You are here: HomeSocial Issues ዛሬም፣ ኢትዮጵያችን ፈጥና እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች?

ዛሬም፣ ኢትዮጵያችን ፈጥና እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች?

Written by  Tuesday, 21 April 2015 00:00

እናተዬ ኢትዮጵያውያን ወንድሞችንና እህቶቻችን ትላንት ለነጻነታቸው ደፋ ቀን ሲሉለት በነበረ ሕዝብ (ጥቂት ወሮበሎች) ንብረታቸውን ተገፈፉ ቢባል ማን ያምናል? ሐገር ወገን እንደ ሌለው ሰው ባደባባይ ተወገሩስ ቢባል? አሮጌ የመኪና ጎማ አስነግተው እንደ ጧፍ አነደዷቸው ቢባልስ? የኢትዮጵያዊ ደም በደቡብ አፍሪካ ጎዳናዎች በአንድነት ፈሰሰ ቢባል ማን ያምናል?

 

ታዲያ ዛሬ የአጥንታችን ፍንካች የደማችን ቅጅ የሆኑ ወንድሞቻችን፣ ዓለም እያየ አንገታቸውን ተቀሉ፣ መሮጫ ማምለጫ እንደ ሌለው፣ ሐገር ወገን እንደ ሌለው ሰው፣ በጥይት ተቆሉ ሲባል ልባችን ቢሰበር፣ አንገታችን ቢደፋ፣ ተስፋችን ቢሟጠጥ ያንሰን ይሆን? ድፍን ኢትዮጵያ ማቅ ለብሰ አደባባይ ወጣች ቢባልስ ማን ይፈርድ ይሆን? የወላድ አንጀት በእቅፏ ስሌሉ ልጆችዋ ተላወሰ፣ እንቅልፍ ካይኗ ጠፋ…አይኗም ከእንባ ብዛት ጠፋ፣ አምላክን «ወይ ውረድ ወይ ፍረድ» አለችው ቢባል ማን ይፈርዳል? አባት እጁን ጨብጦ በጸጸት ደም ስሩ ተገታሮ ጭብጥ እጁን ወደ አምላኩ አነሳ ቢባል ማን ይፈርዳል?

 

በየመን ጎዳና ላይ የሐገሬ ልጆች ለነፍሳቸው ሮጡ፡፡ የአገሬ ልጆች እንደ እባብ ራሳቸውን ተቀጠቀጡ፡፡ ከፎቅ ተፈጠፈጡ፡፡ ተገደው ተደፈሩ ፡፡ ከሰማይ፣ ከምድር፣ ከሓገር ውስጥ ከሐገር ውጭ እርዳታን ተማጠኑ ቢባልስ?


አምላክስ ይሄን እያየ ምን ይል ይሆን?


አምላክ ወደ እርድ እንደሚንደሚነዳ በግ ዝም ማለትን ያውቃል(ኢሳ. 53፡7)፡፡ አምላክ ቀይ ግምጃ መልበስን፣ «እማዬ አድኚኝ፣ አባቴ አድነኝ» ማለት አለመቻልን ያውቃል(ማቴ.27፡46)፡፡ አምላካችን «ይግባኝ የሌለው ፍርድ» ምን እንደሚመስል ያውቃል(ማቴ.26፡65-68)፡፡ አምላካችን እንደ ምድር ጨው በዓለም ዳርቻ መበተን ምን ማለት እንደ ሆነ ያውቃል(ዘጸ.2፡23-22)፡፡ ማወቅ ብቻም አይደለም አብሮን ያለቅሳል፡፡ አብሮን ማልቀስ ብቻ አይደለም፤ እንደ ጠፋው ልጅ ወደ እቅፉ እንድንመለስ ምስማር በሸነቆሩት እግሮቹ ቆሞ፣ ጦር ወደ ተሰካበት ጎኑ እያመለከተ በፍቅር በተዘረጉ ችንካር ያረፈባቸውን እጆቹን ዘርግቶ (ዮሐ. 20፡24-29፤ ኢሳ 53፡5) «መከራችሁን አውቃለሁ» ይለናል፡፡ እናንት ሐዘናችሁ የጠና ፣ ልባችሁ የተሰበረ ትከሱ፣ ታመሰግኑት የጣችሁ ሰዎች ኑ ወደ እኔ ይላል፡፡

 

እሱ ብቻ አይደለም ኢትዮጵያችንም ታለቅሳለች፡፡ ጥቁር ፣ጠይም ፣ ቀይ…ቆንጆ፣ ፉንጋ ፣ጎራዳ…አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ…. አውራ ፓርቲ፣ ግልገል ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ደጋፊ…ክርስቲያን ፣ እስላም፣ ጴንጤ፣ ካቶሊክ፣ ከሐዲ እምነት የለሽ ሁሉ ያዝናል ፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉ ታዝናለች፡፡ ኢትዮጵያ በባዕድ ሐገር ተበትነው ስላሉ ልጆቿ ታዝናለች፡፡ ነገ ይበተናሉ ብላ ስለምትሰጋባቸው እጉያዋ ስላሉ ልጆቿም ታነባለች፡፡

 

ኢትዮጵያች ግን አዝና አትቀርም፡፡ ኢትዮጵያችን ውዷ እንደናፈቃት ወጣት እጆቿን ወደ ጎን ዘርግታ ትበራለች፡፡ ምን ቢሰምር፣ ምን ቢከሽፍ፣ ምን ቢስፋፋ ፣ ምን ቢለማ ፣ የዚህ ዘመን መፍትሄ «ስም ከማውጣት»፣ በዓል ከማክበር እንደማይዘል አውቃ፡፡ ኢትዮጵያችን ልጆቿ በአዳፋ ቀሚሷ ሽሽጋ ፣ በደማቸው ፍሳሽ ጨቅይታ፣ በሥጋቸው ሽታ ጠልሽታ ፣ በእንባቸው ብዛት እርሳ ፣ ኢትዮጵያችን እጆቿ ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡ ከዚያም ትሮጣለች… ትበራለች…

Seen 3592 times
Abinet Ababu

I am Abinet Ababu a disciple, a husband and a father of two. A graduate of for Evangelical Theological college (ETC) in Bible Translation and Literacy. A student at at Africa Nazarene University (Nairobi, Kenya). A Bible school teacher, speaker and writer. An Interpreter by trade (to Amharic,English to Ormiffa -pending). 

Website: abinetababu.wordpress.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 198 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.