You are here: HomeTheologyመስቀሉን ሰቀሉት

መስቀሉን ሰቀሉት

Written by  Wednesday, 07 May 2014 00:00

ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የዓለም መድኀኒት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ (ማር. 15፥24፤ ዮሐ. 19፥18) ደሙን በማፍሰሱ ምክንያት፣ “በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኝተናል፤ እርሱም የበደላችን ስርየት” (ኤፌ. 1፥7) ነው። “ደም ሳይፈስ ስርየት የለም”ና (ዕብ. 9፥22)። ስለዚህ ክርስቶስ ደሙን ሰጠ። ዐዲሱ ኪዳን ተመርቆ በተከፈተበትና (ዕብ. 9፥15፡18) የኀጢአታችን ማስተሰረያ ይኾን ዘንድ በመስቀል ላይ በፈሰሰው ንጹሕ ደሙ (ቆላ. 1፥19) አማካይነት ታጥበን (ራእ. 1፥5) በመንጻት ወደ እግዚአብሔር መግባት ኾኖልናል (ሮሜ. 5፥2፤ ኤፌ. 2፥18፤ ዕብ. 10፥19-20)። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን።

 

እንግዲህ ይህን እውን ለማድረግ መድኅኑ ስለ ኀጢአታችን የሞተው በእንጨት ላይ ነበር። “ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” (1ጴጥ. 2፥24)። ይህ የመስቀል ላይ ሞቱ የመከራና የህማም ጣር የተሞላ ነበር። አዳኙ ጌታ በፈቃዱ ለአባቱ በመታዘዝ እንደ ሎሌ ነበር የኖረውና ያገለገለው (ፊል. 2፥6-9)። ሊያውም የህማም ጣርና ሥቃይ ያልተለየው ሎሌ። በመጨረሻም፣ ሥቅዩው ሎሌ ድኅነትን ያስገኝልን ዘንድ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ።

 

ከዚህም የተነሣ፣ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ሁለት ሺ ዓመታት መስቀሉን ማእከል ያደረገውን ወንጌል ስታበሥር ኖራለች፤ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1ቆሮ. 1፥23) እያለች። የመንግሥቱ ወንጌል ቤዝዎታዊ እውነቱ የሚታየው ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በኩል ነውና። ያልተዋጁ መንግሥቱን አያዩም።

 

በአንጻሩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ውጭ በኾነ ትምህርትና ኑሮ የመስቀሉን መልእክት አዛብታ የተገኘችበት ወቅትም ነበረ፤ ዛሬም አለ። ከእነዚህ ግድፈቶች መካከል አንደኛውን ማለትም ከሥቅዩው ሎሌ ይልቅ ማሠቃያውን፣ የመከራው ተካፋይነት ከሚገለጥበት የመስቀል ኑሮ ይልቅ ምልክታዊ ጌጥነቱን ማስቀደማችንን እንዲሁም መስቀሉን ማእከል ካደረገው ትምህርት ይልቅ ቅምጥልነትን የሚያስፋፋውን “ዘመነኛውን ወንጌል” ማስቀደማችንን በማንሣት እንታረምበት ዘንድ ዐጭር ሐሳብ አስፍሬአለሁ። ይህን ሐሳብ በቅንነትና በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ስር ኾነን እንድናነብም እማጠናለሁ።

 

ለመኾኑ መስቀል ምንድነው? የምልክቱ ፋይዳስ ምንድነው? እንግዲያስ ስለ ነገረ መስቀሉ ትንሽ ማየት ያስፈልግ ይመስለናል— ምልክትነቱና ክብሩ የሚገባን ያን ጊዜ ነውና! ምልክቱ ከወከለው እውነት በላይ አይደለምና! የመስቀሉ በረከቶች ከመስቀሉ መከራ ተነጥለው አይገኙምና። ለመኾኑ መስቀል ለክርስትና እምነት ምኑ ነው?

 

ነገረ-መስቀሉ

ሰው በአምሳለ ሥላሴ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው። እግዚአብሔር በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮታልና (ዘፍ. 1፥26-28)። እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር በአጽናፈ ዓለሙ ካሉት ፍጥረታት በሙሉ የተለየና ክቡር አድርጎ ነው። ሁሉን በቃሉ ብቻ ሲፈጥር ሰውን “ከምድር አፈር አበጀው” (ዘፍ. 2፥7)። “በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” (ዘፍ.2፥7)።

 

“እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፥ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ.1፥27)። ያዘጋጀለት መኖሪያውም ያማረና የተሟላ የአትክልት ስፍራ ነበረ። “እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው” (ዘፍ. 2፥8)። በምድርና በባህር የሚኖሩትን በሰማይም የሚበሩትን እንዲገዛ እግዚአብሔር ለሰው ሥልጣን ሰጠው (ዘፍ. 1÷26-28)። ታላቁ አምላክ በማይነገር ጥበቡና ፍቅሩ ሰው በብርሃን የተሞላ የክብርና የጽድቅ ሕይወት ይጎናጸፍ ዘንድ ባለሟሉ አደረገው። ሊቁ ጎርጎርዮስ እንዳለው፣ “ምንትኑ ይከብር እም ዝንቱ ማዓረግ ወአይ ምክሕ የዐቢ እምኵሉ ትምክሕት… ወይኩን ስምዐ ከመ ውእቱ ገብሮ ለእጓለ እመሕያው በአርአያሁ ወበአምሳሊሁ።— ከዚህ ክብር የሚበልጥ ምን ክብር አለ? ከዚህስ ትምክሕት የሚበልጥ ምን የሚያስመካ ነገር አለ?...ሰውን በርሱ አምላክ እንደ ፈጠረው እንዲመሰክር ከመሆን የበለጠ ምን ትምክሕት አለ?” (ሃይማኖተ አበው፤ ዘጎርጎርዮስ ም. 36፣ ቊ. 12፣ ገጽ፣ 124)

 

ለሰው የተሰጠው ታላቁ በረከት ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት መኖሩ ነበር። የሕይወት ምንጭ ከኾነው አምላክ ጋር በሚኖር ኅብረት ብቻ ሕይወት በክብርና በብርሃን ትቀጥላለችና (መዝ. 36፥9፤ ዮሐ. 1፥4)። ይህን ለማረጋገጥም በመታዘዝ መኖር ይጠበቅበት ነበር። የመታዘዙ ምልክትም “ክፉና ደጉን ከሚያስታውቀው ዛፍ” አለመብላት ነበር። ከዚህ ዛፍ በበላ ቀን እንደሚሞት (ከእግዚአብሔር መለየትን የሚያካትተው መንፈሳዊ ሞትን ጨምሮ) እግዚአብሔር ለአዳም ነገረው (ዘፍ. 2፥15-17)።

 

ሰው የመረጠው የዐመፃ መንገድ ግን አስፈሪ ነበር። ከአምላኩ ይልቅ “እባቡ” የነገረውን በማመን እግዚአብሔርን “ሐሰተኛ” ለማድረግ ተጣደፈ። በራሱ ያለ እግዚአብሔር መኖር እንደሚቻለውና እንዲያውም “እንደ እግዚአብሔር” ለመኾን ተመኘ (ዘፍ. 3፥5)። አዳምና ሚስቱ ሔዋንም የተከለከለውን ዛፍ ፍሬ በመብላት በእግዚአብሔር ላይ የተገዳዳሪነት ዐመፅ ፈጸሙ (ዘፍ. 3፥1-6፤ 1ጢሞ. 2፥14)። በዚህም ምክንያት ኀጢአት ወደ ዓለም ገባ (ሮሜ 5፥12)። ውጤቱም ሞት፣ ኀዘን፣ ውርደትና ውድቀት ኾነ (ዘፍ. 3)። በመተላለፋችንና በኀጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለየን (ኤፌ. 2፥1-3)። አዳምና ሔዋን የሰው ዘር ሁሉ ወላጆች እንደ መኾናቸው፣ በሠሩት ኀጢአት ምክንያት ለመላው ልጆቻቸው ያወረሱት በኀጢአት የወደቀ ባሕርይን ነው (ሮሜ 5፥12-14፤ ኤፌ. 2፥3)። አባቶች “ጥንተ አብሶ” (የውርስ ኀጢአት) ብለው የሰየሙት የኀጢአት ተፈጥሮ ሁሉንም የተጠናወተው በመኾኑ፤ በኀልዮ፣ በነቢብ፣ በገቢር (በሐሳብ፣ በቃል፣ በሥራ) ኀጢአተኛ አደርጎን ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በአካል ክፍሎቻችን ሁሉ ይሠራ ነበር (ሮሜ 7፥5)። የኀጢአት ውጤቱ ደግሞ ሞት (ከእግዚአብሔር መለየት) በመኾኑ ከኵነኔ በታች ወድቀን ተከረቸምን (ሮሜ 6፥23)። እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ አምላክ በመኾኑ፣ ኀጢአታችን ከእርሱ ለይቶን ነበርና (ኢሳ. 59፥2)።

 

ነገር ግን ጨለማው እንደነበር እንዲቀጥል የመለኮት ዘላለማዊ ምክር አልፈቀደም። እግዚአብሔር በመቤዠት ጥበቡ የፈረሰውን ሊሠራው፣ የወደቀውን ሊያነሣው፣ የተበላሸውን ሊያድሰው ፍቅሩና ጥበቡ ቤዛችንን ገለጠው። የዚህ ሰማያዊ ድነት (ድኅነት) አጀንዳ መካከለኛው ደግሞ መስቀሉ (የክርስቶስ ቤዛዊ ሞት) ነበር። ከአብ ጋር በክብር የተካከለ ወልድ ወረደ፤ እስከ መስቀል ሞትም ድረስ ራሱን አዋረደ (ፊልጵ. 2፥5)። “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኀያል እመንበሩ፤ ወአብጽሖ እስከ ለሞት— ፍቅር፣ ኀያል ወልድን ከዙፋኑ ሳበው፤ እስከ ሞትም አደረሰው” እንዲል።

 

ጌታ ኢየሱስ ኀጢአታችንን ተሸክሞ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ (ማቴ. 27፥35፤ 1ጴጥ. 2፥24) ። የኀጢአታችንን ቅጣት ተቀበለ (ኢሳ. 53፥5-6)። ታላቁ እግዚአብሔር በመስቀል ላይ በሞተው በልጁ ሞት ምክንያት የእያንዳንዳችንን መከራ፣ ሞትና እርግማን አስወግዷል (ኢሳ. 53፥4፤ ገላ. 3፥13)። በዚህም አደራረጉ ጻድቅ ፈራጅነቱን አሳይቷል (ሮሜ. 3፥25-26)። እንዲሁም፣ አንድ ልጁን በመስጠት እግዚአብሔር ፍቅሩን በመስቀሉ ላይ ገለጠልን (ሮሜ. 5፥4)። ላመንን ለኛም ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ዐዲስ በር ተከፈተልን (ዕብ. 10፥19-20)። በመስቀሉ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ዐዲስ ኅብረት መሠረትን። በመስቀል ላይ በፈሰሰው በኢየሱስ ደም የኀጢአታችንን ስርየት ስለምንቀዳጅ (ቆላ. 1፥12-14፤ 1ዮሐ. 2፥1-2) በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተናል (2ቆሮ. 5፥21)። ስለኾነም፣ “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ” (መዝ. 85፥10) የሚለው እውነት በመስቀሉ ላይ ተፈጸመ።

 

እግዚአብሔር በጻድቅ ፈራጅነቱ በኀጢአታችን ላይ ከበየነው ፍርድ፣ በሩቅ ብእሲ ቤዛነት መዳን ስለማይቻለን፣ አንድያ ልጁን ሰጠ (ዮሐ. 3፥16)። ጌታ ኢየሱስም በፈቃዱ ሞተልን (ዕብ. 10፥9)። ይህ ተግባር ደግሞ የፍቅሩን ጥልቀት የሚያሳይ ነው (ሮሜ. 5፥4)። ትክክለኛ ፍርዱንና ፍቅሩን በአንድነት እውን ያደረገው ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። ከመታወቅ የሚያልፈው ይህ ድንቅ ጥበቡ ደግሞ በክርስቶስ የመስቀል ሞት ተገለጠ— ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል ነውና (1ቆሮ. 1፥23-24)! ስለዚህም “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።” (1ቆሮ.1፥18) ተባለ። ሎቱ ስብሐት ለዓለመ ዓለም፤ አሜን!

 

እንግዲያስ መስቀልን እንዴት እንረዳው?

አሁን ወደ ተነሣንበት ጥያቄ እንመለስ። መስቀል ምንድነው? የቃሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አጠቃቀም ስናይ፣ መስቀል በሦስት መንገድ ይተረጐማል። አንደኛው ሰው ለቅጣት ይሰቀልበት የነበረ ቀጥ ያለ ወይም የተመሳቀለ እንጨት ነው። ክርስቶስም የሞተው በእንጨት መስቀል ላይ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ የክርስቶስን ወጆአዊ ሥራ ትእምርታዊ ትክ (symbolic representation of redemption) የሚያሳይ ነው። በሦስተኛው ትርጓሜው ደግሞ ስቅለትን ራሱን (በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞትን) ያመለክታል 1።

 

እንግዲህ ቀደም ባሉት ገጾች ባጭሩ እንዳ’የን፣ መስቀል የታሪከ- ድኅነት መካከለኛ የኾነው የቤዛችን የክርስቶስን መከራና ሞት፣ ደሙን ማፍሰሱና በአጠቃላይም የቤዛነቱን ሥራ የሚያመለክት ነው (ኤፌ. 2፥16፤ ቆላ.2፥14)። መድኀኔ ዓለም ሊቤዠን ራሱን ለሞት የሰጠው በመስቀል ላይ ነውና። እኛ የምንሰብከውም የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው (1ቆሮ.1፥23)። በመስቀል ላይ የሚሞት የተረገመ አልነበረምን (ዘዳ. 21፥23)? ነገር ግን፣ ስለ እኛ ርግማን ኾኖ ከሕግ ርግማን ይዋጀን ዘንድ መሲሕ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቀለ (ገላ.3፥13)! የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም ይህንኑ ሲያመለክቱ፣ “በኦሪትም ሥርዓት በመስቀል፤ በስቅላት የሚቀጡ ሁሉ ርጉማን ዉጉዛን ነበሩ። ከጌታ በኋላ ግን የነጻነታችን ዐዋጅ የተነገረበት ሰላማዊ ዙፋን ስለኾነ ለክርስቲያኖች ሁሉ የነጻነት፣ የድል ምልክት ነው። ‘ገብረ ሰላመ በመስቀሉ’ ክርስቶስ ሰላምን እኩልነትን በመስቀሉ አድርጓልና2” ይላሉ።

 

እንግዲህ ይህንን ታላቅና ክቡር የክርስትና እውነት ለማስታወስና ለማሳየት በቤተ ክርስቲያን ትውፊት የተመሳቀለ የመስቀል እንጨት ምልክት ከክርስትና ጋር ተዛንቆ ይገኛል። ይህ የሚያሳፍር አይደለም። አሳፋሪው የሚኾነው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ካዳነን ጌታ ይልቅ ክርስቶስ ተሰቅሎ የሞተበት የተመሳቀለ እንጨት ምልክት ካልተመለከ (ካልተሰገደለት) ብሎ ዱታ ነኝ ማለት ነው። ሕይወት ያለው በምልክቱ ላይ ሳይኾን ምልክቱ የሚጠቍመው እውነት ላይ ነውና። እውነቱ ደግሞ የጌታችን ቤዛዊ ሞት በመስቀል ላይ መፈጸሙ ነው።

 

የመስቀል ምልክት ከላይ በተመለከትነው ምልክታዊ ፋይዳው በክርስትናው ዓለም ሁሉ ትውፊታዊ ቦታ አለው። ቄስ ኮሊን ማንሰል ስለዚህ ሐሳብ ሲጽፉ፣ “መስቀል የክርስትና ምልክት ነው። መስቀል በየቤተ ክረስቲያኑ ላይ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ በካህናት ልብስ ላይ… ወዘተ ይታያል። ቄሶች በእጃቸውም ኾነ በኪሳቸው መስቀል ይዘው ይሄዳሉ፤ ብዙ ሰዎችም መስቀልን በአንገታቸው ያንጠለጥሉታል። መስቀል ክርስቶስ የተሰቀለበትና የስቅለት ታሪክ መታሰቢያ ነው”3 ብለዋል።

 

የምንሰግድለት ግን በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ ለሞተልንና ሞትን አሸንፎ ለተነሣው ንጉሣችን ነው (ራእ.5)። ሃይማኖተ አበው፣ “እንከሰ ተሰቅለ እግዚእነ ወንሕነኒ ንሰግድ ለዘተሰቅለ ወወረደ ውስተ መቃብር ወተንሥአ እምኔሃ አመ ሣልስት ዕለት ወዐርገ ሰማያት፤—እንኪያስ የተሰቀለው የክብር ባለቤት ነው። እኛም ለተሰቀለው ወደ መቃብር ለወረደው በሦስተኛው ቀን ለተነሣው ወደ ሰማይም ለዓረገው እንሰግዳለን” 4 ይላል (ዘኤጲፋንዮስ፣ ም. 57 ክ. 9 ቊ. 18)። ሃሌ ሉያ!

 

መስቀልን አስመልክቶ በትምህርተ ኅቡአት ላይ የተጻፈውን ስንመለከት እጅግ ያስደምመናል። “ወበእላ ከናፍር ጾታ ነጊር ኢይትከሀል ጥንቁቀ፤ ዘእምትካት ኅቡአ ኮነ ይእዜሰ ክሡተ ምስጢረ ኮነ ለምእመናን፤ አኮ ከመ ይትረአይ አላ ከመ ይትሐለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ወቦቱ ንትመካህ ከመ ንሰብሖ — በእነዚህ ከንፈሮች ጠንቅቆ የመናገር ስልት ሁሉ የማይቻል ነው። ከጥንት ስውር የነበረው ዛሬ ግን ለምእመናን የተገለጠ ሆኗል። እናመሰግነው ዘንድ የምንመካበት ይህ መስቀል በልብ የሚታሰብ ረቂቅ ነው እንጂ በዐይን የሚታይ ግዙፍ ነገር አይደለም።5” እንዴት የሚደንቅ ነው!

 

የኛ ነገር! “መስቀሉን ሰቀሉት” እንዳይኾን

እንዴት አድርገው ሰቀሉት ወይም እንዴት አድርገን ነው የሰቀልነው? ኧረ! እነግራችኋለሁ። መስቀል በቤዝዎት ታሪክ ውስጥ ከነበረው ቦታ የተነሣ የክርስትና አርማና ምልክት ተደርጎ መወሰዱ ይታወቃል። ይህ በራሱ ችግር የለውም። ነገር ግን የመስቀሉ ምልክት በራሱ የተለየ መድኀኒትነት እንዳለው ማሰብና ማስተማር ግን የሚዘገንን ነው። በታሪካችን ውስጥ እንዲያውም ይህን አለማድረግ የሚያስቀጣበትና የሚያስነቅፈበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል “ፀረ ማርያም” ከሚለው ቀጥሎ “የመስቀል ጠላት” የሚለው ነቀፌታ በኢትዮጵያውያን ሃይማኖት፣ ባሕልና ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ የራሱን አሉታዊ አሻራ ካሳረፉ አባባሎች ውስጥ ይመደባል። በነዚህ ስያሜዎች አማካኝነት የማይወዱትን ሰው/ ቡድን ስምና ዝና ማጨቅየት በጣም ቀላል ኾኖ ኖሯል። 

 

አስቀድመን የነገሩን የትመጣነት በአጭሩ እንመልከተው። ዐፄ ዘርአ ያዕቆብና አድር ባይ ጋሻ ጃግሬዎቹ፣ በአገዛዝ ዘመኑ የተነሡትን የወንጌል አገልጋይ መነኮሳት፣ ማለትም አነ አባ እስጢፋኖስ (ዐምደ ሃይማኖት ወማኅቶት ቤተ ክርስቲያን ዘጕንዳጕንዲ)፣ አባ አበ ከረዙል፣ አባ ዕዝራንና ሌሎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን ለመፍጀት የተጠቀሙበት ዋነኛ ክስ “ፀረ- ማርያምና ፀረ- መስቀል ናቸው” የሚል ነበር። ንጉሡ በዐዋጅ ባስነገረው መሠረትም ለማርያም ስዕልና ለመስቀል ቅርፅ መስገድ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን ዜግነታዊ ግዴታ ኾኖ ተቈጠረ (ማንም ሰው “ይህን ማድረግ እምነቴ አይፈቅድም” ብሎ ሳይሰግድ በዜግነቱ መኖር አይችልም ነበርና)። ዘርዓ ያዕቆብም “ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ፤ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ፤—ለእነዚህ ሁለቱ ፍጥረታት [ለማርያምና ለመስቀል] የፈጣሪ ክብር ይገባቸዋል፤ በክብር [ከእርሱ ጋር] ተካክለዋልና።” 6 ሲል የኑፋቄ አዋጁን ያለኀፍረት አስቀሳፍቷል። 

 

ንጉሡ ለማርያምና ለመስቀል ቅርፅ መስገድን ጨምሮ ሌሎች እንግዳ ትምህርቶችን የማይቀበሉትን ክርስቲያኖች በዘግናኝና አሠቃቂ መንገድ ያሳድድ፣ ያገልልና ይገድል እንደነበር ወዳጆቹ ነን የሚሉ ሳይቀር በኩራት ጽፈውለታል። 7 አፍንጫቸውን እየፎነነ (እየጐመደ)፣ እጅ እግራቸውን እየከላ መነኰሳቱን ከነቆባቸው ተከታዮቻቸውንም ከነሳዱላቸው በደም ነክሮ ጨፍጭፏቸዋል። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በተረጐሙት “ገድለ አበው ወኣኀው” ላይ እንዲህ ተጽፏል፤ “በትምህርቱ [በአባ እስጢፋኖስ ትምህርት] የዳኑና ከሕይወት በር የደረሱ ብዙ ናቸው።… በድብ ፀር (በዘርአ ያዕቆብ) ዘመን ዘብር ከምትባል ሀገር ጀምሮ ደብረ ብርሃን ዝማ፣ ጐዘም እስኪደርስ፣ ከነዚህ አገሮች በስተግራ በኩልና በንጉሡ አደባባይም ሁሉ ሰማዕትነታቸውን በመልካም ሰማዕትነትና መንፈሳዊ ገድል ከፈጸሙት ውስጥ፣ ቍጥራ ቸውን ያወቅነው የቅዱስ ብፁዐዊ እስጢፋኖስ ወንድና ሴት ልጆች ሰማዕታትና ጻድቃን ጠቅላላ ድምር ፲፻፬ (1004) ነው። የማናውቀውን እሱ [እግዚአብሔር?] ንብረቱን ይሰብስብ። 8

 

…” እኒህ ሁሉ ክርስቲያኖች በዘርአ ያዕቆብ የቍጣና የአምልኮ ባዕድ እሳት የተበሉት ከሕያው እግዚአብሔር በቀር ለማርያም ሥዕልና ለመስቀል ምልክት አንሰግድም በማለታቸው ነበር።9

 

አንድም መስቀል በታሪከ ድነት ውስጥ ከነበረው ቦታ የተነሣ የክርስትና እምነት ምልክትና አርማ ተደርጎ መወሰዱ ባያስገርምም ነገር ግን መስቀሉ በራሱ የተለየ መድኀኒትነት እንዳለው ማሰብና ማስተማር ትክክል አይደለም። በወርቅ በከበረ ድንጋይ፣ ከእንጨትና በሌሎችም ነገሮች አስመስለን በሠራናቸው የመስቀል ምልክቶች ለመዳን መሞከር መጽሐፍ ቅዱሳዊነት የለውም። የተመሳቀለ የመስቀል ምልክት ያለውን ግዑዝ ነገር በሰሌዳ፣ በመጽሐፍ፣ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በተንቀሳቃሽም ኾነ ቋሚ ነገሮች ላይ ማዋል የነበረና ያለ ነገር ነው። በጌጣ ጌጥ መልክ አሠርቶ በተለያየ የአካል ክፍል ላይ ማንጠልጠል ወይም ደግሞ መነቀስም የተለመደ ኾኖ ቈይቷል። ይህ ሁሉ ኾኖ ግን፣ ሕይወታችን ለተሰቀለውና ከሙታን ለተነሣው ጌታ ያልተሰጠ፣ እናምነዋለን ለምንለው ወንጌል ሕይወታችን የማይኖር ሰዎች ደግሞም ለዐዲስ ልደት በሚኾን መታጠብና በመንፈስ መታደስ ሳንጐበኝ በኀጢአታችንና በበደላችን በሞት ሰንሰለት እንደታሰርን መስቀሉን ብናንጠለጥለው ሰቀልነው ቢባል እንጂ ሌላ ምን ፋይዳ አለው? ስመ ክርስትናን አንግበን መስቀሉንም አንጠልጥለን ሕይወታችን ግን ለክርስቶስ ለራሱ ያልተሰጠ ከኾነ “መስቀሉን ሰቀሉት” እንባላለን።

 

ይህም ብቻ አይደለም። ሌላም ጉድ አለ። “ከዘመናችን ስብከቶች፣ ትምህርቶችና ዝማሬዎች ውስጥ የመስቀሉን መልእክት ምን ሰወረው?” የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ ነው፤ ልንነጋገርበትም የተገባ ነው። በየጉባኤው የተዘሩት አንዳንድ ሰባኪያን፣ መምህራንና ዘማርያን ሕግን ያለ ጸጋ፣ የሥነ ሥርዓት ርምጃን ከተሓድሶ ውጭ ይሰብካሉ። ግለሰባዊ ድነትን ከማኅበራዊ ርኅራኄ ነጥለው ያመነዥካሉ። ፍቅር በጐደለው ሃይማኖት መመሪያዎችን እንደዶፍ ያዘንባሉ። የመስቀሉን ጥበብ ሸፍነው እውቀታቸውን ይደሰኩራሉ። የመሲሑን ግርማ ገፍትረው የራሳቸውን ገድል ይዘምራሉ። ሌሎች ዝነኞች በፈንታቸው በ“ክርስቶስ ስም” ሰበብ ጐረቤቶቻቸውን ተንኵሰውና አዳቅቀው ሲያበቁ በኩራት ይፍነከነካሉ። ተቃውሞ ከገጠማቸውም ራሳቸውን እንደ ሰማዕት ይቈጥራሉ። ለመኾኑ የራሳችንን ስምና ዝና ከፍ አድርገን የሰቀልነው መስቀሉን ወዴት ደብቀነው ነው? ኧረ፣ መስቀሉን ሰቀሉት!

 

ይህ ሐዋርያዊ ድምፅ እንዴት እንደማያቃጭልብን ግራ ነው፦ “በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና” (1ኛ ቆሮ. 2፥2)። እኛስ ምን ለማወቅና ምን እንዳወቅን ለማሳወቅ ነው ዛሬ በጽኑ የዘመትነው? በትኵረት ስንታይ የመስቀሉን ክብር እንፈልጋለን፤ ውርደቱን ግን እንሸሸዋለን። ምነው? ባለግርማው መሲሕ “ሥቅዩው ሎሌ” አልነበርምን?

 

አንዳንዶቻችን ደግሞ በተገላቢጦሽ ይቅርታን ከመስቀሉ ውጭ እናውጃለን። ኅብረትን ያለ ጸጋና ተግሣጽ እናልማለን። ንጉሡን ገፍትረን መንግሥቱን ልንሰብክ እንቃዣለን። ምትክ የለሽ የኾነውን ወንጌል በአርቲ ቡርቲ ተክተን እየተጯጯህን ሰዎችን ለንስሐ እንጋብዛለን። እግዚአብሔርን ማሳዘዘናችን ግድ ሳይለን ሰዎች እንዳይከፋቸውና ከስብሰባችን እንዳይቀሩብን እንጠነቀቃለን። መንፈስና ኀይልን በመግለጥ የመስቀሉን ቃል ማወጅ ስላቃተን፣ ወጣቶቻችን እንዳያኮርፉ እናቈላምጣቸዋለን። ኧረ መስቀሉ ወዴት ነው? ወንጌል የሰዎችን ሓሳብ እያንኰታኰተ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ያገንናል። ለሚያምኑ ሁሉ ለማዳን የእግዚአብሔር ኀይል ነው (ሮሜ. 1፥17)። የመስቀሉ ቃል ለብዙዎች “ሞኝነት” ነው፣ ለበርካቶች “ማሰናከያ” ነው፣ ለአንዳንዶች ደግሞ “የእግዚአብሔር ጥበብና ኀይል ነው” (1ኛ ቆሮ. 1፥18)። ይህን እንዴት እንዘነጋለን? ይህ እውነት ችላ ከተባለስ ለተከታዩ ትውልድ ምን እናወርሳለን?

 

1J.D Douglas and Merrill C. Tenney. (eds.), New International Bible Diction- ary (Grand Rapids: Zondervan, 1987), p., 241.
2አባጎርጎርዮስ፣የኢትዮጵያኦርቶዶክስተዋሕዶቤተክርስቲያንታሪክ (አዲስአበባ፤አልቦአሳታ ሚ፣ 1991 .)ገጽ፣ 104፡፡
3ኮሊንማንሰል (ቄስ)ትምህርተክርስቶስ (አዲስአበባ፤ 1999 .)ገጽ፣ 334፡፡
4የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ፣ ሃይማኖተ አበው፣  (አዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ 1986)፣ 192፡፡
5መሠረትስብሐትለአብ፣ስምዓጽድቅብሔራዊ  (አዲስአበባ፤አርቲስቲክማተሚያቤት፣ 1951 .)ገጽ፣ 109-110፡፡
6መስተበቊዕ ዘመስቀል
7ኢኦተቤክ. ተአምረማርያም (አዲስአበባ፤ትንሣኤማሳተሚያድርጅት፣ 1985 .)ገጽ፣ 133-134፡፡
8ጌታቸውኃይሌ፣ደቂቀእስጢፋኖስበሕግአምላክ” (ሚኖሶታ፤ኮሌጅቪል፣ 1996)ገጽ፣ 220-221፡፡
9ኢኦተቤክ.ተአምረማርያም (አዲስአበባ፤ትንሣኤማሳተሚያድርጅት፣ 1985 .) 133፡፡

 

Seen 8669 times Last modified on Wednesday, 07 May 2014 08:37
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 71 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.