይሁንና ድክመቶቹ የሁላችንም እንደሆነ የሚያመለክት ቋንቋ መጠቀም ተመርጧል፤ ምነው ቢባል አንዱ ፈራጅ ሌላው ተፈራጅ የሚሆንበት ጉባኤ ስላልሆነ ነው፡፡ ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን የሚል እሳቤን የተመረኮዘ አቀራረብ ነው፤ የሚቀረቡትም ጽሑፎች በዚህ መልክ ነው የተቀረጹት (የዕዝራን፣ የነህምያንና የዳንኤልን ጸሎቶች ያስታውሷል)፡፡

 

ይህ ጉባዔ ከአንድ ወገን የችግሮች መፍትሔ የሚቀርብበት ገበታ ሳይሆን ሁላችንም በጋራ ምክክርና ጸሎት በንስሓ በመመለስ ለርምጃ የሚበጀንን ፈለግ የምንቀይስበት፣ መንገድም የምንጠርግበት ነው፡፡

 

እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልን፣ ይመልስልን፣ በመመለስ የሚገኘውን የሕይወት ሙላት ይላክልን፡፡ ተልእኳችንንም የመወጣት ልብና ዐቅም ይለግሰን፡፡ አሜን፡፡

Seen 3324 times Last modified on Friday, 12 June 2015 10:03

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 94570 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.