You are here: HomeSocial Issues ስለጊዜ በጊዜ

ስለጊዜ በጊዜ

Written by  Thursday, 25 June 2015 00:00

በዘመናችን በአብዛኛው ሰው የእጅ ሰአት፣ ተንቀሳቃሽ ስልክና የመሳሰሉትን ጊዜ ጠቋሚ መሣሪያዎች ይጠቀማል፡፡ በእለታዊ እንቅስቃሴያችን አዘውትረን የምንሰማቸው እንደ “ጊዜ የለኝም፣ ጊዜህን አታባክን፣ ጊዜያችንን በአግባቡ እንጠቀም” የመሳሰሉ አባባሎች ሰዎችና ጊዜ ቢያንስ በዚህ ምድር ላይፋቱ መቆራኘታቸውን ያሳዩናል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሐረጋት በየንግግሮቻችን መኻል ቢደመጡም በአገራችን ለጊዜ የሰጠነው ዋጋ አነስተኛ ለመሆኑ “ጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ ካልቀረበልኝ አላምንም” የሚያሰኝ አይደለም፤ ይልቁን ለሁሉ ግልጥ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ የምዕራቡን ዓለም የጊዜ ምልከታ እንደ ጥሩ ማሳያ በመውሰድና የጊዜ አጠቃቀም ባህላችንን በማሳደግ ፍሬያማ መሆን እንችላለን ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ በእርግጥ እኛ ለጊዜ ያለን መረዳትና ለጊዜ አጠቃቀም የምንሰጠው ዋጋ ከምዕራባውያን ጋር ሲነፃፀር አጠገባቸውም አንደርስ፡፡ ነገር ግን ምሳሌ ልናደርጋቸው የምንመኛቸው ምዕራባውያን የጊዜ አጠቃቀም ላይ መገታት ግዴታ ይሆንን? ከዚያ የተሻለ የጊዜ አጠቃቀም ሊኖረን አይችልም? ይችላል!!! ቀጣዩ ጥያቄ ለምንና እንዴት የሚል ይሆናል፡፡ ስለዚህ በመቀጠል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሀሳቦች ላይ በመመሥረት ከጊዜና በጊዜ ውስጥ ከፍተኛውን ትርፍ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድና ምክንያቱን በጥምረት ለማየት እንሞክር፡፡ ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሰው ʽጊዜʼ ቁሳዊውን (physical) ይወክላል፡፡

 

ጊዜ እንቅስቃሴ

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ጊዜን የሚገልፁ ቃላት ከ700 ጊዜ በላይ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ ይህ ምናልባት ዕብራውያኑ ለቦታ ከስጡት የቅድስና ይልቅ ለጊዜ ቅድስና ከፍ ያለ ደረጃ ሰጥተው ይሆናል ብለን እንድንገምት ያደርገን ይሆን? ግምቱ መሠረት የለሽ አይሆንም፤ ምክንያቱም የስፍራና የጊዜ ቅዱስ መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ከቅዱስ ቦታ ጋር ተያይዞ ቤተ መቅደሱ መጠቀስ የሚችል ሲሆን፤ ዓመታዊና ሌሎችም በኣላትን በማንሳት የተቀደሰ ጊዜ መኖሩን ማሳየት ይቻላል፡፡

 

ዓመታዊና ሌሎችም በዙር የሚመጡ “ቅዱስ” ጊዜያት ጊዜ እሽክርክሪታዊ እንዲመስለን ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፡፡ እውነቱ ግን ጊዜ እሽክርክሪት ጠብቆ ተመላሽ ሳይሆን ወደፊት ያለማቋረጥ በማይለዋወጥ ፍጥነት ተጓዥ መሆኑ ነው፡፡ በዘፍ 1 ከተዘረዘሩልን ፍጥረታት መካከል የመጀመሪያውን በቁጥር 3 የምናገኝ ሲሆን እርሱም ብርሀን ነው፡፡ የብርሀን መፈጠር ከጊዜ ጋር ያለው ግንኙነት የጊዜ መቁጠሪያ ሆኖ ማገልገሉ ሲሆን፣ ቁ 5 ላይ ይህ በግልፅ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት (በአጠቃላይ 6) የፍጥረት ቀናት ሁሉ ቀናቱ ወደፊት ይቆጥሩና ይቆጠሩ ነበር እንጂ በዙረት የተመለሰ ጊዜ አልነበረም፤ ከዚህ የተለየ ምልከታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ጊዜ ትርጉም በተሞላ መልኩ ወደፊት ተጎዥ ለመሆኑ የትንቢቶች ፍፃሜ መጠቀስ የሚችል ሲሆን፤ የኢየሱስ ልደት (ገላትያ 4፡4-5)፣ መስዋዕትነት (ሮሜ 5፡6) እና ዳግም ምፅአት (ማር 13፡32) በተወሰነው ጊዜ ሙላታቸውን ማግኘታቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ጊዜ ራሱን የሚደግም ስላይደለ ወይም እንደ ሀገራችን አባባል ጊዜ እንደ ታክሲ ቆሞ ስለማይጠብቅ ጊዜን በጊዜ መጠቀም ያሻል፡፡

 

የጊዜ ሁኔታ

የሰው ልጅ በኃጢአት መውደቁን ተከትሎ ሌሎች ፍጥረታት የኃጢአት ተፅእኖ እንደደረሰባቸው ሁሉ ጊዜም የኃጢአት ሰለባና ትድግና ፈላጊ ሆኖአል (ኤፌ 5÷16፤ ቆላ 4÷5)፡፡ ከዚህ የምንረዳው ጊዜ ለብክለት የተጋለጠ መሆኑን ሲሆን፤ በኃጢአት ባርነት ውስጥ ያለ ሰው ደግሞ ለችግሩ መባባስ ሚናው ቀላል አለመሆኑን ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት ችግሮች፣ ማለትም የሰው ኃጢአተኝነት እና የጊዜ በኃጢአት መበከል፣ የጊዜ አጠቃቀምን ብዙ ጥበብ ፈላጊ ያደርገዋልና፤ ጊዜ ጠቅለል ባለ መልኩ ከፍጥረት ጋር ያለውን ግንኙነት እንይ፡፡

 

የፍጥረትና የፍጡርነት ዓላማ

የሰው በኃጢአት መውደቅ በሰው ላይ ካስከተለው የእውቀት መዛባት መካከል አንዱ የፍጥረትና የፍጡርነት ዓላማን መሳት ነውና በቅድሚያ የፍጥረትን ዓላማ በደምሳሳው እንመልከት፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጠረበትን ዋነኛውን ምክንያት ለማየት ስንሞክር እንደሚታወቀው ፍጥረት ሁሉ የመፈጠሩ ዋነኛው ዓላማ በአንድም በሌላም መንገድ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሆን፣ እንዲሰራና እንዲያገለግል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በኢሳይያስ 43÷7 እግዚአብሔር ሁሉን ለክብሬ ፈጥሬአለሁና ሁሉ ይሰብሰብልኝ ይላል፡፡ ቀጠል አድርጎም በቁጥር 21 ላይ ይህ ክብር የሚመጣው ምስጋና በመስጠትና ምስጋና የመስጫ ምክንያት በመሆን መሆኑን እንስሳትንም በመጥቀስ ይበልጥ ያብራራል፡፡ በተጨማሪም 48÷11 እግዚአብሔር ራሱ ክብሩን ለሌላ ለማንም አሳልፎ እንደማይሰጥና እንደማያጋራው ይናገራል፡፡ በሮሜ 9÷23 ሐዋርያው ጰውሎስ እግዚአብሔር ሁሉን አስቀድሞ ያዘጋጀው የክብሩ ባለጠግነት ይታወቅ ዘንድ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ከዚህ በመነሳት እግዚአብሔር ሁሉን ያደረገው፣ በማድረግ ላይ ያለውና ለወደፊትም ቢሆን የሚያደርገው በዋናነት ለእርሱ ክብር እንዲያገለግል መሆኑን መረዳት ይቻላል፤ ይህም ፍጥረትን ሁሉ የሚያካትት ይሆናል፡፡ የፍጥረትን ስፋትና ግዝፈት የሰብዕ ውስን አእምሮ ሊረዳው የሚችል ባይሆንም እያንዳንዱ ፍጥረት የመፈጠሩ ዓላማ እንዳለው አያጠራጥርም፡፡ ይህ ሲባል ግን ጊዜን ጨምሮ እያንዳንዱ የፍጥረት ክፍል በፍጥረት ስርአት ውስጥ የተለየ ድርሻ እንዳለው ሊዘነጋ አይገባም፡፡

 

በፍጥረት ውስጥ የጊዜ ድርሻ

እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት ፍጥረታት በዋናነት ቁስ አካላት ናቸውና፣ በቀጣይነት በቁስ አካላትና በጊዜ መካከል ያለውን ግንኙነት እንይ፡፡ ያለ ጊዜ እና ያለ ስፍራ ቁስ አካልም ሆነ ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ ህልውና የለሽና ቀጣይነት አልባ ይሆናሉና እግዚአብሔር ከቁስ አካል (ምናልባትም ከሰማያዊ ፍጥረታትም) በፊት ጊዜን ፈጠረ፡፡ (ይህን ሁሉ ያደረገው እግዚአብሔር በጊዜ ውስጥ ሳይወሰን ነው መዝ. 90:4 ኢሳ. 40:28፡፡) ለዚህም ነው ይህ ጽሑፍ ሲጀምር ቢያንስ በዚህ ምድር ስንኖር ቀጣይነት ይኖረን ዘንድ ከጊዜ ጋር ሳንፋታ መኖራችን የተመለከተው፡፡

 

ነገር ግን ለቀጣይነት በጊዜ ውስጥ የመወሰናችን እውነት ለጊዜ የምንሰጠውን ምልከታ ከተገቢው በላይ ሊያደርግብን አይገባም፡፡ ምንም እንኳን ሁላችን በጊዜ ውስጥ ያለንና ከዚህ መውጣት የማንችል ቢሆንም፤ ጊዜ የፍጥረት ስርአትን በተመለከተ ፍፁም ተቆጣጣሪ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜ ራሱ በፈጣሪው ቁጥጥር ስር ነውና፡፡ እግዚአብሔር የጊዜ ገዢና ተቆጣጣሪ ነው ሲባል ምን ማለት ይሆን? በጊዜና በክስተቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ “ጊዜ ያመጣውን ጊዜ ይመልሰዋል” ይባላል፡፡ እውነት ነው መልካምም ሆኑ ክፉ ክስተቶችና ሁነቶች በጊዜ ውስጥ ብቻ እውነታ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን በድጋሚ የምንጠይቀው ጥያቄ በጊዜ ውስጥ የመጣውን ጊዜ አመጣውን? የሚል ይሆናል፡፡ መልሱ በጭራሽ የሚል ይሆናል! አንድም ነገር፣ ደግሜ እላለሁ አንድም ነገር ጥቃቅን የሚመስሉትን ጨምሮ የጊዜ ውጤት ሳይሆኑ በጊዜ ውስጥ የመጡ ብቻ ናቸው፡፡ የሚመጡና የሚሄዱ እንዲሁም “የሚፀኑ” እውነታዎች ሁሉ በጊዜ ውስጥ በጊዜ ገዢና ተቆጣጣሪ የተወሰኑና የሚደረጉ ናቸው፡፡ በሐዋ ሥራ 17÷26 የሰውን ወገኖች በተመለከተ ሲናገር ለሁሉም የሚኖሩበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን ጊዜያቸውም (ዘመኖች) በቅድሚያ የተወሰነ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህም በጊዜ ውስጥ የተወሰነውን የሚያመጣ እግዚአብሔር እንጂ ጊዜ ራሱ ላለመሆኑ ማስረጃ ነው፡፡

 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጊዜ ሰፊና አጠቃላይ አስተምህሮ መስጠት መቻሉና አለመቻሉ አከራካሪ ሊሆን ቢችልም፤ እግዚአብሔር ወጥነትን በተላበሰ መልኩ የታሪክን ሂደት እንደራሱ ሀሳብ መምራቱ ግልፅ ነው፡፡ በእግዚአብሔር የተጀመረውና የተፈጠረው ጊዜ በእርሱ ቁጥጥር ስር ይኖራል፡፡ ለቁስ አካል ቀጣይነት ጊዜ አስፈላጊ ሲሆን ለጊዜ ቀጣይነት እግዚአብሔር አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ በፍጥረት አጠቃላይ ዓላማ ውስጥ የጊዜ ድርሻ ቀጣይነቱን ከእግዚአብሔር በማግኘት ለፍጥረት ቀጣይነትን መስጠት ሲሆን፤ እግዚአብሔር ጊዜን ሌሎች ፍጥረታትን ለማስቀጠያነት ይመቀመዋል ማለት ነው፡፡ ይህም ጊዜ በዋናነት ፈጣሪውን በማስከተል ደግሞ በመልኩ የተፈጠረውን ሰውን ያገለግላል ለማለት ያስችላል፡፡

 

የጊዜአችን የጊዜ አጠቃቀም

ጥቂቶች ብቻ ጊዜን ከተፈጠረለት ዓላማ ጋር በሚስማማ መልኩ ሲጠቀሙት፣ ብዙዎች የጊዜ መጠቀሚያ ሆነዋል፡፡ አንዳንዶች ለሥጋቸውም ሆነ ለአእምሮአቸው እረፍት በመንሳት በከፍተኛ የሥራ ውጥረት ውስጥ ሲባክኑ፤ በአንፃሩ ሌሎች በታካችነት ኃጢአት በጊዜ ብክነት ይባክናሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ጊዜን በሚገባ መጠቀም በሚለው የተቃና አመለካከት ነገር ግን በተሳሰተ ዝምደት (application) ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከተዛባ ዝምደት ውስጥ ለምሳሌ ያክል ለሌሎች ሰዎች ማለትም ለቤተሰብና ጓደኞች እንዲሁም ማኅበራዊ ግንኙነቶች የአብሮነት ቆይታ አለመስጠትና አልፎ ተርፎም ጊዜ ማባከን አድርጎ መቁጠር መጠቀስ ይችላሉ፡፡ የዚህ አይነት ዝንባሌ በተወሰነ ደረጃ ትዕቢት ያለበትም ይመስላል፣ ምክንያቱም በውስጠ ታዋቂነት የእንደዚህ ዓይነት ሰዎች አስተሳሰብ በህይወቴ ውስጥ እነዚህ ግንኙነቶች አያስፈልጉኝም ለራሴ ራሴ በቃለሁ ማለትን የያዘ ነውና፡፡ እግዚአብሔር ሲፈጥረን ማኅበራዊ ማንነትንም ጨምሮ በኛ ውስጥ አኑሮአልና የእግዚአብሔርን የፍጥረት ስርአት አለማዛባቱ ይመረጣል፡፡ የዚህ ዝንባሌ መገለጫው ትእቢት ብቻ ሳይሆን ራስ ወዳድነትን ይጨምራል፡፡ ለሙግት ያክል የሌሎች ድጋፍ አያስፈልገኝም ልበልና፤ የእኔ እርዳታና አብሮነት የሚያስፈልጋቸው አይኖሩ ይሆን? አሉ በሚለው ከተስማማን ይህን የሰዎችን አስፈልጎት መንፈግ ራስ ወዳድነት መሆኑም ላይ መስማማት ይኖርብናል፡፡ ለነገሩ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው እንጂ ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም፡፡ ምክንያቱም ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ውስጥ ሌሎች አሉበትና፡፡

 

ሌሎቹ ደግሞ (አብዛኞቻችን በዚህ ምድብ ውስጥ ሳንገኝ አንቀርም) የታካችነት በሽታ ይዞን ይመስላል፣ ነግቶ ይመሽብናል መሽቶ ይነጋብናል፡፡ ይህ ሕይወት በእግዚአብሔር መልክ ከመፈጠራችን ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ እግዚአብሔር ሠራተኛና ትጉ አምላክ ነውና ታካችነት ከኛ ይራቅ፡፡ ጊዜ ፍጡር መሆኑን ካወቅን የጊዜ መጠቀሚያ ሳይሆን ተጠቃሚ መሆን ያሻል፡፡

 

መደምደሚያ

ፍጥረት ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር የተፈጠረ ሲሆን፤ በመልኩ የተፈጠረው የሰው ልጅ ደግሞ የሚያደርገውን ሁሉ የሚያደርገው በጊዜ ውስጥ ስለሆነ ሁሉን ነገር በፈቃድ ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ አለበት፡፡ ያለማቆረጥ ወደፊት ብቻ በመጓዝ ላይ የሚገኘውን ጊዜን ለእግዚአብሔር ክብር መጠቀም የተዋጀ የቅዱሳን አእምሮ የጥበብ ውጤት ሲሆን፤ ጊዜን ካለበት የኃጢአት ብክለት ባለፈ መልኩ መጠቀም ትልቁ የሰው ልጅ ትርፍ ነው፡፡ ከጊዜ ውጪ የሆነው እግዚአብሔር ነውና እርሱ ብቻ ጊዜ አያልፍበትም፤ በጊዜ ውስጥ ያለ ስብእና ሁሉ አላፊ ነውና በጊዜ እግዚአብሔርን ሳናከብር ጊዜ አይለፍብን፡፡

Seen 8254 times
Gedion Agezew

Website: gedi2004agzew@gmail.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 163 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.