You are here: HomeOpinions“እየመረጥን እንዝፈን! እየመረጥንም እንሞዝቅ!” የወር ተረኛው ርእሰ ጒዳይ

“እየመረጥን እንዝፈን! እየመረጥንም እንሞዝቅ!” የወር ተረኛው ርእሰ ጒዳይ

Written by  Friday, 17 June 2016 01:45

“ቤት ያጣው ቤተኛ” የዚህ ጽሑፍ ፅንሰትና ልደት፣ “የወር ተረኛው” ርእሰ ጒዳይ ነው፡፡ ባልንጀራዬ ዮናስ ጐርፌ፣ “ቤት ያጣው ቤተኛ—ሙዚቃ፣ ሙዚቀኛነትና ኢትዮጵያዊቷ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርእስ ያሳተመው መጽሐፍ እንዲሁም መጽሐፉን ተከትሎ የወጡ በርካታ አጸፋዎችና መወድሶች፣ የዚህ ጽሑፍ መነሻ ናቸው፤ መድረሻ ግን አይደሉም1፡፡ አጸፋዎቹንና መወድሶቹን በተመለከተ ጠቅለል ካለ አስተያየት ያለፈ (ያውም ኢርቱዕ በሆነ መንገድ) ዝርዝር ሐተታ አላቀርብም—ፋይዳ ያለው ስለማይመስለኝ2፡፡ ጌታ ይችን ምስኪን ጽሑፍ ባርኮ ዳርቻዋን ቢያሰፋ ግን፣ ምንኛ ደስተኛ እሆን ነበር፡፡ ይህች መጣጥፍ፣ “ምስኪን” ያልኋት፣ “በጠባብ ደረት በአጭር ቊመት” በመወሰኗ ብቻ ሳይሆን3፣ በችኰላ የተጻፈች እንዲሁም ከብዙ አንጻር ጽንፈኛ መጣጥፍ ስለመሰለችኝ ነው—በነሂትለር መንደር እማሆይ ትሪሳ ይወደሱ፣ ይንገሡ የምትል የቅስቀሳ ጽሑፍ ቢጤ፡፡ ከብዙ አንጻር ሳየው የዘመኑ መንፈስ ቋሚው የክርስትና ትምህርት በሚቀዝፍበት እቅጣጫ እየቀዘፈ እንዳልሆነ ከገባኝ ሰነባብቷል፡፡ “ሚስቴን ለመፍታት ፈልጊያለሁ፣ እስቲ ጥሩ ጥቅስ ፈልግልኝ” ወይም “ሊቃውንት የማይወዛገቡበት ርእሰ ጒዳይ ስለሌለ፣ እኔ የምደግፈውን አስተሳሰብ አቅጣጫ የሚከተል ምሁር ስሙንና መጽሐፉን ብትጠቁመኝ” ከሚለው ጀምሮ፣ የዘፈን ዜማ የሚያሰርገው4፣ “ሜልኮል ትናቀኝ” (2ሳሙ. 6÷21) በሚባለው “ሽብሸባ” በዐውደ ምሕረቱ ላይ የዘፈን ውዝዋዜ፣ ዳንኪራና ዳንስ እስከ ሚያሾልከው ድርስ፣ የዘመኑ መንፈስ “አትዝፈኑ!” ለሚለው ተግሣጽ ብዙ የተመቸ አይደለም—ዞሮ ዞሮ በተለያየ መልክ በደንብ እየተጨፈረ በደንብ እየተረገጠ ነው5፡፡

 


እግዚአብሔር የሚሠራውን ግን ማን ያውቃል? ምናልባት ይህ አሁን የተነሣው ውይይት ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ቤተ እምነቶች6፣ የዝምታና የእኔ-የምንተዕዳዬን “ፖሊሲአቸውን” በመለወጥ፣ በጒዳዩ ላይ የአቋም መግለጫ እንዲያወጡ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከመጥፎ ነገር ውስጥ መልካም ነገር እንዲሁም እጅ በምታኽል ደመና አገር ማጥገብ የሚችለው ልዑል አምላክ እስካለ ድረስ፣ “ድንቄም” የሚለው ምፀት የእኔን መጣጥፍ ሊያኳስስ፣ ሊመጣ የሚችለውንም ለውጥ ሊያሳንስ አይችልም፡፡ ስለዚህም እሞግታለሁ፡፡

 


ወንድም ዮናስ ጐርፌ የረጅም ጊዜ ወዳጄ ነው (“ረጅም” የሚለው ቅጽል አንጻራዊ መሆኑ የሚጠፋችሁ አይመስለኝም)፡፡ እስከማውቀው ድረስ ወንድም ዮናስ፣ በሙያውም ሆነ በሥነ ምግባሩ ተወዳጅ ሰው ነው፡፡ ግልጽነቱ፣ ለጋስነቱ እንዲሁም ለሰዎች ያለው በቀላሉ የማይነጥፍ ፍቅር በአብዛኞቻችን ዘንድ እንዲከበር አድርገውታል (መቼም ሁሉ ይወደኛል ማለት ሞኝነት፣ ሁሉ ይጠላኛል ማለትም ወፈፌነት መሆኑን እናውቃለን ለዚህም ነው፣ “በአብዛኞቻችን” የሚለውን ቊጥብ ቅጽል የመረጥሁት)፡፡ ምናልባትም ብዙ ልንጠቀምበት ሲገባ፣ በተለያየ ምክንያት (ከአቀራረብ እስከ አስተዳደር፣ ከነገረ መለኮት እስከ ባህል) እንዲሁም ምክንያታዊ በሆነና ባልሆነ ሰበብ፣ የሚገባውን ያህል ያልተጠቀምንበት እርሱም የሚገባውን ያህል ያላገለገለን ሰው ይመስለኛል፡፡ በአንድ ታሪካዊ አጋጣሚ አሠልጥኖ ያቀረባቸው የቡድን መዘምራን፣ ብዙዎቻችንን አስደምመው አስደንቀው አልፈዋል፡፡ እኔ በግሌ እንደነዚያ የተዋጣለት የመዘምራን ቡድን፣ ያን ዐይነት ጡዑመ ዝማሬ፣ እንደ ጅረት የሚፈስ ማኅሌተ እግዚአብሔር ሰምቼ የማውቅ አይመስለኝም፡፡ ያውም ያለአንዳች የሙዚቃ መሣሪያ እንዲያው በአካፔላ (a cappella) ስልት የቀረበ መሆኑ፣ ነገሩን ትንግርት አድርጐት ዐልፏል፡፡ ያን የመዘምራን ቡድን ያላየ ሰው፣ እንዳጋነንሁ ሊጠረጥር ይችላል—ግን አንዳችም ግነት ወይም እብለት የለበትም፡፡ ንባቡ ያመረ፣ ምስጢሩ የጠለቀ፣ ጣዕመ ዝማሬው የረቀቀ መዝሙር ሰምተናል፡፡ ያን የመዘምራን ቡድን እጹብ ድንቅ ዜማ ያየ፣ በወንድም ዮናስ ጐርፌ ውስጥ እጅግ ትልቅ ስጦታና ክህሎት እንደ ታጨቀ የሚያስተውል ይመስለኛል፡፡ ግን ምን ይደረግ፣ የላመ የጣመ ለመብላት የታደልን አይመስልም፡፡ ተቀባብለን መሥራት አልሆንላችሁ፣ ተረዳድቶ መኖር አላምርባችሁ ብሎን ይኸው እንዳለን አለን፡፡ ጆሮ የሚበጥስ የሙዚቃ ጩኸት፣ የገመረረ ድምፅ፣ ለቅዱሳት መጻሕፍት ባዕድ የሆነ ግጥም፣ ለአማርኛ ቋንቋ ባይተዋር የሆነ የሰዋስው አሰካክ፣ ግጥምና ትርጒሙ ለአፍታ ተራክቦ በማያደርጉበት መዝሙር፣ እንዲያው በአጭሩ ሥርና ጫፉ በውል በማይታወቅ የዝማሬ ማዕበል ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ቅኔ ዘርፎ፣ ግሥ ገሥሦ፣ ወረብ በማዘጋጀት ማኅሌት መቆም ሲበዛ እልም ነው፡፡

 

የመሞገት መብት አለኝ!

እኔ፣ ሐሳብን በማንኛውም መልኩ መግለጽ የሰብአዊ መብት አንዱ ክፍል መሆኑን አምናለሁ፡፡ ወንድም ዮናስ የመናገር መብቱን ተጠቅሞ፣ መጽሐፍ በመጻፍ ሐሳቡን እንዳንሸራሸረ ሁሉ፣ እኔም መጣጥፍ በማዘጋጀት ከእርሱ የምለይበትን ሙግት አቀርባለሁ፡፡ ስለዚህ ይህን ከአምላክ የተቸርሁትን መብት እውን ማድረጌ፣ ቢሆን ሊያስመሰግነኝ እንጂ፣ በጭራሽ ሊያስነቅፈኝ አይገባም፡፡ አድበህ ጨምተህ ለምን አትቀመጥም የሚለኝ ካለ ተሳስቶአል፡፡ ከዚህ ባለፈ በሥልጡን ውይይት አገር እንደሚደረጅ፣ ጨለማ እንደሚበራ፣ ነገረ መለኮት እንደሚጐመራ አምናለሁ፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ ከባልንጀራዬ ጋር እንካ ሰላንታ እንደ ገጠምሁ ሊታሰብ አይገባም፡፡ የጽሑፉም ይዘት ከእንካ ሰላንታ መራቁ፣ ሰላም ወዳድና ጭቅጭቅ ጥዩፍ ለመሆኔ አንዱ አብነት ይመስለኛል፡፡ እንደ ወትሮው ሁሉ፣ ዐቅም በፈቀደ መጠን ሥነ ምግባርን ተከትዬ ሐሳቤን እሰነዝራለሁ፤ ሒሴን አደራጃለሁ፡፡ “ሰው ሆኖ አይስት፣ እንጨት ሆኖ አይጤስ” የለምና ከዚህ የሥነ ምግባር መስፈርት ጐድዬ ብገኝ፣ በአደባባይ ይቅርታ ለመጠየቅ ሙሉ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ በምንም ዐይነት መልኩ፣ ከሐሳብ ጋር መጣላት ከግለሰቦች ጋር መጣለት አይደለም፤ ከሐሳብ ጋር መፋጨት ከግለሰቦች ጋር መቧቀስ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሐሳቦች ሲቧቀሱ፣ ያሞጠሞጡ ሐሰቦች እየተወቀሩ ቱንቢ ይገባሉ፣ ገለባ የሆኑ ሐሰቦች ይበናሉ፣ ስሑት ሙግቶች ይተናሉ፡፡ ስለዚህ “መርጠን እንዝፈን” የሚለው የወንድም ዮናስ ጐርፌ ነባርና ቋሚ ሙግት፣ ትክክል አይደለም የሚል አቋም አለኝ፡፡ በዚህም ጽሑፍ፣ በምን ምክንያት ወደዚህ ድምዳሜ እንደ ደረስሁ ለመተንተን ሙከራ አደርጋለሁ፡፡ በአጭሩ ከወንድም ዮናስ ጐርፌ በተቃራኒው አንጻር የቆምሁ፣ ክርስቲያን ወንድም ነኝ፡፡
“ሰጥቶ መቀበል”


ዳር ድንበር ሲጣስ መኻል አገር ወደ ዳርድንበርነት ይቀየራል፡፡ ባላንጣችን ሰይጣንም ሆነ ዓለም ብልኅ ተደራዳሪዎች ናቸው፡፡ “ሰጥቶ መቀበል” የሚባለውን የድርድር ቴክኒክ፣ ከፖለቲከኞቻችን ይልቅ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ እንዲያው እመር ብለው፣ በአንዴ የመኻሉ አገር ይገባኛል የሚል የገልቱ ጥያቄ አያቀርቡም፤ ደረጃውን በጠበቀ ድርድር ግን፣ መኻል አገር መናገሻ ከተማቸው እንደሚሆን ልቦናቸው ያውቀዋል፡፡ በአሜሪካንና በአውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ሕይወት የታየው፣ ይኸው የድርድር ስልት ነው፡፡ በአንድ ወቅት የአልኮል መጠጥ መጠጣትና ሲጃራ ማጤስ፣ የቅድስና ጠር እንደ ሆኑ በብርቱ ይሰበክ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እንኳን በምዕመኑ፣ በመጋብያኑም ዘንድ እንደ ቊም ነገር አይታይም፡፡ በአንድ ወቅት፣ “ሮክ ኤንድ ሮል” የሙዚቃ ሥልት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መቅረብ የለበትም የሚል የጦፈ ክርክር ነበር፡፡ ዛሬ በሮክ ኤንድ ሮል የማይውረገረግ ቤተ ክርስቲያን ማግኘት ሲበዛ አስቸጋሪ ነው7፡፡ በአንድ ወቅት ክርስቲያን ሰዶማዊ ሊሆን አይገባውም የሚል እሰጥ አገባ ነበር፤ ዛሬ የሰዶማውያኑ የቤተ ክርስቲያን ሙሉ አባልነት ጸድቆ፣ ውይይቱ ጠለቅ መጠቅ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሮል፡፡ ይኸውም ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ሰዶማውያንን በሙሉ አባልነት መቀበል ብቻ አጥጋቢ አይሆንም የሚል አቋም ስላላቸው፣ ሙሉ አባልነታቸው እንደ ጸደቀ ሁሉ፣ በቅስናና በሊቃነ ጳጳስነት ከማገልገል መብታቸው ሊጐሉ አይገባም እየተባለ ነው፡፡ ስለዚህ የቅስና መንበራቸውን በመያዝ፣ ሙሉ ክህነታዊ ባርኮት ይስጡን፣ ሥርዐተ ቊርባን ይምሩልን፣ እንዲያው በአጠቃላይ አብነታቸውን ያሳዩን፣ ፋናቸውን ያስከትሉን እየተባለ ነው፡፡ ሙግቱ ደረጃውን ተከትሎ እንዴት እንዳደገ ልብ ይሏል፡፡ “ግማሽ ሕይወት ይመር ግማሽ ሕይወት ዑመር”8 ማለት ከዚህ ውጪ፣ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

 

የዘፈን እንዝፈን፣ የዘፈን አንዝፈን ጥያቄ ከግብረ ሰዶም ክርክር ጋር አንድ ዐይነት ነው እያልሁ አይደለም፡፡ እኔ ሰዶማዊነትን የጠቀስሁት፣ የቤተ ክርስቲያን ሥነ ምግባር እየተጣሰ፣ አስተምህሮዋ እየተማሰ መሆኑን ለማመላከት ያህል ብቻ ነው፡፡ የዚህም ጽሑፍ ቀዳማይ ዐላማዎቹ መኻል አንዱ፣ ይህ የአስተምህሮ ዝግመተ ለውጥ፣ ተገቢ ያለመሆኑን መውቀስና መዝለፍ ነው፡፡ ዘፈን፣ ጭፈራና ዳንኪራ ለኢትዮጵያ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አማኞች ሲበዛ ባዕድ ነው፡፡ ባህል እንደሚለወጥ፣ ቋንቋም እንደሚቀየር ዐውቃለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ቋሚ ወይም “ዐፅመ ርስት” የሚባል ነገር እንደ ሌላ እረዳለሁ፡፡ ነገረ መለኮት ግን፣ በዚህ ዐይነቱ የዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለበት ብዬ በጭራሽ አላምንም9፡፡ በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ መሆን አለበት ከተባለ ግን፣ በርቱዕ አስተምህሮና በኑፋቄ ትምህርት መኻል ነባራዊ የሆነ ግድግዳ አለ ማለት ያስቸግራል፡፡ የጊዜ ጒዳይ ካልሆነ በቀር፣ የጽድቅ ሰማዕታት ውግዝ አራጥቃ (መናፍቅ) የማይሆኑበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ የጊዜ ጒዳይ ካልሆነ በቀር፣ ክርስትና ከእስልምና ጋር የማይቀላቀልበት፣ ከቡዲሂዝም ጋር ውሕደት የማያደርግበት፣ ከይሁዲ ሃይማኖት ጋር የማይፈጣጠምበት፣ በአጠቃላይ መሥዋዕት እንሆንላቸዋለን የምንላቸው አስተምህሮዎቻችን ለድርድር የማይቀርቡበትም ሆነ፣ የማይለወጡበት አንዳችም ምክንያት አይታየኝም10፡፡

 

እውነቱን ለመናገር ዘፈን እንዝፈን ወይስ አንዝፈን የሚለው ጥያቄ፣ የዳር ድንበር ጥያቄ ነው፡፡ የዳርድንበር ጥያቄ የሚሆንበት ቢያንስ ሁለት ዐበይት ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል፡፡ በየትኛውም መስፈርት ርእሰ ጒዳዩ፣ ዐበይት ከሚባሉት ክርስቲያናዊ ትምህርቶች መኻል የሚፈረጅ አይደለም—ከንዑሳን ወይም ከደቂቃን አስተምህሮዎች መኻል እንጂ11፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ርእሰ ጒዳዩ ፍርጥም ያለ አቋም ለመውሰድ አስቸጋሪ የሚያደርጉት ሥነ ምግባራዊ፣ ባህላዊና ነገረ መለኮታዊ ጒዳዮች ጋር መጐዳኘቱ ነው12፡፡ አንድም ጐበዝ ተነሥቶ፣ “ዝፈኑ” የሚል ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊያሳየን አይችልም፡፡ በአንጻሩ፣ “አትዝፈኑ” የሚሉትን ጥቅሶች አማራጭ ትርጓሜያቸውን በመወሰን፣ ክፍሉ በመደበኛው አካሄድ ዘፈን የሚለውን ቃል የሚወክል አይደለም ማለት ይቻላል (ወንድም ዮናስም ሆነ አንዳንድ “የነገረ መለኮት ድጋፍ ሰጪዎች” ይህንኑ ነው እያደረጉ ያሉት)፡፡ እንግዲያው ሙግታችን ፈርጀ ብዙ ጒዳዮችን ማጣቀሱ፣ ጒዟችንን ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ነው ጒዳዩ የዳርድንበር ጥያቄ ነው ማለት አግባብ የሚሆነው13፡፡

 

የእንዝፈንና የእንጨፍር አጀንዳ የቤተ ክርስቲያንን ቅጥር ዐልፎ ከገባ ግን፣ በምንም ሂሳብ ለቤተ ክርስቲያን ክብር ሊሆንላት አይችልም፡፡ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይ እምነት ሊያድርባቸው አይችልም፡፡ አትዝፈን ሲባል የከረመው ሰው፣ ነገ ዝፈን ከተባለ፣ ዛሬ አትንኩ አትቅመሱ የተባሉ ሥነ ምግባራዊ ጒዳዮች፣ ነገ ላለመለወጣቸው ዋስትናው ምንድን ነው? በምንም ሂሳብ የመሐሙድን ትዝታ ማንጐራጐራችን፣ የቴዲ አፍሮን ጥቊር ሰው መኰምኰማችን ከጥሬነት ወደ ብስልነት አያሻግረንም፡፡ በምንም መልኩ በዚህ መንገድ የውስጥ ፍሥሓና ሐሴት ልንጐናጸፍ አንችልም፡፡ ባለመዝፈኔ ተጐዳሁ፣ ናይት ክለብ (ጭፈራ ቤት) ባለመሄዴ ከደስታ ጐድያለሁ ብሎ የሚቈጭና በዐላፊው ጊዜ የሚብከነከን ክርስቲያን ቢኖር፣ በእውነቱ እጅግ እገረማለሁ14፡፡ ተገላገለን የሚል እንጂ፡፡ በዚህ ረገድ ለውጥ የሚመጣ ከሆነ (አብያተ ክርስቲያናት ዘፈንን “ግባ” የሚሉት ከሆነ) ለውጡ ከሚያመጣው “በረከት” ይልቅ፣ የሚያስከትለው ጥፋትና መዘዝ ከብዙ አቅጣጫ ሰፊ ነው15፡፡

 

የአልኮል መጠጦችን እንጠጣ ወይስ አንጠጣ የሚለውም ክርክር፣ በይዘትም ሆነ በትንታኔው ከዚህ ርእሰ ጒዳይ ጋር በብዙ መልኩ ኲታ ገጠም ነው፡፡ በነገረ መለኮት፣ አንዱ አስተምህሮ ከሌላው ጋር እንደ ሰንሰለት የመያያዝ ጠባይ አለው፡፡ አንዱ ሲፈታ ሌላው ጸንቶ የሚቈምበት ዐቅም ወይም ባሕርይ የለውም፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልክ የመገናኘት፣ የመደጋገፍ፣ የመሰናሰን ባሕርዮት አላቸውና፡፡ ለዚህም ነው መናፍቃን በአንድ አስተምህሮ ሲስቱ፣ ያን አስተምህሮ በሳቱበት ቅጽበት፣ በበርካታ አስተምህሮዎች መንገድ ጥሰው የሚወጡት፡፡ በርግጥ መዝፈን ከጸደቀ፣ የዘፈን መንታ ወንድም የሆነው መጠጥ እነሆ በደጅ ነው16፡፡ ከዚያም ታናናሽ ወንድሞቹ ማጨስና መቃም፣ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ” በሚለው አካሄድ፣ የይገባኛል ጥያቄ የማቅረብ፣ ሙሉ መብት ይጐናጸፋሉ፡፡ አንዱን ፈቅዶ ሌላውን ወግድ ማለት በፍጹም አይቻልም፡፡ ሁሉን ደግፎ የያዘው መሠረት ከተናደ፣ በምን መሠረት ላይ ቆሞ እነዚህን ተጓዳኝ ጒዳዮች ወግድ ማለት እንደሚቻል አይገባኝም፡፡ በዚህ አንጻር ሲታይ ዛሬ እየተሟገትን ያለነው፣ በዘፈን ርእሰ ጒዳይ ላይ ብቻ አይደለም፤ ከእርሱ ጋር ተጓዳኝ በሆኑ ፈርጀ ብዙ ግብረገባዊ ርእሶች እንጂ ፡፡17

 

ዘፈን ወይስ መዝሙር


ቋንቋ የሰዎች ስምምነት ውጤት ነው፡፡ በሬን በሬ ለማለት፣ ግድግዳን ግድግዳ፣ አህያን አህያ ለማለት አንዳችም ሥነ አመክንዮአዊ ምክንያት የለም፡፡ አንድ ቃል በሚወክለው ሐሳብ ወይም በሚያመለክተው ነገር ስንስማማ ተግባቦት ይፈጠራል፡፡ በዚህ አንጻር የአንድን ቃል ትርጒም የመወሰን እንዲሁም አማራጭ ትርጓሜውን የመለጠጥም ሆነ (እንደ ብር ማሰሪያ ላስቲክ) የማሳነስ ሙሉ መብቱ የቋንቋው ተጠቃሚዎች ነው፡፡

 


የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ዘፈን እና መዝሙር ለሚሉት ቃላት ያቀረቡላቸው ገለጻ፣ በብዙ መልኩ አንድ ዐይነት ነው፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ዐውደ ምንባቦች ውስጥ፣ ሁለቱንም ቃል ያለአንዳች የትርጒም ለውጥ እያቀያየርን በተወራራሽነት ልንጠቀምባቸው እንችላለን፡፡ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ ግን፣ ዘፈን እና መዝሙር እጅግ ደማቅ መስመር ተበጅቶላቸዋል፡፡ ይህም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ስያሜ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶአል፡፡ መዝሙር የሚለው ቃል በተለያየ መልኩ ከአምልኮተ እግዚአብሔር (ለአምላክ ከሚቀርብ ማኅሌት) ጋር የሚጐዳኝ ሲሆን፣ ዘፈን የሚለው ደግሞ ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉ ነው፡፡ እኔ በዚህ ጽሑፍ ዘፈንና መዝሙር የሚሉትን ቃላት የምጠቀመው፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መደበኛ በሆነው መንገድ ቃላቱን በሚጠቀሙበት ትርጒማቸው ነው፡፡ ስለዚህ በርእሰ ጒዳዩ ላይ የምናካሄደው ውይይት፣ በቃላት መረጣ ላይ የሚደረግ ውይይት፣ እንዲያው ዝም ብሎ የቃላት ጭቅጭቅ ተደርጐ መወሰድ የለበትም—ቃላቱ በሚወክሉት ፅንሰ ሐሳብ ላይ የሚካሄድ ሙግት እንጂ፡፡

 


እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ ክርስቲያን ዘፈን መዝፈን የለበትም የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው፡፡ ብሔራዊ መዝሙሮች ወይም ለአገራቸው ትልቅ ሥራ ሠርተው ያለፉ ጀግኖችን የሚያሞካሹ ዘፈኖችን በተመለከተ ግን፣ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ የተለያየ አቋም ያለው ይመስለኛል18፡፡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ብናደርገው ምንም አይደለም ሲሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ዜማ የተቀላቀለበት ነገር ከአድናቆት ወደ አምልኮ የመንደርደር ጠባይ ስላለው፣ ክርስቲያኖች እንዲህ ዐይነቱን ዘፈን መዝፈን የለባቸውም ባዮች ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በዚህ መልክ ጀግኖችን ማድነቅ፣ ለሰዎች ኅሊናዊ ብያኔ መተው አለበት ይላሉ (ሮሜ 14÷1-6)፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ያለው ልዩነት ይህ ብቻ ነው፡፡

 


ወንድም ዮናስ በዘፈንና በመዝሙር መካከል ያለው ግድግዳ፣ ሙሉ ለሙሉ መፍረስ አለበት የሚል አቋም የለውም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአውስቦት/በፍትወት የነፈዙ፣ በጦረኝነት የከነፉ፣ በደም የሰከሩ፣ በጥላቻ የተሞሉ፣ በዘረኝነት የጨቀዩ በቀላል አነጋገር ከክርስቲያናዊው ሥነ ምግባር ጋር በእጅጉ የሚጣረሱ በርካታ ዘፈኖች ስላሉ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖች፣ “እየመረጡ መዝፈን” ይጠበቅባቸዋል ባይ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ለሙሉ ፈቅዷል ብሎ እየሞገተ፣ በአንጻሩ ደግሞ የተወሰኑ ማዕቀቦች መኖር አለባቸው ለምን እንደሚል ለእኔ ግልጽ አይደለም—ማለትም በምን ሒሳብ ነው ማዕቀብ የሚጥልባቸው? ለማለት ፈልጌ ነው19 ፡፡ የሆነው ሆኖ፣ በዚህ አንጻር ሲታይ ወንድም ዮናስ በሩ ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጋ፣ በአንጻሩ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ እንዲከፈት አይፈልግም—እየመረጥን እንድንዘፍን፣ እየመረጥን እንድንሞዝቅ እንጂ20 —በሌላ አነጋገር በሩ ደርበብ ተብሎ እንዲከፈት እንጂ፣ ሙሉ ለሙሉ ወለል ተድርጎ እንዲከፈት አይፈልግም፡፡ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾችም ላይ ያለው አካሄድ፣ “ደርበብ ተብሎ ይከፈት” ከሚለው የተለየ አይደለም 21፡፡ እኔ ደግሞ ክርስቲያኖች እየመረጡ መዝፈን የለባቸውም፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾችም እየመረጡ መሞዘቅ የለባቸውም የሚል አቋም አለኝ፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ እኔ ሙሉ ለሙሉ ይዘጋ ባይ ነኝ22 ፡፡ ስለዚህ በእኔና በወንድም ዮናስ መካከል ያለው ልዩነት፣ ሙሉ ለሙሉ ይዘጋ በሚለውና23 በተወሰነ ደረጃ ደርበብ ተደርጐ ይከፈት በሚሉት መሠረታውያን ነጥቦች ላይ ያለ ልዩነት ነው፡፡ ወንድም ዮናስ ሙሉ ለሙሉ አይዘጋ፣ ሙሉ ለሙሉም አይከፈት የሚለው አማራጭ፣ ወዲህ ወዲያ እንዲያጣቅስ ሰፊ የሙግት መላወሻ ስፍራ የሰጠው ሊመስለው ይችላል፡፡ ነገር ግን ከብዙ አንጻር ደርበብ ብሎ መከፈቱ፣ ሙሉ ለሙሉ ወለል ብሎ ከመከፈት ይልቅ፣ ዝርክርክ መሆኑን ወደ መሞገቱ ልዝለቅ፡፡

 


አንደኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን ሙሉ ለሙሉ ስለከለከለ፣ ሙሉ ለሙሉ ልንከፍተው አንችልም (ኋላ እሞግትበታለሁ)፡፡ ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጒዳይ ላይ አንዳችም አስተያየት ባይሰጥ እንኳ፣ አስተያየት ያለመስጠቱ እንዳሻችሁ አድርጉት ወደሚለው ድምዳሜ እንጂ24 ፣ አድርጉት የሚለውን ፈቃድ መስጠቱን በጭራሽ አያሳይም፡፡ ሦስተኛ፣ ዘፈን አትዝፈኑ የሚለው አቋም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ቋሚ ትውፊት ነው፡፡ ትውፊቱ ደግሞ ከብዙ አንጻር ጠቀመን እንጂ አልጐዳንም—ቢያንስ ከወጪ ቀሪ ጥቅሙ አመዝኖ ተገኝቶአል25 ፡፡ አራተኛ፣ በአካሄድ ወይም በአፈጻጸም ደረጃ ሲታይ፣ በተወሰነ ደረጃ ይከፈት የሚለው ሐሳብ፣ ሙሉ ለሙሉ ይከፈት ከሚለው ይልቅ ውስብስብ ችግሮች አሉበት፡፡ ለምሳሌ ዘፈኖችን የምንገመግምበት፣ በሰዎች ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ወጥ መስፈርት ማዘጋጀት አዳጋች ስለሆነ፡፡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ዘፈኖችን ሁሉ አንድ በአንድ ገምግማ፣ በእያንዳንዱ ዘፈን ላይ መግለጫ ልታወጣ አትችልም፡፡

 


“ስለልተኰነነ መደገፉን ያሳያል”


ወንድም ዮናስ መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን አልከለከለም፤ ዘፈንን አልኰነነም የሚለውን ሙግት አስታኮ፣ ስላልተኰነነ (ስላልተከለከለ ወይም ስላልተቃወመ) ደግፏል ማለት ነው፤ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ ሙግት መሠረታዊ የሆነ የአመክንዮ ችግር አለበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ያለመኰነኑ (ያለመከልከሉ፣ ያለመቃወሙ፣ ያለማውገዙ)፣ አድርጉ የሚል ፈቃድ መስጠቱን በጭራሽ የሚያሳይ አይደለም (ኰንኗል የሚለውን ሙግቴን በቀጣይነት አቀርባለሁ)፡፡ እርሱ “አትዝፈኑ የሚል መከልክል አላኖረም” የሚል ከሆነ፣ በሌላ አንጻር ያለው ሰው ደግሞ፣ “ዝፈኑስ የሚል ፈቃድ መቼ ሰጠ?” የሚል ሙግት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የይሖዋ ምስክሮች፣ “‘ኢየሱስ አምላክ ነኝ’ አላለም፤ ስለዚህ አምላክ አይደለም” የሚል ክርክር ይገጥማሉ፡፡ እኔ ደግሞ፣ “‘አምላክ ነኝ’ ብሎ ያለመናገሩ አምላክ ያለመሆኑን የሚያሳይ ከሆነ፣ ‘አምላክ አይደለሁም’ ስላላለ፣ አምላክ ነው ማለት ነው” የሚል አጸፋ አቀርባለሁ፡፡ የእኔ ሙግት የእነርሱን ሙግት አካሄድ የተከተለ ቢሆንም፣ በሁለቱም ወገን ይህ የጥሩ ሙግት አካሄድ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን አምላክነት የሚያስተምረው በራሱ የሙግትና የትንታኔ መንገድ እንጂ፣ እኛ እንዲልልን በፈለግነው መንገድ አይደለምና፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ አልከለከለም ማለት ፈቅዷል ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባዋል፡፡ ወንድም ዮናስ ዘፈንን ይከለክላሉ በመባል የሚጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በመጥቀስ፣ አለመከልከላቸውን ከመሞገት ባሻገር፣ መዝፈንን ደግፈዋል ወደሚል ሐሳብ ሙግቱን ቀልብሶታል፤ አጡዞታል፡፡ ይህ ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ለዚህ ነው አልከለከለም የሚለው ክርክር፣ ደግፎአል ከሚለው ክርክር መነጠል የሚኖርበት፡፡ በዚህ ሒሳብ ሲታይ ወንድም ዮናስም ሆነ የእርሱን ሐሳብ የሚጋሩ ወገኖች መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን ደግፎአል የሚል አንዳችም ሙግት እንዳላቀረቡ እንዲሁም አንዳችም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንደ ሌላቸው፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ በግልጽ ሊያውቅ ይገባዋል26 ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ ወገኖች እየተጠቀሰልን ያለው፣ “ዘፈንን ኀጢአት አትበሉ” ለማለት እንጂ፣ “መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን ይደግፋል” ለማለት አይደለም፡፡“የምሁራን አስተያየት”


ወንድም ዮናስ ጐርፌ በግሪክ ቋንቋ ዕውቀታቸው የተመሠከረላቸውን ሰዎች ስለጠቀስሁ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን አለመኰነኑን ተቀበሉ ብሎናል 27፡፡ የመስኩ ምሁራንን አስተያየት ጠይቆ ሙግት ማደራጀት፣ የትክክለኛ ሙግት አካሄድ ነው 28፡፡ ወዳጄ ይህን በማድረጉ አንዳችም ቅሬታ የለኝም፡፡ የመስኩን ምሁራን አስተያየት ዐውቆ ሙግትን ማዋቀር በተመለከተ ግን፣ ልናውቃቸው የሚገቡ ቢያንስ ሦስት መሠረታውያን ነጥቦች ያሉ ይመስለኛል (ከርእሳችን ጋር በተጐዳኘ)፡፡ አንደኛ፣ በርእሰ ጒዳዩ ላይ የመስኩ ምሁራን አንድ ዐይነት አቋም አላቸው ወይስ የላቸውም የሚለው ጒዳይ በትክክል መመለስ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ሥነ ፍጻሜን አስመልክቶ የነገረ መለኮት ምሁራን አንድ ዐይነት አቋም የላቸውም፡፡ አንድ ሰው በአንዱ ወገን የተሰለፈውን ምሁር በእማኝነት በመጥቀስ ብቻ፣ የመስኩ ምሁራን ሁሉ አንድ ዐይነት አቋም አላቸው፣ ስለዚህ ሙግቴን ተቀበሉ ቢል ሙግቱ ትክክል አይሆንም፡፡ ሁለተኛ፣ ወንድም ዮናስ እነዚህ ምሁራን ሰጥተውኛል የሚለውን አስተያየት እኔ የምመለከተው በአምስት አቅጣጫ ነው:— (1) ምናልባት የሚፈልገውንና ሙግቴን ያጠናክራል የሚለውን መረጃ ብቻ መርጦ ቢሆንስ? (2) የነገሩትን ነገር በትክክል አላስተዋለው ቢሆንስ? (3) የነገሩትን መረጃ በተሟላ መልክ አልነገረን ቢሆንስ? (4) ግለሰቦቹ ተሳስተው አሳስተውት ቢሆንስ? (5) የነገሩትን መረጃ በትክክል አልተነተነው ቢሆንስ? እነዚህን አማራጭ ትንታኔዎች የማቀርብበት፣ አጥጋቢ ምክንያት አለኝ (ከሦስተኛው ነጥብ በኋላ ያለውን ትንታኔ ይመለከቷል)፡፡ ሦስተኛ፣ አስተዳደጋችን በቅዱሳት መጻሕፍት አተረጓጐማችን ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ማወቅ ይኖርብናል፡፡ በዚህ ረገድ አንድ ናሙና ላቅርብ፡፡ ከተለያየ የሕይወት ተሞክሮና ከተለያየ አገር የመጡ ወጣቶች፣ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ዐሥራ አምስት ላይ የሚገኘውን ጠፍቶ የተገኘውን ልጅ ታሪክ አንብበው፣ ያነበቡትን ታሪክ በትረካ መልክ እንዲያቀርቡት ተደረገ፡፡ የሚያስደንቀው ነገር ከአፍሪካ የመጡት ወጣቶች በሙሉ፣ ልጁ በመራቡና በመቸገሩ ጒዳይ ላይ ትልቅ ትኵረት ሰጥተው ሲናገሩ፣ ከሰሜን አሜሪካ የመጡት ወጣቶች መኻል ግን አንድም ሰው ልጁ የመራቡን ጒዳይ አልጠቀሰም29 ፡፡ ይህ ክሥተት አንድ ትልቅ ቊም ነገር የሚያስጨብጠን ይመስለኛል፡፡ ይኸውም አስተዳደጋችን፣ በቅድመ ግንዛቤያችንና በአተያያችን ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው የሚያስተምር ነው፡፡ ወንድም ዮናስ ጥያቄ ያቀረበላቸው ሰዎች አብዛኞቹ ከምዕራቡ አገር የመጡ መሆናቸው፣ አንዳንድ መረጃዎችን እኛ ኢትዮጵያውያን ባየንበት መልክ እንዳያዩ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ሁሉም ባይሆኑ እንኳ፣ በምዕራቡ ዓለም ያሉ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ዘፈንን እንደ ኀጢአት አይመለከቱም 30፡፡ ይህ አመለካከት ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት የገባ የለዘብተኝነት ጅኒ ነው፡፡ ስለዚህ መጠየቅ ያለብን ጥያቄ፣ “እናንተ ኢትዮጵያውያን ከምንባቡ አየነው የምትሉት መረጃ በርግጥ በክፍሉ ውስጥ አለ?” የሚለው እንጂ፣ “ምዕራባውያኑ ስላላዩ፣ እናንተም ልታዩ አትችሉም” የሚለው ሊሆን አይገባውም፡፡ ለዚህም ነው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን፣ ነገረ መለኮት ዓለም ዐቀፋዊም ሆነ ቀዬአዊ ውበት አለው የሚሉት፡፡ ያየነውን መረጃ ምዕራባውያኑም ሊያዩትና ሊቀበሉት በሚችል መልክ ላብራራ፡፡

 

“ኮሞስ ዘፈንን አያካትትም”


ነገሩ እንዲህ ነው— የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒሞች፣ “ዘፈን” ብለው የተረጐሙት፣ ግሪኩ “ኮሞስ” (κῶμος) የሚለውን ቃል ነው31፡፡ ይህን የግሪክ ቃል፣ የግሪክ መዝገበ ቃላት ሦስት አማራጭ ትርጒሞች አቅርበውለታል (ሮሜ 13÷13፤ ገላትያ 5÷21፤ 1ጴጥሮስ 4÷3)፡፡ አንደኛው፣ ቅጥ ያጣ፣ ኢሥነ ምግባራዊ የሆነ፣ ከአውስቦት/ከወሲብ ጋር የተገናኘ፣ በአልኮል መጠጥ የተደገፈ ጭፈራ 32፡፡

ሁለተኛ፣ በአረማውያን የጣኦት አምልኮ ወቅት የሚካሄድ ጭፈራና ዜማ33 ፡፡ ሦስተኛ፣ የመንደር ክብረ በዓል፤ ታላቅ ደስታ፣ ፈንጠዝያ ፡፡ 34
ወንድም ዮናስ “ኮሞስ” (κῶμος) የሚለው የግሪክ ቃል፣ ሁለት ትርጒሞች እንዳሉት ቢጠቅስም (አንደኛውና ሁለተኛው ትርጒም)፣ የእርሱ ዐላማ ከዳር የሚደርሰው ግን፣ ቃሉ በመጀመሪያው ትርጒሙ ብቻ ጥቅም ላይ ከዋለ ነው፡፡ ነገር ግን አንደኛውና ሦስተኛው ትርጒም ከእርሱ አቋም ጋር በቀጥታ ይቃረናሉ፡፡ በቅድሚያ አንደኛውን ትርጒም እንመልከት፣ “ቅጥ ያጣ፣ ኢሥነ ምግባራዊ የሆነ፣ ከአውስቦት/ከወሲብ ጋር የተገናኘ፣ በአልኮል መጠጥ የተደገፈ ጭፈራ” 35፡፡ “ቅጥ ያጣ” የሚለው ገለጻ፣ “ቅጥ ያው ዘፈን አለ እንዴ?” የሚለውን ትርጒም ይጭራል፡፡ ለእኔ ብዙ ግልጽ ስላልሆነ፣ ለውይይታችንም ብዙ እርባና ያለው ስላልመሰለኝ ብናልፈውስ? “ኢሥነ ምግባራዊ የሆነ” የሚለው ቃል፣ ከክርስትና ሥነ ምግባር ጋር የሚቃረኑ ብዙ ዘፈኖችን ከመስመር የሚያስወጣቸው ይመስለኛል፡፡ ከአውስቦት/ከወሲብ ጋር የተገናኘ የሚለው ሐረግ ደግሞ፣ ሰማንያ በመቶ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ዘፈን ዶግ ዐመድ ያደርገዋል (ያራግፈዋል) 36፡፡ የአገራችን አብዛኛው ዘፈን የተቃራኒ ጾታን ፍቅር ታሳቢ ያደረገ መሆኑ የሚያከራክረን አይመስለኝም፡፡ “በአልኮል መጠጥ የተደገፈ” የሚለው ሐረግ ደግሞ፣ ዘፈን በአልኮል መጠጥ መታገዝ እንደሌለበት የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የምሽት ጭፈራ ቤቶች ይዘጉ የሚል ዐዋጅ ዐይነት ነው፡፡

 


ሁለተኛው ትርጒም ብዙ የሚያከራክረን ስላልሆነ ወደ ሦስተኛው ትርጒም እንዝለቅ፣ “የመንደር ክብረ በዓል፤ ታላቅ ደስታ፣ ፈንጠዝያ”፡፡ ይህ ለወንድም ዮናስም ሆነ “እየተመረጥ ይዘፈን” ለሚሉ ወዳጆቼ ሁሉ የራስ ምታት ነው ፡፡37 ምክንያቱም ማናቸውንም ዐይነት ፈንጠዝያዎች ወይም ደስታ የማግኛ ጥረቶች ሁሉ ፉርሽ ስለሚያደርጋቸው፡፡ ሙዚቃ ለፊሽታ እንዳይውል ከከለከለ፣ እንግዲያው ምን ቀረልን? ለአምላክ ጥዑመ ዝማሬ ከማቅረብ በስተቀር አንዳችም ምርጫ ያለን አይመስለኝም፡፡

 


ወንድም ዮናስ በዋነኝነት ሊታይልኝ የሚገባው ሁለተኛው ትርጒም ብቻ ነው የሚል ክርክር አለው (አንደኛው ትርጒም ደግሞ በደምሳሳው)፡፡ ይህን አካሄድ የመረጠው ሌሎቹ ትርጒሞች ጥረቱን ሁሉ መና ስለሚያስቀሩበት ይመስለኛል፡፡ እኔ ደግሞ አንደኛውና ሦስተኛው ትርጒሞች በአንክሮ ይታዩልኝ እያልሁ ነው (ዐላማዬን ቤቱ ስለሚያደርሱልኝ)፡፡ እርሱ “ኮሞስ” (κῶμος) የሚለው ቃል፣ እኛ በመደበኛው አነጋገር ዘፈን ብለን የምንጠራውን ቃል የሚወክል አይደለም ከተባለ፣ እኔ ደግሞ እነዚህኑ መዝገበ ቃላት ጠቅሼ (በተለይ አንደኛውንና ሦስተኛውን ትርጒም)፣ “ነው እንጂ ጐበዝ!” ብል፣ የዳኝነት ፍርዱ እንዴት ሊሰጥ ይችላል?

 


ወገኖቼ በዚህ ረገድ ያለው የዳኝነት ፍርዱ እንዴት ይሰጥ፣ የሚለው ጒዳይ እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ የአንድን ቃል አማራጭ ትርጒም የሚወስነው ቃሉ የሚገኝበት ዐረፍተ ነገር ወይም ዐውድ እንደ ሆነ ቅቡል ነው፡፡ በዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ቃላት አሻሚ ትርጒም ሲኖራቸው፣ በዋነኝነት የምንጠቅሰው ቃሉ የሚገኝበት ዐውድ ወይም ዐረፍተ ነገር የሚያቀርቡትን ማብራሪያ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ቃል የሚገኝባቸው ዐውደ ምንባቦች ሁሉ (ሮሜ 13÷13፤ ገላትያ 5÷21፤ 1ጴጥሮስ 4÷3) 38፣ ቃሉን ይጠቀሙ እንጂ፣ ቃሉ በየትኛው ትርጒሙ ጥቅም ላይ መዋል አለብት የሚለውን ጒዳይ ለመወሰን የሚያስችል ፍንጭ አልሰጡንም (የእኔንም ሆነ የወንድም ዮናስን የአማራጭ ትርጓሜ መረጣ ለማጽደቅ የሚያስችል አቅጣጫ ጠቋሚ ማለቴ ነው) ፡፡39 ግራም ነፈሰ ቀኝ ወንድም ዮናስ የጠቀሳቸውን ክፍሎች እንዲሁም መዝገባ ቃላት ጠቅሼ አትዝፈኑ ወይም ዘፋኝነት ኀጢአት ነው ማለት የሚከለክለኝ አንዳችም ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ለቃሉ የቀረቡለት አማራጭ ትርጒሞች እኛ ዘፈን ብለን ከምንጠራው ቃልና ሐሳብ ጋር የሚጓደኙ ናቸውና፡፡ የመልእክቶቹ ቀዳማይ ተደራስያን ወይም የመልእክቶቹ ጸሓፍያን በአካል ተገኝተው፣ “እኔ ማለት የፈለግሁትና ክፍሉንም መተርጐም የሚጠበቅባችሁ በዚህ ትርጒሙ ብቻ ነው” የሚል ማሳሰቢያ ካልሰጡን በስተቀር፡፡ ልብ በሉ እነዚህን ሦስት አማራጭ ትርጒሞች ያገኘነው ስመ ጥር ከሚባሉትና በነገረ መለኮቱ ዓለም ሙሉ ተቀባይነት ካላቸው መዝገበ ቃላት ነው፡፡ እነዚህ መዝገበ ቃላት ደግሞ የሐዲስ ኪዳን ጸሓፍያን ጽሑፋቸውን በሚጽፉበት ወቅት ቃሎቹ የነበሯቸውን ትርጒሞችና የያዙትን አማራጭ ትንተናዎች የሚያገልጹ ናቸው ፡፡40 ስለዚህ ዘፈንን ለመኰነን እነዚህ ጥቅሶች አያስሄዷችሁም የሚባልበት አንዳችም ምክንያት የለም ፡፡41

 

አንባቢዎቼ እንዲረዱልኝ የምፈልገው አንድ ቊም ነገር አለ፡፡ ይኸውም በእማኝነት የጠቀስኋቸው የግሪክ መዝገበ ቃላት፣ “ኮሞስ” የሚለውን ቃል የፈቱልን፣ “የሐዲስ ኪዳን ጸሓፍት ጽሑፋቸውን በሚያጠናቅሩበት ጊዜ፣ ቃሉ ምን ትርጒም እንዲሸከምላቸው ፈልገው ነው? የመልእክቱ ቀዳማይ ተደራስያንም ቃሉን ሲያነቡ በአእምሮአቸው የሚያቃጭለው ትርጒም ምንድን ነው?” የሚለውን መሠረታዊ ጭብጥ ታሳቢ አድርገው ነው፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ እነዚህ አማራጭ ትርጒሞች በዋዛ ፈዛዛ ሊታዩ አይገባም፡፡ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ እነዚህ ሦስት ትንተናዎች “ኮሞስ” የሚለውን ቃል በትክክል ባይወክሉ ኖሮ፣ በአማራጭነት በአማራጭ ትንታኔ ውስጥ አይካተቱም ነበር፡፡

 


ወንድም ዮናስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዘፈን” የሚለው ቃል ተቀይሮ ሁለተኛው አማራጭ ትርጒም ብቻ ተብራርቶ ይቀመጥልኝ/ይጻፍልኝ እያለ ነው፡፡ ቊም ነገሩ ግን ቃሉ ሳይሆን ቃሉ የወከለው ሐሳብ ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡ “ዘፈን” የሚለው የአማርኛ ስያሜ አያስፈልግም ከተባለ፣ ሁለተኛው ትርጒም ተብራርቶ ይቀመጥ እንደ ተባለው ሁሉ፣ አንደኛውና ሦስተኛው ትርጒም ተብራርቶ ይቀመጥ የማልልበት ምክንያቱ ምንድን ነው? 42 አንደኛውና ሦስተኛው ትርጒም ደግሞ እኛ ዘፈን የምንለውን ቃል ለመወከሉ የሚያጣላን አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም አብዛኞቹ የ“ኮሞስ” (κῶμος) አማራጭ ትርጓሜዎች፣ ክርስቲያኖች በጭፈራ ቤት እንዲገኙም ሆነ፣ በጭፈራው ቤት ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያ እንዳይጫወቱ አጥብቆ ይከለክላል (ጐበዝ አማራጭ ትርጓሜዎቹ ሁሉ በርጋታ ይታዩልኝ)፡፡ ይከለክላል ስል ፍጹም ይከለክላል ማለቴ እንጂ፣ እየመረጡ ይዝፈኑ እየመረጡ ይሞዝቁ የሚለውን አያሳይም፡፡ በዚህ ሂሳብ ሲታይ፣ ወንድም ዮናስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓምያን፣ የነገረ መለኮት ሰዎች፣ አንዲሁም የቤተ ክርስቲያን መምህራን አሳስተውናል የሚለው መሪር ክሱ፣ ፍጹም ፍትሓዊ አይደለም፡፡ እንዲያውም እውነቱ፣ እርሱና ባልንጀሮቹ፣ ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ እያሳሳቱ ነው (ይህን የሚያደርጉት ግን ባለማወቅ ይመስለኛል)፡፡ እንግዲያው ወገኖቼ ይህ የሙግት አካሄድ በደንብ ከገባችሁ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን ይከለክላል ብላችሁ መስበክም ሆነ ማስተማር ሙሉ መብታችሁ ነው፡፡ ድሮም እያደረጋችሁት ነበር፣ አሁን ደግሞ ከሙሉ ዕውቀት ጋር ቀጥሉበት፡፡ ይህን ማድረጋችሁ ከመጽሐፉም ሆነ ከሊቃውንቱ ጋር መስማማታችሁ የሚያሳይ ነው፡፡ ዘፈን ኀጢአት ነው፡፡ አራት ነጥብ ፡፡43

 


የኮይኔ ግሪክ መዝገበ ቃላት “ኮሞስ” የሚለውን የግሪክ ቃል፣ “በአረማውያን የጣኦት አምልኮ ወቅት የሚካሄድ ጭፈራና ዜማ”44  በሚለው ትርጒሙ ብቻ አልተረጐሙትም፡፡ እንዲያ ተርጒመውት ብቻ ቢሆን፣ የወንድም ዮናስ ክርክር ሚዛን የደፋ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ “ቅጥ ያጣ፣ ኢሥነ ምግባራዊ የሆነ፣ ከአውስቦት/ከወሲብ ጋር የተገናኘ በአልኮል መጠጥ የተደገፈ ጭፈራ” 45 እንዲሁም “የመንደር ክብረ በዓል፤ ታላቅ ደስታ፣ ፈንጠዝያ” 46 ብለው ነው የተረጐሙት፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁ፣ እኛ ዘፈን የምንለው ከአውስቦት/ከወሲብ ጋር የተገናኘውን ጭፈራ አይደለም እንዴ? በቡድን ሆኖ ለፌሽታ የሚደረግ ጭፈራ/ዜማ አይደለም እንዴ? (በመሠረቱ ጭፈራዎች ሁሉ ዐላማቸው ከፊሽታ ውጪ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?) ይህ ዐይነቱ ግብር በመጽሐፍ ቅዱስ ከተኰነነ፣ ዘፈን በመጽሐፍ ቅዱስ ተኰንኗል የማንልበት ምክንያቱ ምንድን ነው (ሮሜ 13÷13፤ ገላትያ 5÷21፤ 1ጴጥሮስ 4÷3)?

 

“ናይት ክለብ ጥሩም ነው! መጥፎም ነው!”


ወንድም ዮናስ፣ “የምሽት ጭፈራ ቤቶች ጥሩም ናቸው መጥፎም ናቸው” የሚል ሙግት አለው፡፡ ጥሩ የሚያደርገው ተመርጦ መዘፈኑ፣ መጥፎ የሚያደርገውም ተመርጦ ያለመዘፈኑ እንደ ሆነ ማብራሪያ አቅርቧል47 ፡፡ በአንጻሩ ክርስቲያን ሙዚቀኞች (ይኸውም ሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወቱም ሆነ፣ መረዋ ድምፅ ያላቸው ቮካሊስቶች)፣ ለዳንኪራ የማይመቹ እንዲሁም ከክርስቲያናዊው ሥነ ምግባር ጋር የሚጣጣሙ ወይም የእንደ ቤትሆቨን ያሉ በሙዚቃ ብቻ የተቀነባበሩ የሙዚቃ ስልቶችን በናይት ክለብ መጫወት ይኖርባቸዋል የሚል አስተያየት ሰጥቶአል ፡፡48 ግን ጥያቄዎች አሉኝ:— (1) “በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዐይነት ጭፈራ ቤቶች አሉን?” (ማለትም ተመርጦ የሚዘፈንባቸውና ተመርጦ የማይዘፈንባቸው፤ በሕዝብ ጭፈራ መኻል መራጩ ባለሥልጣንስ ማነው?)፣ (2) “ይህን የሙዚቃ ሥልት፣ መሸታ በሚሸመትባቸው የምሽት ጭፈራ ቤቶች ውስጥ ማካሄድ ለምን አስፈለገ (“ፉት” ለማለት እንዲመች ካልሆነ በስተቀር፡፡ የምሽት ጭፈራ ቤቶቹ ደግሞ ዋና ምናልባትም ብቸኛ ገቢያቸው የአልኮል መጠጦችን መሸጥ አይደለም እንዴ? አልኮል መጠጥ የማይሸጡ ከሆነ፣ ትርፋቸው ምን ሊሆን ይችላል)? (3) በርግጥ ቅምቀማንና ጭፈራን ታሳቢ ካላደረግን፣ ይህ ዐይነቱን የሙዚቃ ምሽት በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳናካሂደው የሚከለክለን ነገር ምንድን ነው? ማድረግ የምንችል ከሆነ ናይት ክለብ ለምን በአማራጭነት ይቀርባል?” (4) “አንዱን ዘፈን ከሌላው ዘፈን የምንመርጥበት ቋሚና ሁሉን የሚያግባባ መስፈርት ማዘጋጀት ይቻላልን?” ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ መስፈርቱን ይቀበል ዘንድ፣ ዘፈን ኀጢአተ ያለመሆኑን ካመነ በኋላ በግምገማ በመስፈርቱ ላይ መወያየትም ሆነ መተማመን ይኖርበታል፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ በርግጥ በዚህ ጒዳይ ሕዝበ ክርስቲያኑን ሁሉ የሚያቅፍ ጉባኤም ሆነ ሱባኤ ማደራጀት ይቻላል? እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች በሌሉበት ሁኔታ፣ “እየተመረጠ በሚዘፈንበት ቦታ የሙዚቃ ተጫዋቾቻችንም ሆኑ ድምፀ መረዋዎቹ (ቮካሊስቶቹ) ሄደው ሙዚቃ ይሥሩ” የሚለው ነገር ትክክል ነውን? ድፍረት ካልሆነብኝ በስተቀር ወንድም ዮናስም ሆነ እርሱን የሚደግፉ ወገኖች የሚናገሩትን ነገር ቊጭ ብለው እስከ ጥግ ድረስ የመረመሩት አይመስልም (ዘፈን ከጸደቀልን በኋላ በዝርዝር ጒዳዮቹ ላይ እንወያያልን ለማለት የፈለጉ ይመስላል፡፡ ነገር ግን እንዝፈን አንዝፈን ከሚለው የክርክር ጭብጥ ይልቅ፣ ዝርዝር ጒዳዮቹና አፈጻጸሞቹ ይመልጥ ራስ ምታት እንደ ሆኑ ሊገነዘቡት ይገባል)49 ፡፡“ችግር የለም እየመረጣችሁ ዝፈኑ”

ምናልባት አንዳንድ ወገኖች፣ “ከእኛ ሥነ ምግባር ጋር የሚጣጣሙ፣ በአንጻሩ አንዳችም የአውስቦት መንፈስ የሌለባቸው፣ ዘፈኖችስ እንዴት መታየት አለባቸው?” የሚል ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ይህ የአንድ ሚሊዮን ብር ጥያቄ ነው፡፡ ወንድም ዮናስ ጐርፌም እየመረጥን እንድንዘፍን ሐሳብ አቅርቦልናል፡፡ ይህ አስተያየቱ ከሥነ ምግባራችን ጋርም ሆነ ከነገረ መለኮታችን ጋር የሚጣጣሙ ዘፈኖች መኖራቸውን አጣቅሶ ነው (ለምሳሌ ስለ እናት ፍቅር፣ ስለ አገር ፍቅር፣ ስለ ባልንጀርነት፣ ቀጠሮን ስለማክበር፣ ስለታማኝነት ወዘተረፈ)፡፡ ሥነ ምግባራችንን የሚጋሩ፣ ነገር ግን እንደ አስቴር መጽሐፍ የአምላክ ስም የሌለባቸው በርካታ ጥሩ ዘፈኖች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ዘፈኖች የማንዘፍንባቸው ቢያንስ ሰባት መሠረታውያን ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው፣ ይህ ዐይነቱን ዘፈን መዝፈን የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት አይደለም፡፡ ቈይ! ትውፊት ምንድን ነው? ትውፊት ማለት ከእኛ ውጭ ያለ፣ የጥንት አባቶች ይከተሉት የነበረ ሕግ ማለት ነው? መልሱ በተወሰነ መልኩ አዎ፣ በተወሰነ መልኩ ደግሞ አይደለም የሚል ነው፡፡ ትውፊት እኛ ነን፡፡ አስተዳደጋችን፣ አስተምህሮአችን፣ አተያያችን፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የሐዘን አገላለጽ ዘዬአችን፣ የሙሾ አወራረዳችን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ባህልና ልማድ ነው፡፡ እንዲያው በአጭሩ የአኗኗር ቅኝታችን ነው፡፡ ለዚህ ነው የሥነ ሰብ ምሁራን፣ “ሰው ሁሉ የባህሉ እስረኛ ነው” የሚሉን፡፡ ይህን ጒዳይ ያብራራልኝ ዘንድ፣ አጭር ሐሳብ ወለድ ብጠቀምስ?

 


እኔና ባለቤቴ የወር አስቤዛ ልንገዛ በሄድንበት ገበያ፣ ለትንሹ ልጃችን የሚሆን መልኩ ያማረ ፖፖ በጥሩ ዋጋ አገኘን፡፡ ከገበያ የተመለስነው ግን በጣም ደክሞን ነበር፡፡ ትላንት ራት የተበላባቸው ሳሕኖች አይታጠቡ እንጂ፣ ከራት የተረፈ እጅ የሚያስቈረጥም የዶሮ ወጥ በሸክላ ድስቱ ውስጥ አለ፡፡ ባለቤቴ ይህን የዶሮ ወጥ ስታሞቅ፣ እኔ “የምንበላበትን ሳሕን እጠብ” የሚል የሥራ ድርሻ ተሰጠኝ፡፡ ነገር ግን ድካሙ በርትቶብኝ ስለነበር በተቀመጥሁበት እንቅልፉ ለሽ አደረገኝ፡፡ ከዛ ጣፋጭ እንቅልፍ የቀሰቀሰኝ፣ “ሳሕኖቹ ታጠቡ?” የሚለው ንግግር ነው፡፡ ዐይኔን ስከፍት ወዲያው አንድ መላ አብሮ ከች አለልኝ፣ “ባልታጠበ ሳሕን ከምንበላ፣ የጆጆን50 ፖፖ በሳሕንነት ብንጠቀምስ”፡፡ “በስመ አብ በፖፖ፤ ፖፖ ነው ያልኸው? እንዴት ምግብ በፖፖ ይበላል? ስንፍናህ ወደር አይገኝለትም፤ በቃ ተወው ቢያንስ አንድ ሳሕን ለቅለቅ አድርጌ ላንጣ” አለች፡፡ “እንዴ ምን ችግር አለው የእኔ እመቤት፤ በአሁኑ ወቅት ቤታችን ውስጥ ካሉ ሳሕኖች ሁሉ ይህ ፖፖ ንጹሕ እንደ ሆነ እንኳን እኛ ጆጆ ራሱ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ከዛሬ በኋላ መደበኛ ሥራውን ይጀምራል፣ ዛሬ ግን ንጽሕናውን ምክንያት በማድረግ፣ የሳሕን ወግ ብናሳየውስ?” አልኋት፡፡ ባለቤቴ፣ “ኧረ እንዴት አድርገን በፖፖ እንበላለን” ስትል በመኅተሟ ጸናች፡፡ እኔ ደግሞ የፖፖውን ንጽሕና በመጥቀስ፣ ያለማወቋን በመውቀስ እንዲበላበት ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፍሁ፡፡ እንዲያውም ይህን ማድረጋችን ዘመናዊ ሰዎች መሆናችንን፣ የተማርን የተመራመርን መሆናችንን ያሳያል ስል ሞገትሁ፡፡ እንደ ወትሮው ሁሉ ባለቤቴ በሙግቴ ስለተረታች፣ ፖፖውን የምግብ ጠረጴዛው ላይ አድርጋው እንጀራውን አነጠፈችበት፡፡ ወጡንም አወጣችበት፡፡ ሁለታችንም እጃችንን ታጥበን ቀረብን፡፡ እኔ፣ የምንበላው በፖፖ ነው የሚለውን ጒዳይ በጭራሽ ማሰብ አልፈለግሁም፤ ፖፖነቱን ካድሁ፡፡ ባለቤቴ ግን፣ “ይህ ነገር የሚሆን አልመሰለኝም፤ እኔ አላደርገውም አሁን የሚታየኝ ዶሮ ወጥ ሳይሆን…አለች”፡፡ እኔም “ካፈርሁ አይመልሰኝ” ሆኖብኝ እንጂ፣ ሽቅብ ሽቅብ እያለኝ ነበር፡፡

 

ለምንድ ነው በፖፖ ያልበላነው? መልሱ አጭር ነው፤ ፖፖ በእኛ ባህል የምግብ መብያ ሳሕን አይደለም፡፡ ቤት ውስጥ ካሉ ሳሕኖች ይልቅ ንጽሕ አይደለም እንዴ? ምንም ጥያቄ የለውም ንጹሕ ነው፡፡ ነገር ግን ሳሕንን ሳሕን የሚያደርገው ንጽሕናው ብቻ ሳይሆን፣ ባህል ወይም የሕዝቡ አኗኗር ዘዬ ጭምር ነው፡፡ ቊም ነገሩ እዚህ ላይ ነው፡፡ እንኳን ነቢያት አምላክ ራሱ ክንፍ ያላቸውን መላእክት ልኮ ዘፈን “ከኮሞስ” ግላጼ ወጥቶአል ቢል፣ ቢያንስ እኔን ጨምሮ ቀደምት ክርስቲያናች ልንዘፍን አንችልም፡፡ ፖፖው ንጹሕ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥሩ ዘፈኖች እንዳሉ ቅን ልቦና ያለው ሰው ሁሉ በግልጥ የሚረዳው ጒዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ፖፖው ንጹሕ መሆኑ ለሳሕንነት እንዲያገለግል እንዳልረዳው ሁሉ፣ እነዚህ ዘፈኖች ጥሩ መሆናቸው ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ እንዲዘፍናቸው ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ እንኳን እኛ ክርስቲያኖች፣ ዓለማውያኑም የእኛን መዝፈን፣ የስምንተኛው ሺህ ምጽአት እንጂ፣ የነገረ መለኮት ለውጥ አድርገው ሊመለከቱት አይችሉም፡፡ እንዲህ የሚዋዥቅና የሚንሸራተት ሕይወትስ ይዘን፣ ወጥነት ያለውን ክርስቲያናዊ ሕይወት አብረናቸው መኖር እንዴት እንችላለን? ወንድም ዮናስ በግልጽ ያላስተዋለው ሐቅ ይሄ ይመስለኛል፡፡
ሁለተኛ፣ ልክ ነው እነዚህ መዝሙሮች ጥሩ ይዘት አላቸው፣ ነገር ግን ባለመዝፈናችን ምን ተጐዳን? ምን ጐደለብን? 51 እንዲያውም ጊዜያችን፣ ኢኮኖሚያችን ተጠብቋል (በየጭፈራ ቤት እንዲሁም ለሲዲና ካሴት ግዢ የምናወጣው ገንዘብ በኪሳችን ዐድሯል)፡፡ ሦስተኛ፣ የምናደርጋቸውን ማናቸውም ነገሮች ለእግዚአብሔር ክብር እንድናደርገው ታዘናል (1ቆሮንቶስ 10÷31፤ ሮሜ 12÷1-2) ፡፡52 ምናልባት እግር ኳስ መጫወት፣ መጽሐፍ ማንበብ ወዘተ ለእግዚአብሔር ክብር እንዴት ሊውሉ ይችላሉ? የሚል ካለ መልሱ አጭር ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንንና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነውን አካላችን ጤነኛ እንዲሆን፣ አእምሮአችንን ንቁ እንዲሆን አምላክ ይፈልጋል፡፡ ስፖርት መጫወትም ሆነ መጻሕፍትን ማንበብ መንፈሳዊ ፋይዳቸው እዚህ ጋ ነው፡፡ አራተኛ፣ እየመረጡ መዝፈን እጅግ ሲበዛ ውስብስብ መሆኑን ወንድም ዮናስ በቅጡ የተረዳው አልመሰለኝም፡፡ መስፈርት ማዋቀሩ አስቸጋሪ የመሆኑን ያህል፣ ጒባኤ ጠረቶ፣ አገር ሰብስቦ፣ “የትኛውን ዘፈን እንዝፈን? የትኛውን ደግሞ አንዝፈን?” የሚለውን ጒዳይ መገምገም፣ ትልቅ አበሳ፣ ትልቅ አሳር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ዘፈንን፣ መዝሙርን እንኳ በቅጡ ለመገምገም ጊዜ አግኝታ አታውቅም፡፡ ከዚህ ሁሉ ዝርክርክ አካሄድ ሁሉን ዘግቶ መቀመጡ የተሻለ ነው፡፡

 


አምስተኛ፣ በሩን አንገርብበን (ደርበብ አድርገን) ከከፈትነው፣ “ምን ያህል ይከፈት?” “ምን ያህልስ ይዘጋ?” በሚለው ኅሊናዊ ፍርድ ከምንወዛገብ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት፣ ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ስለዚህ አማራጩ አንገርብቦ (ደርበብ አርጐ) መክፈት ሳይሆን፣ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት ነው፡፡ መቼም ሙሉ ለሙሉ ይከፈት የሚለውን ጒዳይ ወንድም ዮናስ ራሱ አይስማማበትም፡፡ ምክንያቱም በርካታ ኢሥነ ምግባራዊ የሆኑ፣ ከነገረ መለኮታችን ጋር በቀጥታ የሚጻረሩ ትምህርቶች ስላሉ፡፡ ለዘመናት ዘግተን መቀመጣችን አንዳችም ነገር ካልጐዳን፣ ሕዝባችንም ይህን አሜን ብሎ ከተቀበለው፣ እንዲያውም ይህ የሙሉ ለሙሉ ማዕቀብ አካሄድ፣ ኢኮኖሚያችንንና ጊዜያችንን ከታደገልን፣ ጠቃሚውን ነገር ከማይጠቅም ነገር ጋር ሳይሆን ጠቃሚውን ነገር ከሚጐዳ ነገር ጋር እያነጻጸርነው ነው ማለት ነው፡፡

 


ስድስተኛ፣ የምሽት ጭፈራ ቤቶች ተመርጠው የሚዘፈንባቸው ቦታዎች አይደሉም ፡፡53 ይህ እውነት ከሆነ ወንድም ዮናስ ሙዚቀኞቻችን ናይት ክለብ ሄደው ይጫወቱ የሚለን ለምንድን ነው? በአንድ ወቅት ለወንድም ዮናስ፣ “ክርስቲያን ሙዚቃ ተጫዋች የጭፈራ ቤት ታዳሚዎቹ፣ ዘፈኑን ወደ ወሲብ ቢያንደረድሩት ምን ሊያደርግ ይችላል?” የሚል ጥያቄ ጠይቄው ነበር፡፡ “ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ከተፈጠረ ክርስቲያኑ ጊታሩን አስቀምጦ መሄድ አለበት” የሚል ምላሽ ሰጥቶኛል ፡፡54 ምላሹ አላሳመነኝም፤ ምክንያቱም ይህ አካሄድ አስጀምሮ ሳያስጨርሱ መሄድ ነውና፡፡ በተረፈ የጭፈራ ቤቱን ታዳሚዎች በዚህ መልክ ማስቀየም ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ቦታው ለእኔ የሚመጥን አይደለም በማለት፣ ከጅምሩም ወደዚያ ስፍራ ዝር ያለማለት፣ ከሄደም ደግሞ ሙሉ ክብሩን ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለውንም አበሳ መጠጣት፣ ፍዳውን መብላት ይኖርበታል፡፡ ሰባተኛ፣ ክርስቲያን ዘማርያን ቀጠሮ ስለማክበር፣ ስለወንድማማችነት ፍቅር አስፈላጊነት፣ ስለቤተሰብ ፍቅር፣ ጠንክሮ ስለመሥራት ወዘተ (እንዲዘምሩ ማድረግ የእነዚህ ነገሮች ሁሉ መሠረት አምላካችን እግዚአብሔር እንደ ሆነ በሚያስገነዝብ መልኩ)፡፡ ችግሩ የአማራጭ መዝሙሮችን ማጣት፣ ወደ ቅልውጥና ወስዶን ከሆነ፣ መዝሙሮቹን እኛው ብናዘጋጃቸው መፍትሔ ሊሆን ይችላል ለማለት ነው ፡፡55ማጠቃለያ


አንድ የንጉሥ ልጅ፣ አንድ ዕውቅ ዘፋኝ ታገባለች፡፡ ንጉሡ ከመንበራቸው ሲገረሠሡ፣ የንጉሡ ቤተ ሰቦች ከያሉበት እየተለቀሙ ዘብጥያ ይወረወራሉ፡፡ ዘፋኙ ግን በለስ እየቀናው፣ ተወዳጅነቱ ከዕለት ዕለት እየጋመ ይመጣል፡፡ በአንጻሩ የልዑላኑ ቤተሰብ መከራና አሳር እየበረታ ይሄዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ዘፋኙና ልዕልቲቱ ተገናኝተው የተጋቡት፡፡ ትዳራቸው ግን ብዙም አልዘለቀም፤ ዘፋኙ ልዕልቲቱን በመፍታት ሌላዋን ባለሳምንት ያገባል፡፡ በአንድ አጋጣሚ የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን፣ ልዕልቲቱ ከአርቲስቱ ጋር እንዴት እንደ ተገናኙ ጥያቄ አቅርቦላት ነበር፡፡ እርሷም፣ “የተገናኘነው እርሱ ወደ ላይ ሲወጣ፣ እኔ ደግሞ ወደ ታች ስወርድ ነው” አለች ይባለል፡፡ መልእክቱ ወደ ልባችሁ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ በምንም ሂሳብ ይህ ርእስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ላይ በምትወጣበት የታሪክ ጊዜ ላይ የመጣ ጥያቄ አይደለም፡፡ በቀን ጐዶሎ፣ በድጡ መንገድ እየተንሸራተተች ባለበት የታሪክ ወቅት ያገኛት አበሳ ፍዳ እንጂ፡፡ ይህ የእንዝፈን ጥያቄ ከሃያና ከሠላሳ ዓመት በፊት ቀርቦ ቢሆን ኖሮ፣ ወንድም ዮናስም ሆነ ባልደረቦቹ እግር ከወርች ታስረው አማኑኤል ይወሰዱ ነበር ፡፡56 ዛሬ ግን ይህን እንግዳ ሐሳብ፣ አንዳችም ፋይዳ የሌለውን ትምህርት ለቤተ ክርስቲያን ለማስተዋወቅ የትውልዱ ሥነ ምግባር ፈቅዷል፡፡

 


ወንድም ዮናስ የመጽሐፉን ርእስ፣ “ቤት ያጣው ቤተኛ” ያለው በምን ሂሳብ ነው? ዘፈን የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ቤተኛ የሆነው መቼ ነው? በመጽሐፉ ሽፋን ላይ፣ አንድ ሰው ቤተ ክርስቲያን በር ላይ እንደ ጒድፍ ተጥሎ ይታያል፡፡ በእውነቱ ምን መልእክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ እንደ ሆነ በጭራሽ አልገባኝም፡፡ ባይሆን፣ “ቤት ያላገኘው ነገር ግን ቤተኛ ለመሆን የሚዋደቀው ታጋይ” ቢባል ይሰዳል/ያስሄዳል (የገላትያ 5÷21 ትርጒም ቀይሮ)፡፡ ከዚህ መለስ ግን በምንም ሂሳብ መዝፈንም ሆነ ናይት ክለብ ሄዶ ሙዚቃ መጫወት፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አስተምህሮ፣ ትውፊትም ሆነ ሥነ ምግባር አይደለም፡፡ አትዝፈኑ፣ አትጨፍሩ የሚለውን ትምህርት ከቤተ ክርስቲያን በማስወጣት፣ ባይተዋር እናደርገዋለን፤ ቤተ ክርስቲያን በር ላይ እንደ ጒድፍ እንጥለዋለን፤ ይህም መጽሐፍ የዚህ ዘመቻ አንድ አካል ነው የሚል ምፀታዊ ተምኔት ከሆነ ግን ይገባኛል ፡፡57 እኔ በዚህ ጽሑፍ ዘፈን ኀጢአት አይደለም የሚለው ሙግት ትክክል ያለመሆኑን፣ መርጠን እንዝፈን የሚለውም ሐሳብ ከብዙ አንጻር የከሰረ ሐሰብ መሆኑን፣ ከዚህ በተረፈ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቅ የሥነ ምግባር አደጋ እንደ ተጋረጠ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ በቸር ይግጠመን፡፡

 

ለአስተያየትና ለዕርማት የተላከው ረቂቅ በርካታ ስሕተቶችና ግድፈቶች ነበሩበት፡፡ ይሁን እንጂ የጽሑፉ የሙግት ጭብጥም ሆነ ድምዳሜ በጭራሽ አልተቀየረም፡፡ የአርትዖቱ አዛባ የተዛቀው በደቦ ቢሆንም፣ በጽሑፉ ላይ የሚታየው ስሕተት (ካለ ማለቴ ነው) እንዲሁም ጽሑፉ የሚያራምደው አቋም፣ የጸሓፊው ብቻ እንጂ የአስተያየት ሰጪዎቹ፣ የአርታዕያኑ ወይም ጽሑፉን ያተመው ክፍል አይደለም፡፡ በአርትዖት ሥራውም ሆነ አስተያየት በመስጠት የተባበሩኝን ወገኖች ሁሉ ከሙሉ ልብ አመሰግናለሁ:—  ወንድም ዮናስ ጐርፌ፣ ወንድም አፈወርቅ ካራ፣ ወንድም አማረ መስፍን፣ ዶ/ር ዮሴፍ መንግሥቱ፣ ወንድም ጳውሎስ ፈቃዱ፣ ወንድም መንግሥቱ ታምሬ፣ ወንድም ክሩቤል መኰንን፣ እኅት ዮዲት ኀይሉ፣ ወንድም ይግረም ረታ፣ ጋሽ ሰሎሞን ከበደ፣ ጋሽ ደጃቸው መኖር፣ ወንድም ዘላለም መንግሥቱ፣ መጋቢ ጽና ይልማ፣ ወንድም ያዕቆብ ዋዩ፣ ወንድም ዓለማየሁ ማሞ፣ ወንድም ተካልኝ ዱጉማ፣ እንዲሁም ዶ/ር ገዛኸኝ በቀለ፡፡ ለሁሉም እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ ዕድሜና ጤና ይስጥልኝ!     

 

 

 1. ለአስተያየትና ለዕርማት የተላከው ረቂቅ በርካታ ስሕተቶችና ግድፈቶች ነበሩበት፡፡ ይሁን እንጂ የጽሑፉ የሙግት ጭብጥም ሆነ ድምዳሜ በጭራሽ አልተቀየረም፡፡ የአርትዖቱ “አዛባ” የተዛቀው በደቦ ቢሆንም፣ በጽሑፉ ላይ የሚታየው ስሕተት (ካለ ማለቴ ነው) እንዲሁም ጽሑፉ የሚያራምደው አቋም፣ የጸሓፊው ብቻ እንጂ የአስተያየት ሰጪዎቹ፣ የአርታዕያኑ ወይም ጽሑፉን ያተመው ክፍል አይደለም፡፡ በአርትዖት ሥራውም ሆነ አስተያየት በመስጠት የተባበሩኝን ወገኖች ሁሉ ከሙሉ ልብ አመሰግናለሁ:— ወንድም ዮናስ ጐርፌ፣ ወንድም አፈወርቅ ካራ፣ ወንድም አማረ መስፍን፣ ዶ/ር ዮሴፍ መንግሥቱ፣ ወንድም ጳውሎስ ፈቃዱ፣ ወንድም መንግሥቱ ታምሬ፣ ወንድም ክሩቤል መኰንን፣ እኅት ዮዲት ኀይሉ፣ ወንድም ይግረም ረታ፣ ጋሽ ሰሎሞን ከበደ፣ ጋሽ ደጃቸው መኖር፣ ወንድም ዘላለም መንግሥቱ፣ መጋቢ ጽና ይልማ፣ ወንድም ያዕቆብ ዋዩ፣ ወንድም ዓለማየሁ ማሞ፣ ወንድም ተካልኝ ዱጉማ፣ እንዲሁም ዶ/ር ገዛኸኝ በቀለ፡፡ ለሁሉም እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ ዕድሜና ጤና ይስጥልኝ!
 2. መርጠን እንዝፈን መርጠን እንሞዝቅ ከሚለውም ሆነ፣ ይህን ሐሳብ አጥብቆ ከሚቃወመው ወገን ጥሩ አስተያየቶች እንደ ቀረቡ ሁሉ፣ በርካታ መስመር የሳቱ ሙግቶችና በጽርፈት የተሞሉ መቈራቈሶችን አንብበናል፡፡ ለጊዜው ኪራላይዞ (አምላክ ምሕረት ያድርግልን) ከማለት ውጪ፣ ምን ማለት እንደሚቻል አላውቅም፡፡       
 3. በጠባብ ደረት በአጭር ቊመት የሚለው ገለጻ፣ 272 ገጽ ካለው ከወንድም ዮናስ ጐርፌ መጽሐፍ ጋር በተነጻጸረ መልኩ እንደ ሆነ ልብ ይሏል፡፡ 
 4. በርካታ የደርግ ዘፈኖች ዜማቸው እየተዘረፈ፣ መዝሙር እንደ ተሠራባቸው አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ ጊዜው ይርዘም እንጂ፣ አንድ ቀን ይህ ሁሉ ጒድ ይፋ መውጣቱ የሚቀር አይመስለኝም፡፡       
 5. ምናልባትም አንዳንድ ወገኖች፣ “‘እናንተ እያልህ በዚህ መልኩ ስትገሥጽና ስትወቅስ፣ በአንጻሩ ራስህን ብጹዕ ወቅዱስ እያደረግህ አይደለም ወይ ሊሉ ይችላሉ፡፡ አይደለም፤ መናገሬ ችግሩን መጠቈሜ እንጂ፣ ራሴን ንጹሕ ማድረጌን የግድ (necessarily) የሚያሳይ አይደለም፡፡
 6. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ ምናልባት እነርሱም በርእሰ ጒዳዩ ላይ መክረው መግለጫ በማውጣት፣ እያንዳንዱ ቤተ እምነት ይህንኑ አካሄድ እንዲከተል ሊያበረታቱ ይችላሉ፡፡    
 7. ይህን ስል ግን ሁሉ ቤተ ክርስቲን ይህን ያደርጋል እያልሁ አይደለም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የሰሜን አሜሪካ ቤተ ክርስቲያናት ዘፈን ኀጢአት ነው የሚል፣ ጠበቅ ያለ አቋም አላቸው፡፡ በዚህ አንጻር ወንድም ዮናስ፣ የሰሜን አሜሪካ አብያተ ክርስቲያነት ሁሉ ዘፈንን አንደ ኀጢአት አይመለከቱትም የሚለው ፍረጃው ትክክል አይመስለኝም፡፡  
 8. ከወንድም አማረ መስፍን ያገኘሁት ነው፡፡
 9. የአንዳንድ መረጃዎች መገኘት፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትን እንዴት መተርጐም አለብን የሚለውን ጕዳይ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንደሚቀይረው ዐውቃለሁ፡፡ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ በተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ላይ የተንጠለጠለ እስካልሆነ ድረስ፣ ለውጡ መሠረታዊ የሆነ የነገረ መለኮት ለውጥ ሊያስከትል አይችልም፡፡ በሌላ መልኩ በክርስቲያናዊ ትምህርቶች ውስጥ የተለያዩ ግንዛቤዎችና የነገረ መለኮት አተያዮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከአንዱ አተያይ ወደ ሌላው አተያይ መሄድ ያለና የተለመደ አካሄድ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚሞግትበት ጭብጥ ግን፣ የአስተምህሮ ለውጡ ብቻ ሳይሆን፣ ትልቅ የሥነ ምግባር ለውጥ ማስከተሉን ልብ ይሏልያውም በመላው የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አማኝ ላይ፡፡     
 10. እውነት አንጻራዊ ናት፣ ነባራዊ የሆነ የሥነ ምግባርም ሆነ የነገረ መለኮት እውነት የለም የሚለው የድኅረ ዘመናዊነት ፍልስፍና ትውልዱን ቀንብቦ ይዞታል፡፡ እውነት ነባራዊ ካልሆነች ነገሮች የሚሰሉት ከእውነት አንጻር ሳይሆን፣ ከአዋጪነትና ከፍላጎት አንጻር ብቻ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያን መሥራት ያለባት ትልቅ የቤት ሥራ ተወዝፎ የተቀመጠ ይመስለኛል፡፡
 11. ዐበይት የሚባሉት ክርስቲያናዊ ትምህርቶች፣ ትምህርተ እግዚአብሔር፣ ትምህርተ ሥላሴ፣ ትምህርተ ሥጋዌ፣ ትምህርተ ክርስቶስ፣ ትምህርተ ድነት፣ ትምህርተ ሰብ ወዘተ ሲሆኑ፣ ደቂቃን የሚባሉት ደግሞ ከድነታችን ጋር የማይጐዳኙ (ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ያገኘነውን ድነት በተመለከተ አንዳችም ተጽእኖ የማያደርጉ) ነገር ግን በክርስቲያናዊ ትምህርትና ሥነ ምግባር ውስጥ ቦታ የተሰጣቸው ጒዳዮች ናቸው፡፡
 12. ይህ ምን ያህል እውነት ነው የሚለውን በተወሰነ ደረጃም እንኳ ቢሆን ኋላ እንመለከተዋለን፡፡  
 13. የአልኮል መጠጦችን እንጠጣ ወይስ አንጠጣ የሚለውም ክርክር፣ በይዘትም ሆነ በትንታኔው ከዚህ ርእሰ ጒዳይ ጋር ተጐራባች ነው፡፡ በዘፈን ረገድ የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናትን እንምሰል የሚለው አካሄድ፣ በዘፈን ብቻ የሚቋጭ አይደለም፡፡ ነገ እንደ ምዕራባውያኑ እንጠጣ፣ እናጭስ፣ ሰዶማውያንን በሙሉ አባልነት እንቀበል የማይባልበት ምክንያት የለም፡፡ እኛን በእነርሱ፣ መልክና አምሳል ጠፍጥፎ ባበጀት ትክክል ነው ተብሎ እስከ ታሰበ ድረስ፡፡         
 14. 30 ዓመት በቤተ ክርስቲያን ኖሪያለሁ፡፡ ባለመዝፈኔ፣ ጭፈራ ቤት ባለመሄዴ፣ ባለመጠጣቴ…ተጐዳሁ የሚል ክርስቲያን በእውነቱ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡  
 15. እኔ በዚህ ጽሑፍ ዘፈን እንዝፈን (መርጠን እንዝፈን) ወይስ አንዝፈን  ከሚለው ጒዳይ ጋር ተዛማጅ የሆኑና ክርስቲያናች ልብ ሊሏቸው የሚገባቸውን ነጥቦች እያወሳሁ ነው፡፡ ምናልባት አንዳንድ ሰዎች፣ እኔ ሙግት ስላነሰኝና የምሞግትበት ጭብጥ ሚዛን እንዲደፋ ተጐራባች የሆኑ ነገሮች ላይ ብቻ የሙጥኝ እንዳልሁ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ እኔ ዘፈን መዝፈን ትክክል ለምን እንደማይሆን አጥጋቢ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሙግት አለኝ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ጒዳዩ ከበርካታ ርእሰ ጒዳዮች ጋር እንደሚጐዳኝ ማሳየት ነገሩን ከነጓዙ ከመመልከትም ባሻገር ኀላፊነት እንደሚሰማው የቤተ ክርስቲያን መሪ የበሰለ ውሳኔ ለመወሰን ትልቅ ዕገዛ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንዲያውም በተቃራኒ ወገን ያሉ ሰዎች የጒዳዩን ፈርጀ ብዙነት በውል ያስተዋሉት አይመስለኝም፡፡         
 16. መጠጥን አስመልክቶ የሚነሣው ሙግት ከዚህ ጋር አንድ ዐይነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አትስከሩ አለ እንጂ አትጠጡ መች አለ?  ስለዚህ ቊም ነገሩ መመጠን እንጂ አለመጠጣት አይደለም? የሚል ሙግት ይቀርባል፡፡ ለዚህ ነው የሙግት አካሄዱ አንድ ዐይነት ነው ያልሁት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘፈን ባለበት ቦታ ሁሉ መጠጥ አለ፤ ዘፈንን የሚያቀርቡ መሸታ ቤቶች ሁሉ መጠጥንም ያቀርባሉ፡፡      
 17. ተሟጋቾቻችን፣ እኔ ስለዘፈን እንጂ ይህ ሁሉ ተያያዥ ጒዳይ አይመለከተኝም ይሉ ይሆናል፡፡ ይህ ግን፣ እኔ መንገዱን ልክፈት እንጂ፣ በመንገዱ ላይ በቋሚነት የሚመላለሱት እነማን ናቸው የሚለውን ሞራላዊ ጥያቄ ልጠየቅ አይገባም እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ግን ስሕተት ነው፡፡ አንድ መድኀኒት አንድን በሽታ የመፈወስ ሙሉ ብቃት ኖሮት፣ ነገር ግን በጐን ጠንቁ አማካይነት ትቶት የሚሄደው በሽታ የሚበልጥ ከሆነ፣ እጩ መድኀኒት ሆኖ የቀረበው፣ በመድኀኒትነት ሊያገለግል የሚችል አይመስለኝም፡፡ ወገኖቼ፣ ዘፈን እንኳ ጥሩ ቢሆን (ጥሩ ነው የሚል አቋም ግን የለኝም)፣ ዘፈንን ተገን አድርገው፣ ዘፈን በቀደደው በር የሚገቡ የዘፈን አጫፋሪዎች፣ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም (ወገኖቼ ዘፈንን የምናጸድቅበት አካሄድ ሌሎችን ለመኰነን ዐቅም ያሳጣናል እያልሁ ነው)፡፡ በዚህም አካሄድ ነው አብዛኞቹ የምዕራብ አገሮች ሁሉን አጽድቀው የተቀመጡት፡፡       
 18. ኀይሌ፣ ኀይሌ ገብረ ሥላሴ…ቀነኒሳ አንበሳወይም ባልቻ አባነፍሶ የሚለውን የቴዲ አፍሮ ዘፈኖችን ያስታውሷል፡፡     
 19. መሠረት ከሌለው ደግሞ፣ ማዕቀብ መደረግ አለበት የሚላቸው ጒዳዮች ኅሊናዊ እንጂ ነባራዊ ሊሆኑ አይችልም፡፡
 20. እርሱም ሆነ የእርሱን ሐሳብ የሚጋሩ ሰዎች፣ የመረጣው በስፈርት እንዴት መካሄድ እንዳለበት አልነገሩንምገቢር እንሥራለት ብንል እንኳ፡፡ 
 21. ኋላ በዚህ ጒዳይ ላይ እተቻለሁ፡፡           
 22. ምናልባት ብሔራዊ መዝሙሮችና ጀግኖችን ለማሞካሸት ለሚዘፍኑ ሰፈኖች በሩ እጅግ በጠባበ መልኩ (በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ብቻ) ሊከፈት ይገባል የሚለውን ጒዳይ፣ ቤተ ክርስቲያን መግለጫ ልታወጣበት ወይም ማዕቀብ ልታኖርበት ትችላለች፡፡
 23. ብሔራዊ መዝሙሮችን መዘመር ስሕተት ነው ብዬ አላስብም፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያን አቋም ብታወጣ ያወጣችውን አቋም፣ አቋሜ ለማድረግ ሙሉ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ 
 24. እንዳሻን ለማድረግም ቢሆን፣ ቢያንስ የአዋጪነት ሙግት ሊቀርብለት ይገባል፡፡
 25. ጥቅሙና ጒዳቱን የሚወስነው መላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ እንጂ፣ እኔም ሆንሁ ወንድም ዮናስ ጐርፌ አይደለም፡፡
 26. ክርስቲያኖችም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን ኰንኖአል ለማለት የሚጠቅሷቸውን ጥቅሶች፣ ወንድም ዮናስም ሆነ የእርሱ የትግል አጋሮች እነዚያኑ ጥቅሶች በመጥቀስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን ደግፎአል ወደ ማለት ሲንደረደሩ ታዝበናል፡፡ መርጠን እንዝፈን፣ መርጠን እንሞዝቅ ለማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀስ ጥቅስ የለም፡፡     
 27. በመጽሐፉና በፊስቡክ ገጹ ላይ፡፡
 28. ይህ ሕግ ሲሳት፣ “Appeal to Unqualified Authority” የሚባለው ተፋልሶ ይከሠታል፡፡      
 29. ሥነ ትርጓሜን አስመልክቶ በቅርብ ጊዜ ታትሞ ለንባብ ከሚቀርበው ከወንድም ምኒልክ አስፋው መጽሐፍ ያገኘውት ሐሳብ ነው፡፡ ወንድም ምኒልክ ምንጩን በትክክል ስላሰፈረ፣ ምንጩን ከምንጩ እንድታመሳክሩልኝ እጠይቃለሁ፡፡       
 30. ወንድም ዮናስ የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ዘፈንን ኀጢአት አድርገው እንደማይመለከቱት ገልጾአል፡፡ ይህ ሚዛናዊ ንግግር አልመሰለኝም፡፡ ብዙ የሰሜን አሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት ለምሳሌ አብዛኞቹ ጴንጤቈስጣውያን፣ ጒባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንና ሜኖናይቶች ዘፈን ኀጢአት ነው ባዮች ናቸው፡፡ በመሠረቱ ሁሉም የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ኀጢአት አይደለም ቢሉ እንኳ፣ እኛ ማለት የለብንም ወደሚለው ድምዳሜ ሊያመጣን አይችልም፡፡ አንደኛ፣ መሠረታችን ቃለ እግዚአብሔር እንጂ እነርሱ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ግብረ ሰዶማዊነት በበርካታ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ ስለዚህ ግብረ ሰዶም በመጽሐፍ ቅዱስ አልተኰነነም ማለት ይቻላል? ሁለተኛ፣ የምዕራባውያኑ ዘፈንና የእኛ አገር ዘፈን በይዘቱም ሆነ በቅርጹ የሚለያይበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስንና ትውፊታችንን እንጂ፣ ምዕራባውያንን መከተል አይጠበቅብንም፡፡ እኔ በግሌ “West always best!” የሚለውን አስተሳሰብ አልወደውም፡፡        
 31. ሐዋርያቱ የሐዲስ ኪዳንን መጻሕፍት የጻፉልን በግሪክ ቋንቋ ነው፡፡ ለዚህ ነው እናት ቋንቋ የሆነውን ግሪክን ጠቅሰን የምንነጋገረው፡፡  
 32. Johannes P. Louw and Eugene Albert Nida, vol. 1, Greek-English Lexicon of the New Testament: Based on Semantic Domains, electronic ed. of the 2nd edition., 772 (New York: United Bible Societies, 1996). በእኔ ግርድፍ ትርጒም የማይስማማ ካለ እነሆ፣ “drinking parties involving unrestrained indulgence in alcoholic beverages and accompanying immoral behavior.”
 33. H.G. Liddell, A Lexicon: Abridged from Liddell and Scott’s Greek-English Lexicon, 460 (Oak Harbor, WA: Logos Research Systems, Inc., 1996). Johannes P. Louw and Eugene Albert Nida, vol. 1, Greek-English Lexicon of the New Testament: Based on Semantic Domains, electronic ed. of the 2nd edition., 772 (New York: United Bible Societies, 1996). A Greek-English Lexicon of the New Testament and Other Early Christian Literature, transl. & ed. William F. Arndt and F. Wilbur Gingrich (Univ. of Chicago, 1957).
 34. Robert L. Thomas, New American Standard Hebrew-Aramaic and Greek Dictionaries: Updated Edition (Anaheim: Foundation Publications, Inc., 1998). ይህ መዝገበ ቃል፣ ኮሞስ ለሚለው ቃል ያቀረበው ትርጒም ይህ ብቻ መሆኑን፣ አንባቢ ልብ እንዲለው እፈልጋለሁ፡፡ ትርጒምህ ፍትሓዊ ላይሆን ይችላል የሚሉ ሰዎች ካሉ፣ እነሆኝ እንግሊዝኛው (ቃል በቃልሳይጨመር ሳይቀነስ):— “κῶμος kōmos; from 2968; a village festival, revel:—carousing.”
 35. Johannes P. Louw and Eugene Albert Nida, vol. 1, Greek-English Lexicon of the New Testament: Based on Semantic Domains, electronic ed. of the 2nd edition., 772 (New York: United Bible Societies, 1996).
 36. ይህ የእኔ ስሌት ነው፡፡ ሚዛናዊ ለመሆን ስለሞከርሁ እንጂ፣ 90 ከመቶ ልለው አስቤ ነበር፡፡ እናንተ ደግሞ ሚዛናዊ የሚመስላችሁን ስሌት ልትሰጡት ትችላላችሁ፡፡ 
 37. የመንደር የተባለው ቃል፣ የቡድን ተብሎ መተርጐምም የሚችል ይመስለኛል፤ ምክንያቱም የተፈለገው መንደርነቱ ሳይሆን ስብስቡ ናውና፡፡ ከቃል በቃል ትርጒም (literal translation) ይልቅ፣ ሐሳብ ተሻጋሪ (dynamic translation) ትርጒም ጥሩ ትርጒም ፍልስፍና ነው በሚለው ሐሳብ እስማማለሁ፡፡   
 38. ቊም ነገሩ አንድ ቊና ጥቅስ መጥቀሱ ላይ አይደለም፣ ነገር ግን እነዚህን ምንባባት የምናብራራው እንዴት ነው የሚለው መሠረታዊ ጒዳይ እንጂ፡፡    
 39. አንዳንድ ወንድሞች የእነዚህ ክፍሎች ዐዳዊ ምንባብ ኮሞስ የሚለው የግሪክ ቃል ምን ትርጒም ወክሎ እንደ ገባ ግልጽ መረጃ ይሰጡናል በሚል፣ የክፍሎቹን ዐውዳዊ ምንባባት በመተንተን ብዙ ደክመዋል፤ የእኛንም ጊዜ አባክነዋል፡፡ ነገር ግን ትንታኔያቸው የሰጡንን ተስፋ እውን ሲያደርግ አላየንም፡፡ ጐበዝ ዐውቃለሁ ብሎ ጊዜ ከመግደል፣ አናውቅም ማለት ቢያንስ ጊዜን ይዋጃል፡፡ እኔ ዐውዳዊ ትርጒማቸውን ለመመርመር ስንፍና ይዞኝ ሳይሆን፣ መርምሬ ፋይዳ እንደ ሌላቸው ስለተገነዘብሁ ነው በአጭር ቃል አናውቅም ያልሁት፡፡          
 40. የቃላትን አማራጭ ትርጓሜ ስናጠና ማስተዋል ያለብን አንድ መሠረታዊ ቊም ነገር አለ (በዚህም ውይይት ውስጥ አንባቢዎቼ ይህን ነጥብ ቢያውቁት ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ)፡፡ ቃላት መወለድ ብቻ ሳይሆን፣ የማደግና የመሞት ዕጣ ፈንታም አላቸው፡፡ ታዲያ አንድ ቃል መቼ ተወለደ? በተወለደበት ጊዜ የቃሉ ትርጒም ምን ነበር? ኋላስ በታሪክ ሂደት ውስጥ ቃሉ ምን ምን ትርጒሞችን መወከል ጀመረ? ወዘተ የሚሉትን ጒዳዮች የሚያጠናው የዲያክሮኒክ ጥናት” (diachronic study) ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ቃል በአንድ የተወሰነ የታሪክ ጊዜ ውስጥ ምን ትርጒም ነበረው? የሚለውን ጒዳይ የሚያጠናው ደግሞ የሴንክሮኒክ ጥናት (synchronic study) ነው፡፡ ቊም ነገሩ እዚህ ጋ ነው፡፡ እኛ ትልቅ ትኲረት የምናደርገው በዲያክሮኒክ ጥናት ላይ ሳይሆን፣ በሴንክሮኒክ ጥናት ላይ ነው፡፡ ይኸውም የሐዲስ ኪዳን ጸሓፍያን ጽሑፋቸውን በሚጽፉበት የታሪክ ወቅት ቃሉ ምን አማራጭ ትርጒሞችን ይወክል ነበር የሚለው ነጥብ ነው (አንዳንድ ወንድሞች በክላሲካል ግሪክ፣ ኮሞስ የሚለው ቃል ይህንና ያንን ትርጒም ይወክላል የሚለው ትንታኔያቸው መስመር የሚስተው)፡፡ ከላይ የጠቀስኋቸው የግሪክ መዝገበ ቃላት፣ ኮሞስ የሚለውን ቃል የፈቱልን፣ ሐዋርያቱ በሚጽፉበት ጊዜ ምን ትርጒም ወክለው ነበር፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ግልጋሎት ላይ የዋሉት እንዴት ነው የሚለውን መሠረታዊ ነጥብ ታሳቢ አድርገው ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ አንደኛውና ሦስተኛው ትርጒሞች እኛ ዘፈን የሚለውን ቃል አያመለክቱም ማለት እንዴት ይቻላል? የመዝገበ ቃላቱ ጸሓፊዎች ይህ አማራጭ ትርጓሜ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ባይታዩ ኖሮ እነርሱም በአማራጭነት አይጠቅሱትም ነበር፡፡ መጥቀሳቸው መታየታቸውን እሙን ያደርገዋልቢያንስ መዝገበ ቃላቱን ባዘጋጁት ሊቃውንት ዘንድ፡፡           
 41. የፈረንጅ አታትያን ወንድም ዮናስ ቃሉን በተጠቀመበት መልክ መጠቀማቸውን እረዳለሁ፤ ነገር ግን የትኛውም ምሁር በዚህ ዐይነቱ አሻሚና አማራጭ ትርጓሜ ወቅት እኔ የመጨረሻ ብያኔ ሰጪነኝ ሊል የሚችል አይመስለኝም (ከዐውደ ምንባቦቹ አጥጋቢ ድጋፍ ካላገኘ በቀር)፡፡   
 42. ትርጒሞች ሁሉ ማብራሪያ እንደ ሆኑ እሙን ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ልቅ ትርጒምን (free translation) ከቊም ትርጒም (literal translation) ወይም ኢንተር ሊኒየር ትርጒምን (interlinear)ከነጻ ትርጒም (paraphrase) የሚለየው ነገር የለም ማለት ስሕተት ነው፡፡ ትርጒም ሁሉ ማራሪያ ነው በሚል፣ በቊም ትርጒምና (literal translation) በትርጓሜ መጻሕፍት (commentaries)  መኻል ልዩነት የለም ማለት ስሕተት ነው፡፡ ይህን ጒዳይ ልሞግትበት እችላለሁ፤ ግን ይህ ርእስ ለውይይታችን አንዳችም እርባና ያለው አይመስለኝም፡፡ ጒጒቱ ያላቸው ሰዎች የሚከተለውን መጽሐፍ እንዲመለከቱ እመክራለሁ—Merrie Bergmann, An Introduction to Many-Valued and Fuzzy Logic.  አንዳንድ ሰዎች ዳዊትም ሆነ ሌሎች የብሉይ ኪዳን ሰዎች ጨፍረዋልና እኛም ይህንኑ ብናደርግስ? የሚል ክርክር ይዘው እንደ ቀረቡ አይቻለሁ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን በጥንት ዕብራውያን፣ በግሪካውያንና ሮማውያን ባህል ውስጥ እንደ ተጻፈለን ይታወቃል፡፡ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ባህላዊ ዐውድ ውስጥ ለእኛ መሰጠቱ፣ እነዚያን ባህሎች መከተል አለባችሁ እየተባልን አይደለም፡፡ ለዚህ ነው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች፣ ይህ ባህል ነው ይህ ደግሞ የአምላክ ጊዜ አይሽሬ መልእክት ነው የሚሉን፡፡ በብሉይ ኪዳን ሰዎች ጀግኖችን ለማወደስ፣ ሰነፎችን ለማኰሰስ ወዘተ ይዘፍናሉ፡፡ እነርሱ አደረጉ ማለት ግን እኛ ማድረግ ይጠበቅብናል ማለት አይደለም፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ያደረገውን ሁሉ እናድርግ የምንል ከሆነ ገደል ነው የምንገባው፡፡ ክርስትና ከእስልምና ከሚለይባቸው ምክንያቶች መኻል አንዱ ይህ ነው፡፡ አንድ ሰው እስልምናን ሲቀባል አለባበሱ እንደ ዐረብ፣ የቤቱ ወግ እንደ ዐረብ፣ ቋንቋው ዐረብኛ፣ እንዲያው ባጭሩ ነገር ዓለሙ ዐረብ ይሆናል፡፡ በዐረብ ባህልና በእስልምና መካከል ልዩነት ማኖር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የወንዶች ጢም አስተዳደግና ሙስታሽ አቈራረጥ ጭምር እንኳ፣ ሱና በሚባለው አንጻር እንዲቃኝ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎች፣ እስልምና ባህልን የሚገረስስ ሃይማኖት ነው? የሚል ቅሬታ የሚያቀርቡት፡፡ ክርስትና ግን በጭራሽ እንደዚያ አይደለም፡፡ የአምላክን ዘላለማዊ መልእክት በባህላችን ውስጥ በማስገባት ሁሉም እንደ ባህሉ ይኖራል፡፡ ባህላችንን መጣል የምንገደደው ባህላችን ኢሥነ ምግባራዊ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ዕብራውያን ይዘፍኑ ነበር፤ ግሪኮች ይጠጡ ነበር ስለዚህ እኛም እንዲያ ልናደርግ ያስፈልጋል የሚለው፣ ለክርስትና ተረት ነው፡፡ ዳዊትም ሆነ ሌሎች ዘፍነዋል ወዘተ የሚሉት ሙግቶች፣ ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል ናቸው፡፡
 43. አንዳንድ ባልንጀሮቼ፣ ልክ ነህ የኮሞስ አማራጭ ትንታኔ አንተን ሙሉ ለሙሉ ይደግፍሃልግን ይህን ድምዳሜ አለዝበው ብለውኛል፡፡ እኔ ወደዚህ ድምዳሜ የደረስሁት ግልጽ ከሆኑት የሙግት ነጥቦቼ ተነሥቼ እንጂ፣ እንዲያው በዘፈቀደ እንጣጥ ብዬ አይደለም (የሙግት ነጥቦቼ ስሕተት መሆናቸው በግልጽ ከተነገረኝ፣ የማልመለስበት ምክንያት የለም)፡፡ አልያ ግን ማስረጃ የማቅረቡ ኀላፊነት በእነርሱ ትከሻላይ ስለሚወድቅ፣ እንዴት እንደማለዝበው መንገዱን እንዲያሳዩኝ እፈልጋለሁ (ሲጠነክር በመረጃ እንደ ጠነከረ ሁሉ፣ ሲለዝብም በመረጃ መለዘብ ይኖርበታል የሚል አቋም አለኝ)፡፡ ይህን መንገድ እስከሚያሳዩኝ ግን፣ ዘፈን ኀጢአት መሆኑን በትኅትና እገልጻለሁ፡፡ ወገኖቼ ዘፈን ኀጢአት ነው (በቅዱስ መጽሐፋችን) ነውርም ነው (በቅዱስ ትውፊታችን)፡፡ አትዝፈ! 
 44. Johannes P. Louw and Eugene Albert Nida, vol. 1, Greek-English Lexicon of the New Testament: Based on Semantic Domains, electronic ed. of the 2nd edition., 772 (New York: United Bible Societies, 1996).
 45. ዝኒ ከማሁ፡፡
 46. Robert L. Thomas, New American Standard Hebrew-Aramaic and Greek Dictionaries: Updated Edition (Anaheim: Foundation Publications, Inc., 1998). ትርጒምህ ፍትሓዊ ላይሆን ይችላል የሚሉ ሰዎች ካሉ እነሆኝ እንግሊዝኛው (ቃል በቃል):— “κῶμος kōmos; from 2968; a village festival, revel:—carousing.”
 47. ወንድም ዮናስ፣ የሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወቱ ክርስቲያኖች ጭፈራ ቤት (ናይት ክለብ) እንዳይሄዱ ጠንከር ባሉ ቃላት ገልጾአል (ለምሳሌ ገጽ 239)፡፡
 48. የስልክ ውይይት፡፡
 49. ፈረንጆቹ፣ “the devil is in the details” የሚሉት ዐይነት ቢጤ ነው፡፡
 50. ጆጆ፣ የኢዮስያስ የቤት ስም ነው፡፡ 
 51. ጭፈራ ቤት (ናይት ክለብ) ሄዶ ሙዚቃ ይጫወት የሚባለው ሰው፣ እንጀራው ነው፤ ሙያው ነው ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ኮሞስ የሚለው ቃል ከግማሽ በላይ የሆነው ትርጒሙ ጭፈራን ቤት ለማሳየቱ ከላይ ያለውን ትንተና ይመለከቷል፡፡ 
 52. የእኔ ፍላጎት ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ጥቅም፣ የእኔ አተያይ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን አቋም እንዲሁም የምሥራቹ ወንጌል ጒዳይ ይቅደም ማለት ድነት ካገኘ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ ምናልባት አንዳንድ ክርክር የሚወዱ ሰዎች የግል ፍላጎት ሲከበር የማኅበር ፍላጎት ይከበራል የሚል የፖለቲካ ክርክር ሊያጣቅሱ ይችላሉ፡፡ ቢያንስ የግል ፍላጎትና የማኅበረሰብ ፍላጎት በማይጣጣምበት ጊዜ ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን ቀኖና መገዛት እንዳለበት ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩ ይመስለኛል፡፡
 53. መርጦ መዝፈን ትክክል ነው እንኳ ብለን ብናስብ ማለቴ ነው፡፡
 54. ይህን ያደረገ ክርስቲያን ሙዚቃ ተጫዋች ጠቅሶ፡፡
 55. ወንድም ጌታ ያውቃል እና እኅት ቡሩክታዪት ለሠርግ የሚሆን ጥሩ ጥሩ መዝሙሮችን አዘጋጅተው እንዳቀረቡልን ዐውቃለሁ፡፡ ይኸው ጒዳይ ቢበረታታ፣ በሌሎችም ሥነ ምግባራዊ ርእሰ ጒዳዮች ላይ መዝሙሮች ቢዘጋጁ ጥሩ ነበር፡፡
 56. ወንድም ዮናስ፣ እኔ ይህን መጽሐፍ የጻፍሑት፣ ዘፋኞች…የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም እየተባለ ገላትያ 5÷21 ስለሚጠቀስብኝ፣ በሙያዬ ምክንያት ድነት እንደ ማልነፈግ ለማሳየት ነው የሚል ሐሳብ ሰንዝሮአል፡፡ እኔ ለእዚህ ሦስት ምላሾች አሉኝ፡፡ አንደኛ፣ ወንድም ዮናስ ራሱ፣ ዘፋኞች የሚለው ቃል ወጥቶ፣ ሚኮምሱ (“ኮሞስየሚያደርጉ)…የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱምየሚለው፣ የማይነቀስ የማይገሠሥ የአምላክ ቃል እንደ ሆነ ይስማማል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ “‘ኮሞስማለት ምን ማለት ነው የሚለው ነባሩ ክርክር ተመልሶ መጣ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ቢያንስ ኮሞስ የሚለው ቃል የሚወክላቸው ዘፈኖችና ዳንኪራዎች እንዳሉ ወንድም ዮናስ ይስማማልምሳሌ ገጽ 239 ይመለከቷል (ለዚህም ነው ጭፈራ ቤት ለክርስቲያኖች የሚሆን ስፍራ አይደለም፤ ስለዚህ ከዚያ ውጡ እያለ ጥሪ የሚያቀርበው)፡፡ በዚህ ትርጒሙ ደግሞ፣ ሚኮምሱ (“ኮሞስየሚያደርጉ)…የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱምየሚለው ቃል የአምላክ ቃል ነው፡፡ ሦስተኛ፣ ወንድም ዮናስ የእግዚብሔርን መንግሥት ለመውረስ በጽድቅ እና በቅድስናመካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት እንዲረዳው እመክራለሁ (ይህ ሐሳብ ግልጽ ካልሆነ፣ የነገረ መለኮት ተማሪዎችን እርዳታ ይጠይቋል)፡፡ በአጠቃላይ ወንድም ዮናስ ራሱ፣ ሚኮምሱ (“ኮሞስየሚያደርጉ)…የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱያምናል፡፡ ስለዚህ በእኔና በእርሱ መካከል ያለው ልዩነት የመጠን ጒዳይ (ማለትም ኮሞስ እንዴት ይፈታል? ምን ምን ጒዳዮችን ያካልላል?) ብቻ ነው፡፡ የእኔ ሙግት ትክክል ከሆነ፣ ወንድም ዮናስ ብዕር ያነሣበት ምክንያት አጥጋቢ አይደለም ማለት ነው፡፡   
 57. ወንድም ዮናስ ወደ ውጭ የተጣለው ክርስቲያን የሙዚቃ ባለሙያ ነው፡፡ ለመጣሉም ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው ገላትያ 5÷21 ነው የሚል ሐሳብ ሰንዝሮአል (በስልክ ውይይታችን)፡፡ ወንድም ዮናስ፣ በተለያየ ደረጃ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በደል ተፈጽሞብኛል፤ እንደ ጒድፍ የተወረወርሁት እኔ ወንድማችሁ ነኝ የሚል ከሆነ፣ በደረሰበት የአስተዳደር በደል ከልብ አዝናለሁ፡፡ ነገር ግን የመጽሐፉ ጭብጥና የአስተዳደር በደል በአገርም ሆነ በዘመድ የሚያያዝ አልመሰለኝም፡፡ 

 

የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ፣ አሳትሞ በሚያሠራጨው የምሥራች ድምፅ መጽሔት ላይ እንዲታተም የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው፡፡ በጽሑፉ ላይ አንዳች ለውጥ፣ ማሻሻያም ሆነ ቅነሳ እስካልተካሄደ ድረስ፣ ሙሉ ጽሑፉን በነጻ ማሠራጨት ይፈቀዳል፡፡ በኅትመት ሚዲያ ላይ ለማተም ግን ከጸሓፊው ፈቃድ ይጠይቁ፡፡ 

 

Seen 43274 times Last modified on Friday, 17 June 2016 15:02
Tesfaye Robele

ዶክተር ተስፋዬ ሮበሌ በኢንተርናሽናል የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የአዲሱ መደበኛ ትርጒም ተርጓሚ ሆኖ ሠርቶአል፡፡ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የቤተ እምነቱ የሥነ ጽሑፍ ክፍል ኀላፊና የ“ቃለ ሕይወት” መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ አገልግሎአል፡፡ ለዐቅብተ እምነት አገልግሎት ካለው ትልቅ ሸክም የተነሣ፣ ተስፋ ዐቃብያነ ክርስትና ማኅበርን መሥርቶአል፤ በዐቅብተ እምነትም ላይ በርካታ መጻሕፍትን አዘጋጅቶአል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪውንም የሠራው ለረጅም ዓመት በሠራበትና ወደ ፊትም በስፋት ሊያገለግልበት በሚፈልገው በክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት (Christian Apologetics) አገልግሎት ነው፡፡

Website: www.tesfayerobele.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 74 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.