ጽሑፍ 1 - የሕይወት ጥራት

Published in የመንፈሳዊ ተሐድሶ ጥሪ አገር አቀፍ አውደ ጥናት Friday, 12 June 2015 00:00

ምግባረ ብልሹነት ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ይህም የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ዛሬ ያለነው ወንጌላውያን ቤተ እምነቶች “. . . የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ . . .” (1ጴጥ. 1፥14-15) የሚለውን አምላካዊ ጥሪ/ግብዣ የዘነጋንበት በትኩረትም የማናስተምርበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ቅዱሱ ወንጌል በቅድስና መያዝ ያለበት መሆኑን ማስተጋባት ቸል የተባለበት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የቅድስናን ኑሮ ወደ ጎን የተተወበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ሁሉ እነሱም ከዓለም አይደሉም፡፡ ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው (ዮሐ 17፥16-17)” በማለት ጌታ ኢየሱስ የጸለየውን ጸሎት ዘንግተነዋል፡፡ ለቅድስና ባይተዋር የሆነች ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ኢየሱስም ባይተዋር መሆኗ አይቀርም፡፡

 

የዘመኑ ወንጌላዊ ክርስትና አቅፎ ለያዛቸው ምእመናን ብቻ ሳይሆን ከውጭ ላሉትም ጆሮ የሚቀፍ፣ ለማሰብ የሚዘገንን የሞራል ውድቀትና የኑሮ ሰንካላነት እያስተናገደበት ነው፡፡ ይህ ውድቀት የእግዚአብሔርን መንፈስ የሚያሳዝን፣ ጽድቅን የሚያፈቅሩትን አንገት የሚያስደፋ፣ ላልዳኑትም የወንጌሉን ብርሃን እንዳያበራ የሚጋርድ የጨለማ ሥራ ነው፡፡ ለዘብተኛ ከሆነ አመለካከትና አስተምህሮ የተነሣ አማኞች በዕለታዊ አኗኗራችን ክርስቶስን በማሳየት ብርሃንና ጨው ከመሆን ይልቅ በምግባረ ብልሹነትና በልዩ ልዩ የሕይወት ጉድለት የምንከሰስ ሆነናል፡፡ ከዚህም የተነሣ ቤተ ክርስቲያን በኅብረተ ሰቡ ላይ የጽድቅ ጫና ማሳደር አልቻለችም፡፡

 

የክርስቶስ ተከታይ መሆን የሰውን መላ ሕይወት የሚዳስስ ታላቅ ጥሪ ነው፡፡ የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ወልድ ጋር መተዋወቅ ሕይወትን መቀበል ነው፡፡ ‹‹ልጁ ያለው ሕይወት አለው›› ክርስቲያንነት በቀዳሚ ደረጃ የእምነት አንቀጽ መቀበል ወይም የአምልኮ ሥርዐት መውረስ ወይም በቤተ ክርስቲያን ማኅበር ውስጥ መመዝገብ ሳይሆን አምላክም ሰውም ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የሚደረግ ሕያው ግንኙነት ነው፡፡ ከዚህ ግንኙነት አዲስ ሕይወት ይፈልቃል፤ ይህ ሕይወት የሚያድግ፣ የሚጎለብት፣ እየበሰለ የሚሄድ ንቁ ሕይወት ነው፡፡ ሊያሳ ድገው የሚችለውን ንጹሕ ምግብ ሲያጣ፣ ከሕይወት መስመሩ ከግንዱ ጋር ያለው መያያዝ ሲላላ፣ መርዛማ ነገር ሲጠናወተው ግን በማደግ ፈንታ ይደገድጋል፣ እየከሣ፣ እየሟሸሸ ይሄዳል፡፡

 

የክርስቶስ ሕይወት በጋራ የሚካፈሉት ገበታ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህን ሕይወት የምንካፈልባት ማኅበር ናት፡፡

 

ወንጌላዊ የሆነው ይህ ማኅበረ ሰብ ዛሬ የግልም ሆነ የማኅበር ሕይወቱ በጣም አጠያያቂ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እውነተኛው ክርስቲያናዊ ሕይወት በቅዱስ አኗኗር፣ በመልካም ሥነ ምግባር፣ በደማቅ ምስክርነትና በፍቅር ሊገለጥ ሲገባው በአስደንጋጭ የሞራል ውድቀት፣ በተፈረካከሰ አንድነት፣ በተዛባ የኑሮ ዘዬ ከዚህም የተነሣ በተከሰተ ተጽእኖ አልባነት የታወቀ ሆኗል፡፡

 

የሕይወት ጥራት ችግሮቻችን ምንድን ናቸው? እንዴት ልንኖር ይገባናል? ምን ዐይነት የእድሳት ርምጃዎች ያስፈልጉናል? የሚሉትን ብርቱ ጥያቄዎች ይዘን ልንነጋገር፣ ያለንበትን ሁኔታ ልንቃኝና ወደ ጠራው ሕይወት አኗኗር ልንመለስ ይገባል፡፡

 

ሙሉ የጥናታዊ ጽሁፉን ከዚህ በታች ባለው ሊንክ ዳውንሎድ ማድረግ ይችላሉ።

Seen 5180 times Last modified on Thursday, 02 July 2015 08:35
More in this category: « መግቢያ

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 38 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.