You are here: HomeOpinions‹‹ዕርቅ - የጥበብ መንገድ››

‹‹ዕርቅ - የጥበብ መንገድ››

Written by  Tuesday, 01 March 2016 14:13

እኛ በክርስቶስ የምናምን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች አንድነትና ስምምነት አጥተን ስንጣላ የሚሆነው ነገር ምን ይመስላል ቢባል፡ በታላቅ ጥበብና ጥንቃቄ በተባለው የሸራ ቅብ ላይ አሮጌ የቀለም ጣሳ ቀድደን ድፍድፉን ቀለም ማፍሰስ ነው፣ ለመብላት ያሰፈሰፉ ሰዎች ዐይኖች በሚቋምጡት በወግ የተሰናዳ የእንጀራ ገበታ ላይ አሸዋ መድፋት ነው፤ ለድል አንድ ምዕራፍ የቀረውን ሯጭ ቋንጃ በስለት መበጠስ ነው፡፡ ጠብ የዓለም ሁሉ ሰቀቀን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቤተሰብ መካከል ጠብ ጉልበት ካገኘ ለምድርዓለም የተሰጣት የተስፋ ብርሃን ተስለመለመ ማለት ነው፡፡

 

ምን ያጣላናል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ቢሆንም ለጊዜው ለምን እርቅ ያስቸግረናል? የሚለውን መመራመር ሳይሻል አይቀርም፡፡ የዕርቅና የአንድነት እንቅፋቶች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ፈጥጠው የሚታዩኝን አራት ጭራቆች ብቻ ላንሳ፡፡

 

አንደኛው፡ ጠብ የሚያመጣውን አደጋ አለመፍራት ነው፡፡ “የመጣው ይምጣ” የሚል ሥጋዊ ድፍረት ነው፡፡ “ኧረ ይህ ነገር ውሎ ያደረ እንደሆነ ክፉ ጣጣ አለው” ሲባል፡፡ “ምን ይመጣል ቢበዛ መለያየት ነው” የሚል መንፈሳዊ ድንዛዜ ከክርስቶስ የአንድነት ጸሎት እንዴት የራቀ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱን እንዲህ ብሎ ለመነው፡፡ “አንተ እንደላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ….እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ፡፡” ይህ እጅግ አሳሳቢ ጸሎት ነው እንደጌታችን አመለካከት እና አንድ ካልሆንን ዓለም የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛነት ለማመን ይብዳታል ማለት ነው፡፡ የተራቀቀ የወንጌል ስርጭት ስልታችን፣ የፈረጠመው አደረጃጀታችን ወይም የካበተ ልምዳችን ሰውን ሊያሳምን አይችልም ማለት ነው፡፡

 


ሁለተኛው
፡ በራስ አመለካከትና አቋም መዋጥ፣ የሌላውን ለማየት አለመቻል፣ አለመፈለግም፣ የሌላውን ወንድም ወይም ወገን የአስተሳሰብ መንገድ መናቅ፣ ማጣጣል፣ መጠራጠር፣ አዛብቶ መተርጎም፣ ይህንንም የሚመስል የራስ አስተሳሰብ ደሴተኛነት ነው፡፡ በራስ እንደመታሰር ያለ ግዞት የትም የለ፡፡

 

“ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር” ያለው ሐዋርያ ምሳሌ አድርጎ የሚያቀርብልን ራሱን ባዶ ያደረገውን ኢየሱስን ነው፡፡ የባልንጀራውን የአባቱን ፈቃድና አሳብ አስበልጦ ወደደ፣ የሚያስከፍለውን ከፍሎ የኋላ ሽልማቱን በክብር ተጎናጸፈ፡፡ የሌሎችን አሳብ መቀበል ኪሣራ ከመሰለን የኢየሱስ ወንድሞች ነን ለማለት እንዴት እንደፍራለን)

 


ሦስተኛው
፡ “አንዴ ብያለሁ፣ አሳቤን አልለውጥም” የሚል ዕቡይነት፣ ለተሻለ ነገርም ቢሆን ማፈግፈግን አለመውደድ፣ ቢያዋጣም ባያዋጣም የያዝኩትን አቋም እገፋበታለሁ የሚል ቂልነት ነው፡፡ ሞኝ ካመረረ፣ በግ ከበረረ፡፡

 

የጠፋው ልጅ የተሞኘው ስሜቱን ብቻ አዳምጦ ከቤት የወጣ ቀን ነው እንጂ ውድቀቱን አይቶ በልቡ የተጸጸተ ቀን አይደለም አቅጣጫ ቀይሮ ወደተገቢው ቦታ መመለስ ልባምነት ነው እንጂ ፈሪነት አይደለም፡፡ በጨለማ መንገድ መፈርጠጥ ነው ሥጋዊነት፣ መመለስ መንፈሳዊነት ነው፡፡

 


አራተኛው
ጭራቅ ምንድነው የተባለ እንደሆነ፡ “የታረቅሁ እንደሆነ የተስማማሁ እንደሆነ ይህ ይቀርብኛል፣ ይህ ይጎድልብኛል” የሚል የሞኝ ስስት ነው፡፡ ሽማግሌ/አስታራቂ ሰምቼ እሺ ብል ማንነቴ ይደበዝዛል፣ ክብሬ ይስለመለማል፣ ጥቅሜ ይቀናነሳል ተደማጭነቴ ዝቅ ይላል የሚል አጉል ፍርሃት በአስር በትር እንድንደባደብ ያደርገናል፡፡ የፈሪ ዱላ አሥር ነው፡፡ ዕርቅና አንድነት ያበለፅጋል እንጂ አያደኸይም፤ ለመኖርና ለመክበር ዋስትናችን የከበበን ጭፍራ ብዛት ሳይሆን የሚወደንና የሚያስብልን የእውነት ዳኛ እግዚአብሔር ነው፡፡ እውነተኛ ዕርቅ ከድርድር ሰነዱ ይልቅ በጻድቅ አምላክ ላይ ባለን እምነት የምንወስነው የጀግንነት ውሳኔ ነው፡፡

Seen 13479 times Last modified on Tuesday, 01 March 2016 14:30
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 168 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.