You are here: HomeSocial Issues “ዓይን”- ትልቁ የገና ስጦታ

“ዓይን”- ትልቁ የገና ስጦታ

Written by  Monday, 22 December 2014 00:00

የታህሣስ ወር የልደት ግርግር ሞቅ ብሏል፡፡ የገና በዓል ከሀይማኖታዊ ምንነቱ በላቀ ሁኔታ የገበያ እድል መሆኑን የተገነዘቡ ኩባንያዎችም እድሉን ለመጠቀም ማስታወቂያዎቻቸውን በማስጮህ ላይ ይገኛሉ፡፡ በየቤቱ የሚሰሙ ጥያቄዎችም፡- “አባቢ/እማሚ ለገና ምንድን ነው የምትሰጡን?” የሚሉ ሆነዋል፡፡ አንዳንድ ደፈር ያሉ ልጆችም የሚፈልጉትን የስጦታ አይነት ጠቅሰው ይጠይቃሉ፡፡

 

እኔ እንኳን ዛሬ እግረ-መንገዴን ስለ ዘመኑ የገና ስጦታ አነሳሁ እንጂ ለመጻፍ የተነሳሁበት ፍሬ ነገር በመጀመሪያው የጌታችን ልደት ሰሞን የተለየ ስጦታ ከአምላክ የተቀበሉ ሰዎችን የሚመለከት ነው፡፡

 

ሁለት ሺህ ዓመታትን በምናብ ወደ ኋላ ልውሰዳችሁ፡፡ ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት ከድንግል በተለየ ታምር የመጸነሱን ምስጢር የሚያውቁ ጥቂት የቤተሰብ አባላትና የቅርብ ወዳጆች ብቻ ነበሩ፡፡ ለብዙሃኑ ግን በዚያች እለት በቤተልሔም የተወለደው በቃ አንድ “ተራ ሕፃን” ነበር፡፡ ያን ያህል በጣም “ከተከበረ የነገሥታት ዘር” ሳይሆን ከ “ተራ” ሕዝብ ከሚመደቡ ቤተሰብ፤ በጣም በሚያምር ሥፍራ ሳይሆን በከብቶች በረት ውስጥ ተወልዶ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎ የሚገኝ አንድ ሕፃን፡፡ በቃ!

 

በዚያ የመጀመሪያ ልደቱ ሰሞን ግን ከዚህ በተለየ መንገድ ያዩት የሩቅ ሰዎች እንደነበሩ ወንጌላት ይነግሩናል፡፡ ልብ በሉ ሕፃኑ ገና ምንም ታምር መስራት አልጀመረም፤ ስለ ራሱም የእወቁኝ አዋጅ ማወጅ አልጀመረም፤ ዝም ብሎ በወላጆቹ እቅፍ ያለ ሕፃን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከሩቅ አገር መጣን የሚሉ ጠቢባን “ንጉሥ ተወልዷል” እያሉ ይፈልጉታል፡፡ ከእናቱ ከማሪያም ጋር ሲያገኙትም ወድቀው ሰግደው፣ የከበሩ የንጉሥ “እጅ መንሻ” አበርክተው በደስታ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡

 

የዚያች ሰሞን ትእይንት በዚህ አያበቃም፡፡ “በሜዳ ከብት ስንጠብቅ ያደርን እረኞች ነን” የሚሉ በድንገት ደግሞ ለማየት ከተፍ አሉ፡፡ በታላቅ ደስታ ገብተው “ይህ እኮ መድኃኒት የሆነ ክርስቶስ ጌታ ነው” እያሉ ይደሰታሉ፡፡ በሰፈሩ እየዞሩም ይህንኑ ማወጅ ጀመሩ፡፡ ምን አይነት የተለየ እይታ ነው!

 

ሌላም አለ፡፡ የጥቂት ወር ጨቅላ እንደ ሥርዓታቸው ለእግዚአብሔር ሊቀድሱትና መስዋዕት ሊያቀርቡ ወላጆቹ ወደ ቤተ መቅደስ ሲወስዱት ያን እለት የነበረው ተረኛ ካህንም ለየት ያለ ሽማግሌ ነበር፡፡ ወላጆቹም ሕጻኑም ምንም ሳይናገሩ እርሱ በምስጋናና በደስታ ተሞልቶ “ይህ ሕጻን እኮ ተራ አይደለም” የሚለውን አድራቆት ያዥጎደጉደው ጀመር፡፡ “ከዚህ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝ” በሚል አይነት ስሜት አቅፎት፡- “ይህ ሕፃን እግዚአብሔር ያዘጋጀው የመዳን መንገድ፣ ለአሕዛብ ሁሉን የሚገለጥ ብርሃን፤ የእስራኤል ክብር” እያለ ሲያሞጋግሰው ወላጆቹ እጅግ ተገረሙ፡፡

 

በቃ አንዲት የሰማኒያ አራት አመት ለየት ያለች ሴት ያለችውን ነግሬያችሁ ባበቃ ይሻላል፡፡ መቅደስ አካባቢ የማትጠፋ ትጉህ ነቢይት ስለ ነበረች ሕጻኑ ወደ ቤተ መቅደስ በመጣበት አጋጣሚ ተጠግታ አየችና የእስራኤል ታዳጊ መሆኑን እየዞረች ታውጅ ጀመር፡፡

 

እነኝህ እኮ ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ ታሪኮች ናቸው፡፡ አንድን በወላጅ እቅፍ ያለ ሕጻን እንዲህ ባለ መንገድ ማየታቸው አስደናቂ ነው፡፡ ሕጻኑ አድጎ፣ ብዙ ተአምራት አድርጎ፣ አስደናቂ ትምህርቶችን አስተምሮ፣ ስለ ሰዎች ኃጢአት ሞቶ፣ በሦስተኛው ቀን ተነስቶ ሲገለጥ እንዲህ ያልተረዱት ብዙዎች ናቸው፡፡

 

ወንጌላት እንደሚነግሩን እነኛ የመጀመሪያው ልደት ሰዎች የተለየ “የገና ስጦታ” ከሰማይ የተበረከተላቸው ነበሩ፡፡ በስጋ ዓይን ሳይሆን በመንፈስ ዓይን ያዩ ናቸው፡፡ ጠቢባኑን በከዋክብት፤ እረኞችን በሰማይ ሠራዊት፤ ስምዖንንና ነቢይት ሐናን በመንፈስ ቅዱስ መገለጥን እግዚአብሔር ሰጥቷቸው ነበር፡፡

 

እንግዲያውስ ከስጦታዎች ሁሉ ይልቅ ትልቁ የገና ስጦታ የልደቱን ጌታ በማንነቱ የምንረዳበት ልዩ ዓይን ቢሆንልን ይሻላል፡፡ “እኔ ማን እንደሆንኩ ትላላችሁ” ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ እንድንሰጥ የሚረዳ ልዩ ዓይን፡፡

 

ጌታ ሆይ የምናምነው በደንብ እንድናውቅህ፤ የማያምኑ ክብርህን እንዲያዩ ይህንን ዓይን ስጠን!

Seen 10159 times Last modified on Wednesday, 24 December 2014 14:45
Dr. Mamusha Fenta

Mamusha Fenta is a Bible expositor and conference speaker residing in Addis Ababa, Ethiopia.

Studied at

Website: mamushafenta.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 71 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.