You are here: HomeSocial Issues ረጅሙ ጸጥታ

ረጅሙ ጸጥታ

Written by  Wednesday, 08 April 2015 00:00

በቀኑ መጨረሻ በቢሊዮን የሚቈጠሩ ሰዎች በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ባለው መስክ ላይ ተሰባሰቡ። በርካቶች ፊት ለፊታቸው ካለው ደማቅ ብርሃን ወደ ኋላ ሸሽተዋል። ፊት አካባቢ ካሉ ቡድኖች ጥቂቶቹ ግን የተጋጋለ ንግግር ላይ ናቸው - በሀፍረት መሸማቀቅ ሳይሆን፣ ጠብ ፈላጊነት ይታይባቸዋል።

 

“እግዚአብሔር እንዴት እኛን ሊዳኘን ይችላል? ስለ መከራ ምን ያውቅና?” ስትል በቊጣ ተናገረች፣ ጠቈር ያለ ጠጕር ያላት አንዲት ወጣት። በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ሳለች ክንዷ ላይ የተነቀሰባትን ቊጥር ገልጣ ለማሳየት የልብሷን እጅጌ ተርትራ ገለጠችው። “ስንት ሽብር … ግርፊያ … ሥቃይ … ሞት … በላያችን ዐልፏል።”

 

ከሌላኛው ቡድን ደግሞ አንድ ጥቊር ወጣት ኮሌታውን ዝቅ አደረገ። “ይህስ ምን ሊባል ነው?” ሲል ጠየቀ፣ ዐንገቱ ላይ ያለውን የገመድ ጠባሳ እያሳየ። “ያለ ፍርድ በስቅላት የገደሉኝ ያለ በደሌ ነው፤ ጥቊርነቴ ወንጀል ሆኖ!”

 

ሌላኛው ስብስብ ዘንድ ደግሞ ኀዘንተኛ ዐይን ያላት አንዲት ነፍሰ ጡር ተማሪ አለች። “ጥፋቱ የእኔ አልነበረም፤ ተደፍሬ ነው” ስትል ዝቅ ባለ ድምፅ ተናገረች።

 

መስኩ ላይ እነዚህን መሳይ በብዙ መቶዎች የሚቈጠሩ ቡድኖች ነበሩ። በፈጠረው ዓለም ላይ እኩይን እና መከራን በመፍቀዱ እያንዳንዳቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅሬታ ነበራቸው። “ነገር ሁሉ ውብና ብሩህ በሆነበት፣ ልቅሶም ሆነ ፍርሀት፣ ራብም ሆነ ጥላቻ በሌለበት በመኖሩ እግዚአብሔር ምንኛ የታደለ ነው። ሰው በዚህ ምድር ላይ እንዲሸከም የተገደደው ስንትና ስንት ነገር ስለ መኖሩ እግዚአብሔር ምን ያውቃል? እግዚአብሔር በውበት በተጋረደ ስፍራ ነው የሚኖረው!” በማለት ተነጋገሩ።

 

ስለዚህ እነዚህ ቡድኖች እያንዳንዳቸው የሚወክላቸውን መሪ መረጡ፤ መስፈርቱ በመካከላቸው በከፋ ሁኔታ የተሠቃየ መሆን ነበር። አይሁዳዊ፣ ጥቊር፣ ከሄሮሽማ የመጣ ሰው፣ አካል ጕዳተኛ፣ ገና በማሕፀን ሳለ በመርዛማ ንጥረ ነገሮች ጥቃት የደረሰበት ሕፃን። የተመረጡት መሪዎች መስኩ መኻል የእርስ በርስ ምክክር ሲያደርጉ ቆዩና በመጨረሻ ጕዳያቸውን ለማቅረብ ዝግጁ ሆኑ። ክሳቸውን በጥሩ ሁኔታ ነበር ያዘጋጁት።

 

እግዚአብሔር እነርሱን ለመዳኘት ብቁ ከመሆኑ በፊት እነርሱ ባለፉበት መንገድ ማለፍ አለበት። ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ ምድር ወርዶ፣ ሰው ሆኖ እንዲኖር ወሰኑ!

 

“አይሁዳዊም መሆን አለበት። የአወላለዱ ተቀባይነትም አወዛጋቢ ይሁን። በአስቸጋሪ ሥራ ላይም ይሰማራ፤ ከሥራው አስቸጋሪነት የተነሣም ለመሥራት ሲሞክር ቤተ ሰቡ እንኳ እንዳበደ ይቊጠሩት። በቅርብ ወዳጆቹ መከዳት ይድረስበት። በሐሰት ይከሰስ፤ ቅድመ ግንዛቤ በያዙ የፍርድ ሸንጎ አባላት ተዳኝቶ፣ ፈሪ ዳኛ ይፍረድበት። ይገረፍ።

 

“በመጨረሻም፣ በሚያስፈራ ሁኔታ ለብቻ መቅረትን ይቅመሰው። ከዚያም ይሙት፤ መሞቱ በማያጠራጥር ሁኔታ በይፋ የሞት ሞት ይሙት። ይህን የሚያረጋግጡ በርካታ የዐይን ምስክሮች ይኑሩ።”

 

እያንዳንዱ መሪ በፍርዱ ላይ የየራሱን የውሳኔ ድርሻ ሲያቀርብ በአካባቢው ከነበረው የሕዝብ ክምችት ጎላ ብሎ የሚያስገመግም የስምምነት ድምፅ ይደመጥ ነበር።

 

የመጨረሻው ሰው የፍርድ ውሳኔውን ማሰማት ሲያገባድድ ረጅም ጸጥታ ሆነ። ማንም ቃል አልተነፈሰም። አንድም ሰው አልተንቀሳቀሰም። እግዚአብሔር ፍርዱ ቀድሞውኑ እንደ ተፈጸመበት ሁሉም ዐወቁ።

ተርጓሚ፡- ጳውሎስ ፈቃዱ

Seen 6126 times Last modified on Wednesday, 08 April 2015 10:21
Paulos Fekadu

ጳውሎስ ፈቃዱ ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፣ በሞያው መምህር ነው። በነገረ መለኮት እና በኮምፒውተር ሳይንስ፣ ከኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት (EGST) እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪዎች ያሉት ጳውሎስ፣ እግዚአብሔርን በአእምሮውም ለመውደድ የሚሻ አማኝ ተደርጎ ቢወሰድ ይመርጣል።

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 120 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.