You are here: HomeOpinionsየነቢያት ልጆችና የአባቶች ልጆች

የነቢያት ልጆችና የአባቶች ልጆች Featured

Written by  Wednesday, 09 August 2017 06:28

የዚህ ጽሁፍ አላማ ስለነቢይነት አገልግሎት ለማስተማር ሳይሆን መቋጫ ስላጣውና ወደአላስፈላጊ መቃቃር እያመራ ስላለው በምድራችን ስለተነሱ የነቢያት ልጆችና በብዙ መድረክ ስለሚደመጡ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያን መሪዎች (የአባቶች ልጆች) ጥቂት ለመተንፈስ ነው፡፡

 

በ2ኛ ነገ 2፡3 እና 5 እንደተጠቀሰው “የነቢያት ልጆች” የሚባሉ በእግዚአብሔር መንግስት አሰራር ውስጥ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሚስጥርንና ሃይልን በመግለጥ አገልግሎት እግዚአብሔር ያስነሳቸው፤ ነገር ግን ስለእግዚአብሔር መንግስት (ቤተክርስቲያን) ምንነትና ተልዕኮ/አሰራር ስለጸጋ ስጦታ አጠቃቀምና የመንፈስ ፍሬ በመማር ወደሙሉ አገልጋይነት ያላደጉ (የልጅነትን ጠባይ ያልሻሩ) ናቸው፡፡ ይህ በነቢያት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የአገልግሎት ጸጋዎች እንደሚኖር አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ፤ የወንጌላውያን ልጆች (ወንጌልን ለመመስከር የተለየ ሸክምና ድፍረት ያላቸው ነገር ግን በመንፈሳዊ እውቀትና ህይወት እንደሚገባ ያላደጉ)፣ የአስተማሪ ልጆች (አማኞችን በእውቀት ለማሳደግ የተለየ ሸክምና ቃሉን የመግለጥ አቅም ያላቸው ነገር ግን በቂ የእግዚአብሔር ቃል እውቀት የሌላቸውና ቃሉን እንደሚገባ የማይኖሩ)፡፡

 

በአሁኑ ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ተማሪዎችን/ልጆችን ወደብስለት እንደምናሳድግ የቀደሙትም አባቶች የነቢይነት ጸጋ ያላቸውን በመሰብሰብ በተዛማጅ ርዕሶች ያሳድጓቸው ነበር፡፡ ምናልባትም ኤልያስ ወደሰማይ ከመነጠቁ በፊት ተተኪውን ኤልሳዕን ይዞ 50 ወደሆኑት ተማሪዎቹ (የነቢያት ልጆች) ለስንብትና ተተኪውን ኤልሳዕን ለማስተዋወቅ በክፍሉ እንደሄደ ይገመታል፡፡ ከተሰጣቸው ጸጋ የተነሳ ስለኤልያስ መነጠቅ ኤልሳዕም ሆነ ሃምሳው ተማሪዎች በመንፈስ የተረዱ ቢሆንም “ነቢይ ነኝ” ብለው በአደባባይ አገልግሎት አልተገለጡም ነበር፡፡

 

በሃገራችን ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ የሚበላም የሚባላም ነገር ያላቸው አነጋጋሪ የነቢያት ልጆች ታላላቅ መድረኮችንና መገናኛ ብዙሃንን ተቆጣጥረዋል፡፡ ወንጌል ከተሰበከ፣ ነፍሳት ከዳኑ፣ በጌታ በኢየሱስ ስም ድውያን ከተፈወሱ፣ አጋንንቶች ከተባረሩና እንቆቅልሾች ከተፈቱ ምን እፈልጋለሁ በሚል አቋም ብዙዎች ዝምታን መርጠን ቆየን፡፡ ገንዘብ-ተኮር፣ ቁሳቁስ-ተኮርና ዝና-ተኮር የሆነው አገልግሎታቸው ግን በብዙዎች ዘንድ የዝምታን ጽዋ ሞልቶ ፈሰሰ፡፡ በተለይም በአንድ የነቢይነት ጸጋ/ቢሮ ብቻ የተንጠለጠሉ ቤተእምነቶች ደቀመዝሙርን ለማፍራት የሚቸገሩ ቢሆንም የብዙዎችን ቀልብ ሳቡ፡፡

 

80-20 በተሰኘው ፕሮግራሜ በአንዳንዶቹ ጉባኤ ታድሜያለሁ--80ከመቶ በነርሱ በሚያልፈው የእግዚአብሔር ጸጋ ለመገልገል፤ 20 ከመቶ ደግሞ ብርታትና ድካማቸውን ለመመርመር፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በአንድ መበለት ግቢ ዳስ ጥሎ ወደሚያገለግል ነብይ እገሌ ቤተክርስቲያን አቀናሁ፡፡ በደረስኩበት ደረጃ ነብይ እገሌ የእግዚአብሔር መንፈስ በሃይል የሚሰራበት ሰው መሆኑን ተረድቻለሁ፤ አጋንንት ሲወጣ፣ ድውያን ሲፈወሱ፣ እንቆቅልሽ ሲፈታ ብዙዎችም ጌታን ሲቀበሉ በማየቴ ጌታን አመስግኛለሁ፡፡ ነገር ግን የሚከተሉት የልጅነት ባህርያቱ ጣልቃ ገብተው ደስታዬን በአጭር አስቀሩት፡፡

 

አገልጋዩ “ካለው አይሰጥ” ሆነብኝ፡፡ አባቴ የበግ የጀርባ አጥንትን ስጋ “ካለው አይሰጥ” ይለዋል፡፡ በውስጡ ብዙ ስጋ ቢታይም ከከበበው ሹል አጥንቶች የተነሳ ስጋውን ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ይህም አገልጋይ ከገጠር፣ ከከተማና ከውጭ ብዙዎች በጉባኤው ቢታደሙም ከስድስት ያልበለጡ ሰዎችን ከአንድ ሰአት ባልበለጠ በማለዳው ጊዜ ካገለገለ በኋላ ድንገት ጸሎቱን አቋርጦ አሰልቺ የገንዘብ ማሰባሰብና የምስክርነት ፕሮግራሙን ቀጠለ፡፡ በከተማው መሃል አዲስ ወዳሰሩት ትልቅ አዳራሽ በአንድ ወር ጊዜ እንደሚዘዋወሩ በመግለጥ በቅርቡ በአፍሪካ ሁለተኛውን ሰፊ የአምልኮ አዳራሽ በኢትዮጵያ ለመስራት እንዳቀደ ተናገረ፡፡ ለዚህም ግዙፍ አዳራሽ የሚሆን ቦታ ለመግዛት ቦታውን በማፈላለግ ላይ መሆኑንም መሰከረ፡፡ በአሁኑም ወቅት የወር ወጪው አንድ ሚሊየን ብር እንደሆነ በመግለጥ ጉባኤውን ለስጦታ አንቀሳቀሰ፡፡

 

በቅድሚያ አስር ሺህ ብር የምትሰጡ እጃችሁን አውጡ በግል እጸልይላችኋለሁ አለ፡፡ ከጉባኤው ምላሽ ስለጠፋ ደረጃው ወደአምስት ሺህ ዝቅ ብሏል፡፡ ከነቴራንም በማምጣት በቅድሚያ አንድ ሺህ ብር የምትገዙ ሲል ጥቂቶች ገዙ፤ በሂደትም ወደአምስት መቶ አወረደው፡፡ ሰአታትን ከፈጀ ገቢ ማሰባሰብ በኋላ የአንድ ሰአት የምሳ እረፍት ይኖራል ብሎን ሄዶ ከሶስት ሰአት በኋላ ተመለሶ መድረኩን ያዘ፡፡ ብዙዎች የጸሎት ርዕሶች፣ ሰነዶችና ህሙማንን ይዘው ተከማችተዋል፡፡ ምስክርነት የምንሰማበት ጊዜ ይሆናል ሲል በሱ ጸሎት ባለፉት ቀናት ድንቅ እንደሆነላቸው ብዙዎች በየተራ መሰከሩ፡፡ ከምስክርነቱም በኋላ ተጨማሪ የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም ሲደረግ ከምሽቱ 12 ሰአት ሆነ፡፡ ሙሉ ቀን በዚያ ባሳልፍም ወንጌል በቅጡ ሲሰበክ ቃሉም እንደሚገባ ሲነገር አልሰማሁም፡፡ በመጨረሻም ፕሮግራሙ ለአስር ቀናት እንደሚቀጥል በመግለጽ ከውጭ ሃገር ለመጣችሁ ብቻ (ብዙ እስታቴር የዋጡ አሳዎች) ማታ ሁለት ሰአት ላይ በግል እጸልይላችኋለሁ ሲል ከዚህ በላይ መቋቋም ስላልቻልኩ ለመውጣት ተገድጃለሁ፡፡

 

በቀጣይም የዚህን መንፈሳዊ ብላቴና መጨረሻ ለመከታተል ሞከርሁ፡፡ እንደተናገው ባሰራው ግዙፍ አዳራሽ አምልኮ ቢጀምርም ህገወጥ ግንባታ ተብሎ ፈጽሞ እንደፈረሰበት አይቻለሁ፡፡ ቀድሞ ካከራዩትም መበለት ቤተሰብ ነንና እንዲህ ሲሉ አወጉኝ፡፡ የብዙ ወራት የቤት ኪራይና የውሃ ሳይከፍለኝ ሄደ፡፡ ደጋግሜ ብጠይቀው ለጊዜው ገንዘብ የለኝም ሲል ስለቀለደብኝ በመገናኛ ብዙሃን ታሪኩን እንደማወጣ ሳስፈራራው ከፊሉን ሰጠኝ፡፡ በሄደበትም አዳራሹን መንግስት ሲያፈርስበት ተመልሼ በዚህ ልቀጥል ሲል አማላጅ ቢልክብኝ አልፈቀድኩለትም ብለውኛል፡፡

 

ለመሆኑ በኔ አገልግሎት ድንቅ የሆነላችሁ ኑና በጉባኤ መስክሩ የሚለው አላማው ማንን ለማስተዋወቅ ነው? ምሳሌያችን ኢየሱስና ሃዋርያት ድንቅ ያረገላቸውን ጌታ እንዲከተሉና በሚሄዱበት ምስክር እንዲሆኑ እንጂ ከምርኮኞቹ ፊት እየሄደ ነጋሪት እንደሚያስጎስም የሮም ወታደር ለራስ ማስተዋወቂያና ክብር ያገለገሏቸውን አይጠቀሙባቸውም ነበር፡፡ ብዙዎቹ መሰል አገልጋዮች ምዕመኑን አስጨንቀው ብዙ ገንዘብ ቢሰበስቡም ለግል ጥቅማቸው እንደማያውሉት አይቻለሁ፡፡ ይልቅስ ያለጊዜው የተለጠጠው የግዙፍ አዳራሽ ግንባታና የቴሌቭዥን ወጪ አስጨንቋቸው እነርሱም ወደማያምኑበት ገንዘብ ማሰባሰብ መርቷቸዋል፡፡ ስለማያምኑበት በቴሌቭዥን ፕሮግራማቸው አያቀርቡትም/ይቆርጡታል፡፡

 

ምናልባት ለርሱና ለመሰሎቹ በጊዜ መመለስ ቢሆን ስል፣ ለሃገሪቱም የተሰጠው ብርቅዬ ጸጋ በለጋነቱ እንዳይጨነግፍ ሰግቼ ይህን ይፋ ለማድረግ ተገድጃለሁ፡፡ ይህ የአንድ አገልጋይ የአንድ ቀን ትውስታ (Index case) ቢሆንም በተመሳሳይና በባሰ ልምምድ ያሉ የነቢያትና የሃዋርያት ልጆች እንደሚኖሩ አስባለሁ፡፡ ታዲያ እንዲህ አይነቶቹን ብላቴኖች ቀርቦ ለጸጋው እውቅናን በመስጠት እያስተማሩ ለማቅናት መሞከር ነው ወይንስ የጀርባ ጥናት አድርጎ በአዳባባይ የአቋም መግለጫ ማሳወቅ ነው መፍትሄው?

 

የሳቱ እንበላቸው ወይስ የተሳሳቱ? የሳቱ የሚባሉት መሰረታዊ የሃዋርያት አስተምህሮን በሙላትም ሆነ በከፊል የማይቀበሉ ሲሆኑ እንደክርስቶስ ቤተክርስቲያንና የእግዚአብሔር መንፈስ እንደሚሰራበት ጉባኤ የማንቀበላቸው ናቸው፡፡ የተሳሳቱ ደግሞ ልዩነታችን መሰረታዊ ባልሆኑ መረዳት፣ አስተምህሮና ልምምድ ሆኖ በመማማርና መቻቻል የምናልፋቸው ናቸው፡፡ መሰረታዊ የሚባሉት ደግሞ ለደህንነት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግንኙነትና ለአውራ አገልግሎታችን የሚጠቅሙ ርዕሶች ናቸው፡፡ የመፍትሔ ሃሳብ ከመስጠቴ በፊት ስለመንስኤው የሚገባኝን ልናገር፡፡

 

1) የነቢያት ልጆች ወደመማሪያ ጣቢያ ሳይሆን ወደታላላቅ የአገልግሎት መድረኮች መፍጠን፡፡ ብዙዎቹ የህዝቡ ተጠሪነት ለኔ ነው፤ የኔ ደግሞ በቀጥታ ለስላሴዎች የሚል ድብቅ አቋም ስላላቸው በሌሎች እግር ስር ተቀምጠው ለመማር/ለመመከር ይቸገራሉ፡፡ ቤተእምነቷን እንደግል ርስታቸው ስለሚቆጥሯት እነርሱን መገሰጽ እንዲሁም በአስተዳደር ጉዳይ ጣልቃ መግባት ታቦቱን እንደመንካት ያስቀስፋል፡፡

 

ምናልባት ወደኋላ መልሰን አገልግሎቱን አቁማችሁ ማሰልጠኛ ተቋም ግቡ ማለቱ የማያስኬድ ነውና በነርሱ ደረጃ ሊያስተምሯቸውን ሊመክሯቸው የሚችሉ አካላትን ተቀብለው ከአገልግሎቱ ጎን ለጎን በመማርና መመከር የልጅነትን ጠባይ በመሻር ወደሙሉ ነቢይነት ቢያድጉ፡፡ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ልዩ ልዩ ጸጋን ግድ ይላልና ለሌሎች አገልጋዮችም በር ቢከፍቱ፡፡ ገና ወደአደባባይ ያልወጣንም የነቢያት ልጆች በተጠራንበት ቤተእምነት ሆነን ሊያሳድጉን በሚችሉ አገልጋዮች ስር እየተገለገልን እንደግ፡፡ ማንም ሊያስቆመውም ሆነ ሊያዘገየው በማይችል መልኩ በጥቂት የታመንነው ጌታ በብዙ ይገልጠናልና፡፡

 

2) የወንጌላውያን ቤተእምነትና አብያተክርስቲያናት ህብረት መሪዎች (አባቶች) ቀድሞ ሃላፊነታችንን አለመወጣታችን (በማስተማር፣ መምከር፣ ማበረታታትና የአገልግሎት በር መክፈት)፤ እንዲሁም ለተፈጠረው ችግር እውቀትና ብስለት የጎደለው (የልጅነት) እርምጃ መውሰድ፡፡ በሌላ አባባል የበሰሉ መሪዎች/እረኞች ማነስና ልጅነት የሚያጠቃቸው አባቶች (የአባቶች ልጆች) መብዛት፡፡ አቋም መያዝና እርምጃ መውሰድ (ውግዘት) የመጨረሻ ደረጃ ነው---አስተምር፣ ምከር፣ ገስጽ፣ ዝለፍም ተብሎ ደረጃውን የጠበቀ አካሄድ ተጽፎልናልና፡፡

 

በቅርቡ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያን ህብረት ያወጣውን ባለ-አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ አከብራለሁ፤ ተገቢም እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ስለሂደቱ በቀጣይ እንደሰማሁት የሚመለከታቸው አካላት በአካል እንዳልተጠየቁና ለማስተካከልም በህብረቱ ጽህፈት ቤት እድል እንዳልተሰጣቸው ስሰማ ቅር አለኝ፡፡ የህብረቱም ጽህፈት ቤት ለዚህ የሰጠው ምላሽ ለአመት ያህል ስናጠና ቆይተናል የሚል ነው፡፡ የህክምናና ማህበራዊ ጉዳይ ተመራማሪ እንደመሆኔ አንድ ጥናት ሲደረግ ለሚመለከታቸው አካላት የመጨረሻው የአቋም መግለጫ ብቻ ሳይሆን ዝርዝር የጥናቱ አላማ፣ አካሄድ፣ ለጥናቱ የተመረጡ መመዘኛዎች፣ የመረጃ ምንጮችና ጥናቱን ያደረጉ አካላትና ግኝት ዝርዝር አስቀድሞ ይቀርባል፡፡ አሁንም አልመሸምና አመት የፈጀው የህብረቱ ጽህፈት ቤት ጥናት (ካስፈለገ የግለሰቦችንና ድርጅቶችን ስም በማውጣት) ይፋ እንዲሆን እጠይቃለሁ፡፡ አንድን ቤተእምነት ወይም እንቅስቃሴ ለመባረክም ሆነ ለማውገዝ መኬድ ያለባቸው አምስት ደረጃዎች እንዳሉ አስባለሁ፤-

 

  • ከሃዋርያት አስተምህሮና የአባቶች ጉባኤ ቀኖና በመነሳት የክርስቶስ/እውነተኛ ቤተክርስቲያን መሰረታዊ አስተምህሮዎችን መለየት (ይህ እንደሚዛን ያገለግላል)

  • ከታመኑ ምንጮች (መተዳደሪያ ደንብ፣ መሰረተ እምነት፣ የማስተማሪያ ጽሁፎችና የአውራ መሪዎች አስተምህሮና ቃለመጠይቅ) በመነሳት ጥያቄ ያሉብንን ቤተእምነቶችና አገልጋዮች አቋማቸውን መረዳት፡፡

  • መናፍስትን የመለየት ጸጋ ያላቸውን የታመኑ/የታወቁ አገልጋዮች በግልና በስፍራው በመገኘት እየጸለዩ በመንፈስ እንቅስቃሴውን እንዲመረምሩ እድል መስጠት

  • ቀድሞ ባዘጋጀነው ሚዛን መሰረት ጎድለው በተገኙበት በጸሎት፣ ትምህርትና ምክር ለማቅናት መሞከር

  • ሊቀኑ ባይወዱ ወንጌላውያን የሚለውን የወል መጠሪያ ይዘዋልና መንጋውን ከስህተት አሰራር ለመጠበቅ (እንደዘመኑ ባለአደራ) የሃገሪቱን የሃይማኖት መቻቻል ህግ/መመሪያ ከግምት በማስገባት ስህተቱን ለምዕመን መግለጥ

 

በአጠቃላይ የመንፈስ ፍሬ እንጂ የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታ ብስለትን/መንፈሳዊነትን አይጠይቅምና የመንፈስ ፍሬ ጎድሎባቸው የጸጋው ስጦታ የበዛላቸውን የነቢያት/የሃዋርያት ልጆች እንዴት ወደብስለትና ሙላት እንድናመጣ እግዚአብሔር መሪዎችን ይርዳ፡፡

 

Seen 8604 times
Samson Hailegiorgis

I'm  a medical doctor in profession specialized in Public Health with Masters and PhD in Religion and Theology. My PhD thesis is on "Unity among Evangelical Churches in Ethiopia". Currently, I'm a leader in one of the Evangelical Churches in Addis.  

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Latest from Samson Hailegiorgis

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 86 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.