You are here: HomeSermonምግባረ ሰጎንና የሰይጣን ሽንገላ

ምግባረ ሰጎንና የሰይጣን ሽንገላ

Written by  Friday, 22 May 2015 00:00
ምግባረ ሰጎንና የሰይጣን ሽንገላ Image credit: Peter Chadwick

ማያስደስቱትን ነገሮች ችላ የሚልን ወይም እንደሌሉ የሚያምንን ሰው ፈረንጆቹ “Ostrich” ይሉታል፡፡ ሰጎን እንደማለት ነው፡፡ እንደ ሚሪያም ዌቢስተር መዝገባ ቃላት (Merriam-Webster Dictionary) ገለጻ የቃሉ አመጣጥ ከፈረንሳይኛ፣ ከላቲንና ከግሪክ የአንድ ወፍ ዝሪያ መጠሪያዎች በተዋኻዱ ቃላት ነው፡፡ በአማርኛችንም ብዙ ተምሳሌታዊ (metaphorical) የቅጽል ስሞች ለሰዎች እንደሚሰጡት አይነት ነው፡፡ ለምሳሌ ደፋሩንና ቆራጡን “አንበሳ”፣ እንደ አካባቢው ሁኔታ ተለዋዋጭ ባህሪይ ያለውን ደግሞ “እስስት”፣ ተንኮለኛውን እባብ፣ ብልጣብልጡን ጮቅ እና ከዚህም የከፉ የእንስሳትና የአራዊት ስሞች ለሰዎች በቅጽል ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ የቅጽል ስሞች አንዳንዴ ለስድብነትም ስለሚውሉ ስሞቹ የተሰጡአቸው ሰዎች እንደ እንስሳቱ አይነት ባህርይ ሊኖራቸውም ላይኖራቸውም ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን የቅጽል ስሞች የሰዎችን የአሁን ማንነትና ትክክለኛ ጠባይ ገላጭ ሆነው ይገኛሉ፡፡  መጽሐፍ ቅዱስም ይህንን ተምሳሌታዊ አጠራር ሲጠቀም ይታያል፡፡ ኢየሱስ “የይሁዳ አንበሳ” ተብሎአል፡፡ በፍርድ ቀን የመንግስተ ሰማያት ወራሾች በበጎች፤ ውጭ የሚጣሉት ደግሞ በፍየሎች ተመስለዋል፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት ደግሞ “በልባብና በልጓም ካልተገሩ በስተቀር ወደ አንተ እንደማይቀርቡ ማስተዋል እንደሌላቸው እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ” ይላል (መዝ 32፡9 አ.መ.ት)፡፡ ይህ ክፍል በመከራ ውስጥ ሲያልፉ ካልሆነ በቀር ወደ እግዚአብሔር መቅረብና በርሱ መታመን፣ ለእርሱ መገዛት ስለማይሆንላቸው ሰዎች የተጻፈ ተምሳሌታዊ የዝማሬ ስንኝ ነው፡፡

 

የሰው ልጆች በአብዛኛው የምንጠራበት ስም በውልደታችን ቀን ወይም ከዚያ በኋላ “የወጡልን” ስሞች ናቸው፤ “given name” እንደሚሉት አይነት፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በስህተት ወይም የቤት መጠሪያ ስሞች በዚያው ዘልቀው የእድሜ ልክ መጠሪያ ይሆናሉ፡፡ ብዙዎቻችን ስኬታማ በሆነችበት የቴሌቪዥን ቶክ ሾዎችዋ የምናውቃት ዝነኛዋ ኦፕራህ ዊንፍሬይ (Oprah Winfrey) ኦፕራህ “Oprah” የሚለው ስያሜዋ በተወለደችበት ቀን አዋላጅ ነርሷ ኦርፋ “Orpah” የሚለውን በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የምናውቃትን የሩትን አማች ስያሜ በስህተት ፊደሎቹን አቀያይራ በልደት ካርዷ ላይ ኦፕራህ “Oprah” በማለት በመጻፍዋ በዚያው ይዞ የቀረ ነው፡፡

 

 

የስነ ልቦና ምሁራን የሰዎች መጠሪያ ስሞች በሰዎች ስነ ልቦናና ማንነት ላይ ተጽዕኖ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ “ስምን መልአክ ያወጣዋል” እደሚሉት የአንዳንዱ ስም ከባህሪው ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ አሸብር የሚሉት ልጅ ነበር በሰፈራችን፡፡ ልጁ በሰፈሩ ውስጥ ለሚነሱት ከ65በመቶ በላይ ሁከቶች መንስኤ ነው፡፡ “እውነትም አሸብር!” ይባል ነበር፡፡ በ1ሳሙ 25 ላይ ታሪኩ ሰፍሮ የምናገኘው ናባል “እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፤ ስሙ ናባል ነው፡፡ ስንፍናም አድሮበታል፡፡” ተብሎለታል፡፡ በአንጻሩ የአንዳንዱ ስብዕናና ማንነት ደግሞ ከሚጠራበት ስም እጅግ ተቃራኒ ነው፡፡ ምህረት በደረሰበት ደርሰው የማያውቁ ሰዎች “ምሕረት!” የሚል ስም ተሸክመው ይዞራሉ፡፡ እነ ሰላም፣ እነ እውነት፣ እነ ፍቅረ ኢየሱስና ፍቅረ ማሪያም፣ እነ ደስታ ወዘተ ከስማቸው ተቃራኒ ዘመናቸውን የፈጁበት ሁኔታ አለ፡፡

 

 

የየግላችንን ስያሜ ጉዳይ ለጊዜው ተወት አድርጌ ሁላችንም በጋራ በምንጠራበት “ክርስቲያን” በሚለው ስም ሥር በቅድሚ ያነሳሁትን ሰጎን የሚለውን ስያሜ ተንተርሼ ሀሳቤን አስቃኛችኋለሁ፡፡ መግቢያው ላይ እንዳልኩት Ostrich ወይም ሰጎን የሚለው ስያሜ የሚሰጠው የማያስደስቱትን ነገሮች ችላ ለሚል ወይም እንደሌሉ ለሚያምን ሰው ነው፡፡ ሰጎን በመጽሀፈ ኢዮብ ውስጥ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን እንዳልሰጣት ይናገራል፡፡ “…እንቁላልዋን በመሬት ላይ ትተዋለች፣ በአፈርም ውስጥ ታሞቀዋለች፣ እግር ይሰብረው ዘንድ የምድረ በዳም አውሬ ይረግጠው ዘንድ ትረሳለች፡፡ የእርስዋ እንዳልሆኑ በልጆችዋ ትጨክናለች፡፡ በከንቱም ብትሰራ አትፈራም፡፡ እግዚአብሔር ጥበብን ከእርስዋ ከልክሎአልና፣ ማስተዋልንም አልሰጣትምና” (ኢዮ 14-17)፡፡ ከዚህ ባህርይዋ ባሻገር ሰጎን በተለምዶ እንደሚወራው  ሊያጠቃት ከመጣው ጠላት ለመደበቅ አንገትዋንና ጭንቅላትዋን በአሸዋማው መሬት ላይ ታጋድማለች ወይም አንዳንድ ጊዜ እንደሚባለው በአሸዋው ውስጥ ትቀብራለች፡፡ ጭንቅላትዋን በአሸዋ ውስጥ መቅበሯ ለጊዜው ጠላቶችዋን እንዳታይ ወይም እቅስቃሴያቸውን እንዳትሰማ ከሚያግዳት በስተቀር ይህ ቂላ ቂል ድርጊትዋ ከውጭ የቀረውን ግዙፍ አካልዋን የሚያየው አጥቂ ጠላትዋን ህልውና የሚያሳጣው ካለመሆኑም ባሻገር ጥቃት እንዳይፈጽምባት ሊከለክለው አይችልም፡፡ በልጅነታችን ጅቦች ሌሊት ላይ ሲጮሁ አንገታችንን ብርድ ልብስና አንሶላ ውስጥ እንቀብር ነበር፡፡ ተናካሽ የሰፈር ውስጥ ውሻ ካባረራችሁ መሬት ላይ ቁጭ ብትሉ አይነክሳችሁም ስለተባልን ካባረረን መሬት ላይ ቁጭ እንል ነበር፡፡ እንዲሁም ልጆች የሚያስፈራቸውን ነገር ላለመመልከት አይኖቻቸውን በእጃቸው በመሸፈን ፍርሀታቸውን ለመቀነስ ይጥራሉ፤ አንዳንድ ጊዜም አዋቂዎች እንዲሁ አይነት ተመሳሳይ ነገር ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ ይሁንና ፊትን በአንሶላ ውስጥ መሸሸግ፣ ውሻውን ፍርሀት መሬት ላይ መቀመጥ ወይም አይንን በእጅ መሸፈን በራሱ ለጊዜው ፍርሀታችንን ሊያስወግድልን ይችል እንደሆነ እንጂ ከሁኔታዎቹ ሊያስጥለን አይችልም፡፡

 

ሰጎን አስገራሚ ተፈጥሮ ያላት የወፍ ዝርያ ነች፡፡ ዝርያዋ ከወፍ የሚመደብ ቢሆንም መብረር ግን አትችልም፡፡ ከዚህ ይልቅ በሰዓት እስከ 70 ኪሎ ሜትር ድረስ በሚጠጋ ፍጥነት መሮጥ ትችላለች፡፡ ይህም በምድር ላይ ካሉ ሁለት እግር ካላቸው እንስሶች ሁሉ ይልቅ ፈጣኗ ሯጭ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ሰው በሰዓት 33 ኪሎ ሜትር ድረስ መሮጥ ይችላል - እርሱም መቶ ሜትር ሯጭ የሆኑት እንደነ ዪዜይን ቦልት ያሉ ጥቂቶች ብቻ ናቸው ይህን ማድረግ የሚችሉት፡፡ ይህም ሆኖ በዚያው ፍጥነት ለረጅም ጊዜ መሮጥ ከባድ ነው፡፡ ሰጎን አይንዋ እስከ 50 ሚሊ ሜትር (5 ሳንቲ ሜትር) የሚደርስ ስፋት ያለው ሲሆን በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረታት ሁሉ በመጠን የበለጠ ነው፡፡ ይህ አስገራሚ አይንዋ ሊያጠቋት የሚችሉትን እንደ አንበሳ ያሉ ጠላቶችዋን በርቀት ለማየት ስለሚያስችላት ቀድማ ከአካባቢው ለመራቅ ወይም ለመደበቅና ለማምለጥ ያስችላታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጠላቶችዋን ለመከላከል ወደ ፊት ትራገጣለች፡፡ ወደ ኋላ መርገጥ ግን አይሆንላትም፡፡ እርግጫዋ አንበሳን ጨምሮ ሊያጠቋት የሚጠጓት ሁሉ ላይ ቢያርፍ በአንድ ምት ብቻ ሊገድል ወይም አካል ሊያጎድል ይችላል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሰጎን አብዛኛውን ጊዜ ጠላቶችዋን ለማምለጥ የምትሞክረው አንገትዋንና ጭንቅላትዋን በአሸዋማው መሬት ላይ በማጋደም ወይም እግሬ አውጭኝ ብሎ በመሮጥ ነው፡፡

 

 

እንደ ሰጎን ሁሉ “ሰይጣን የለም፣ ወይም ካለም ምንም ሊያደርግ በማይችልበት ሁኔታ አብቅቶለታል” በሚለው የውሸት ጉድጓድ ውስጥ እምነታቸውን የቀበሩ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ ሰይጣንም “እኔ የለሁም” የሚለውን ትምህርት በሰፊው ተቀባይነትን በማግኘት እያሰራጨው ይገኛል፡፡ በተለይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እየተመለከ በመጣበት በምዕራቡ ዓለም ሰይጣን የኃይማኖት ሰዎች ሌሎችን ለማደናገር የሚያወሩት የፈጠራ ወሬ ተደርጎ ነው የሚታሰበው፡፡ በምድረ አሜሪካ ‘ባርና’ ሪሰርች ግሩፕ በ2004 በሰራው ጥናት ዳግም ተወልደናል ከሚሉ ሰዎች ውስጥ 50 በመቶው ‘ሰይጣን የለም’ ብለው ያምናሉ፡፡ እኛጋ ደግሞ “እንደ እምነትህ ነው!” የምትል አባባል ብዙዎቻችን አፍ ውስጥ እየተለመደች መጥታለች፡፡ “ሰይጣን አለ  ብለህ የምታምን ከሆነ እውነትም አለ፣ ይሰራብሀልም፤ ካላመንክ ደግሞ አይኖርም፣ አይሰራብህም!” እንደማለት ነው፡፡ ይህ የምዕራቡ አስተሳሰብ ተጽዕኖ ስር እየወደቅን ለመምጣታችን አንዱ ማሳያም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

 

 

ሌላኛውና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የያዘ የሚመስለው አስተምህሮ ደግሞ “ሰይጣን በቀራንዮ መስቀል ላይ ተሸንፏል፤ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ምንም ኃይል የለውም፤ እንደሌለና ምንም ጥቃት ሊያደርስ የማይችል ነገር እንደሆነ መቁጠር አለበን” የሚለው ነው፡፡ እንደ እንደዚህኛው ጎራ አመለካከት ሰይጣን የብሉይ ኪዳን ችግር ብቻ ነው፡፡ እነኚህ ወገኖች ሰይጣን በአዲስ ኪዳን ሙሉ ለሙሉ ህልውናውን አጥቷል ብለው የሚያምኑና የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ይሁንና ይህኛውም ጎራ “ሰይጣን የለም” ከሚለው የመጀመሪያው ርዕዮተ ዓለም እምብዛም የሚሻልበት ነገር የለውም፡፡ እንዲያው “አልሸሹም ዞር አሉ” ነገር ብቻ ነው፡፡ እውነት ነው ዲያቢሎስ በእግዚአብሔር መንግስትና በአለም ላይ የነበረው የረጅም ጊዜ የመስረቅ፣ የመግደልና የማጥፋት እቅዱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ድል ተነስቶአል፡፡ “ሞት ሆይ መውጊያህ የታል? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የታል…?”፡፡ ይህ ድነት በእግዚአብሕር የአንድያ ልጁ ስጦታ በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በሚገኝ የዘላለም ህይወት ተገኝቷል፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሀ 3፡16) ፡፡

 

እውነት ነው ሰይጣን በቀራንዮ መስቀል ላይ ተሸንፎአል፡፡ በክርስቶስ በማመን ቀድሞ በሰይጣን ስር በነበርንበት የኃጢአት ባርነት አሁን አንኖርም (ኤፌ 2)፡፡ ይህ ማለት ግን ዲያብሎስ ሙሉ ለሙሉ ታስሮአል ማለት ግን አይደለም፤ ምቹ ሁኔታ ካገኘ ጥቃት አያደርስም ማለት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን አያስተምረንም፡፡ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም ገዢ” ይለዋል፡፡ በሌላ ሥፍራ ደግሞ “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና” ተብሎአል (2ቆሮ 11፡14)፡፡ “ዲያቢሎስ የለም፤ ወይም አለ፤ ግን ስለተሸነፈ ከእንግዲህ ምንም አያመጣም” የሚሉት ሁለቱም አካኼዶች አደገኛ ናቸው፡፡ የዛሬይቱን ቤተ ክርስቲያን በርካታ ምዕመናን ወደ እውነተኛ ንስሀና ዳግም ውልደት እንዳይመጡ ያደረገው የሀሰት ትምህርት ነፋስ ይሄ ነው፡፡ ሰዎች ቀድሞ በሰይጣንና በሀጢአት ቀንበር ሥር ከነበሩበት፤ በኃጢአት የሚገኝ ደስታና ዓለማዊነት ውስጥ ሳይወጡ የሚኖሩት ለዚህ ነው፡፡ ብዙዎች የዛሬ ዘመን የመድረክ አገልጋዮች ስብከት ርዕስ ይህ ሳይሆን፤ እንዴት አቋራጭ ደስታና ተድላ በራስ ተኮር መንገድ እንደሚገኝ ማስተማር ነው፡፡ ሰዎች ወደ እውነተኛ ንስሀ እንዳይመጡ እንቅፋት ከመሆናቸውም ባሻገር ራሳቸውም ጌታ የማያውቀውን አገልግሎት ሲያሳድዱ ኖረው በፍርድ ቀን “አላውቃችሁም እናንተ አመጸኞች ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው የእሳት ባሕር ሂዱ” ይባላሉ፡፡

 

 

ቅርብ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ በሚሄድ አውቶብስ ውስጥ አጠገቡ የተቀመጥኩት ሰው አንድ የሆነ በጋዜጣ የተለበደ መጽሐፍ ውስጥ አንገቱን ቀብሮ ተመስጦአል፡፡ ሁሌም ከሰዎች ጋር በሚመቻቸው መንገድ በመቅረብ ወንጌልን ለመመስከር እዲረዳኝ እንደማደርገው ሰውዬውን ከተመስጦው አውጥቼ የማናግርበትን መንገድ ሳፈላልግ አውቶብሱ አዲሰ በተሰራው የሞጆ አዳማ መንገድ ላይ ባለው አቅም ሁሉ በመምዘግዘግ ላይ ነበር፡፡ ቀስ ብዬ በዓይኔ ጠርዝ የሚያነብበውን ነገር ገልመጥ ሳደርግ ስለ ኢሉምናቲና የሰይጣን ማህበራት በአማርኛ የተጻፈ ነገር ነው፡፡ ሰውዬው በፍጹም ተመስጦና ፍርሀት ውስጥ ነበር፡፡ “ኢሉምናቲ እንዴት ነው?” አልኩት፡፡ ይሄኔ ቀና አለና ያዋራኝ ጀመር፡፡ የማኅበሩን መዋቅርና በውስጡ ያሉትን ታዋቂ ግለሰቦች ጠቃቀሰልኝ፡፡ ኃይማኖቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ስር እየሰደደ መምጣቱንና ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን በከፍተኛ ፍርሀትና ተመስጦ አስረዳኝ፡፡ ውይይታችንን በቀጠልን ቁጥር ሰውዬው የወንጌላዊያን አማኞች አባል እንዳልሆነ ገመትኩና ሰይጣን በክርስቶስ ሥራ የተሸነፈ ስለመሆኑ፣ ንስሀ መግባትና ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል እንደሚገባ፣ ሰይጣን ምክንያት ካላገኘ እንደማያጠቃንና፣ ነቅተን ልንዋጋው እደሚያስፈልግ፣ ሁል ጊዜም በቃሉ እውቀት መበርታት እዳለብንና መጽሐፍ ቅዱስን ሳናቋርጥ ማጥናት እንደሚገባን ላስረዳሁ ሞከርኩ፡፡ ሆኖም ግን ካለበት ሁኔታ ውስጥ ላወጣው እንደቻልኩ አላውቅም፡፡ ከላይ ካየናቸው ሁለት የሽንገላ መንገዶች በተጨማሪ “ሶስተኛው አማራጭ” ዲያቢሎሳዊ የማታለያ ስልት ሰይጣን ራሱን አስፈሪና ሁሉን ቻይ አስመስሎ የሚቀርብበት አካኼድ ነው፡፡ በዘመናችን በሰፊውና በይፋ እየተመለከና እየተሰራጨ የሚገኘው የሰይጣን ኃይማኖት አምልኮ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ሰይጣን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አደገኛና አስፈሪ ‘አምላክ’ እንደ ሆነ ለማሳየት እየጣረ ነው፡፡ የዓለማችን ታላላቅ መሪዎችን ሳይቀር፣ ቢሊዬነሮችንና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችን በአባልነት ያቀፈ የ “ኢሉሚናቲ”፣ “ባፖሜት” ወዘተ ኃይማኖቶችና ሚስጥራዊ የሰይጣን ማኅበሮች እንዳሉና ዓለምን እንደተቆጣጠሯት ለወደፊትም የዓለምና የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታ “በእነርሱ” ላይ የወደቀ እንደሆነ ለማሳየት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይሞከራል፡፡ በዚህ የሽብር ፍርሀት ውስጥ ወድቀው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በእነዚህ የትምህርት ነፋሳት የተወሰዱ ሰዎች ለብዙ ስህተትና ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ “የለሁም” ብሎ ያሳመናቸው ዲያብሎስ ወይም የለም ብለው ያመኑትና ምንም እንደማያመጣ የሚገምቱት ዲያብሎስ በረቂቅና ውስብስብ ሽንገላው ወደ ስህተት መርቶአቸዋል እየመራቸውም ነው፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከሆነው በላይ ራሱን አግዝፎ የሰዎች ሁሉ እጣ ፈንታ በእጁ እንደሆነ ለማሳየት የሚሞክረውም ዲያብሎስ አሳሳች ነው፡፡ ብዙዎችን በዚህ የሽብር ፍርሀት ቀንበሩ ውስጥ አጥምዶ እየገዛቸው ይገኛል፡፡

 

 

ዲያብሎስ ከመጀመሪውም ሸንጋይ ነው፡፡ ሀሰተኛ፤ የሀሰትም አባት ተብሎአል (ዮሀ 8፣44)፡፡ ፊት ለፊት “ዲያቢሎስ ነኝ” ብሎ ቢመጣ የሚቀበለው ስለማይኖር ይመስለኛል ሰዎችን ወጥመዱ ውስጥ እስኪያስገባቸው እያማለለ የሚሸነግላቸው፡፡ የሰው ዘር ሁሉ እናት የሆነችውን ሔዋንን ፍሬውን ቀጥፋ እንድትበላ ሲያማልላት የተጠቀመው መሳሪያ ሽንገላ ነው፡፡ ፍሬውን እርሷና ባሏ መብላት ያለባቸው ለራሳቸው ጥቅም አይኖቻቸው እንዲከፈቱና እንደ እግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የሚያውቁ እንዲሆኑ እንደሆነ የእነርሱ ተቆርቋሪ መስሎ አሳምኗት ነበር፡፡ ፍሬውንም ስታየው የሚያስጎመጅ ነበር፡፡ ኢየሱስ አርባ ቀንና ሌሊት ከጾመ በኋላ ሲፈትነው የተጠቀመውም ሽንገላን ነው፡፡ ኢየሱስ በጥበብ አሸነፈው እንጂ፡፡ ዛሬም ይኼው ዲያቢሎስ ብዙዎቹን ጠቃሚ መስሎ በመቅረብ እየሸነገላቸው ይገኛል፡፡ ዛሬ ላይ ብዙ ዓለማዊ ነገር የየዕለት ኑሮአችን ሆኖት አርፎአል፡፡ ለምሳሌ፡- “አንስከር እንጂ የአልኮል መጠጥ ብንጠጣ ምን አለበት? ልንጋባ እስከሆነ ድረስ በእጮኝነት ጊዜ ወሲብ ብንፈጽም ምን አለበት? የእህቶቻችን እያንዳንዱን የሴትነት ብልታቸውን የሚያሳይ እርቃን ቀረሽ አለባበስ ምን አለበት? ዓለማዊ ምኞትና ኑሮ ሁሉ… “ምን አለበት?” በምትል ፈሊጥ ሰርገው ገብተው ተዋኽደውናል፡፡ ዲያቢሎስ ብዙዎች በጌታ ቤት “የበረቱትን” ሁሉ ሳይቀር “እኔ ከእንግዲህ ምንም ጉዳት ማድረስ አልችልም፣ እንደሌለሁ ቁጠሩኝ” ብሎ አሳምኖ ሌሎችንም እዲያሳምኑለት መልምሎና አሰልጥኖ አሰማርቶአቸዋል፡፡ መጽሐፉ ሲናገር ግን (“መጽሐፉ” የሚለው ቃል ሁል ጊዜም መጽሐፍ ቅዱስን ይወክላል) “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና” ይላል (1ጴጥ 5፡8)፡፡ በሌላ ሥፍራ ደግሞ “የዲቢሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር ሁሉ ልበሱ” ይላል (ኤፌ 6፣11)፡፡ ሽንገላውን መቃወሚያ ብቸኛው መንገድ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር ሁሉ መልበስ ነው፡፡ ነቅተን ልንቃወመውና ሀሳቡን ልናውቅበት ይገባል፡፡ “ዲያቢሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” (ያዕ 4፣7)፡፡

 

 

ዛሬ ላይ ራሱን ከጨዋታ ውጪ የሆነ አስመስሎ በረቂቅ የሚሠራው ዲቢሎስ የአማኞችን መጋደል ከሰዎችና ከወንድሞቻቸው ጋር አድርጎታል፡፡ ዛሬ ዛሬ ነገረ ሥራችን ሁሉ እርስ በርሳችን መፋጀት እየሆነብን ነው፡፡ ዋናውን ጠላታችንን ረስተን ከሥጋና ከደም ጋር፣ ከሰዎች ጋር ውጊያ ገጥመናል፡፡ ይሁንና ቃሉ “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከስልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊን ሰራዊት ጋር ነው እንጂ” ይላል (ኤፌ 6፡12)፡፡ ለዲያቢሎስ ፈንታ ልንሰጠውና እንዲያጠቃን ልናመቻችለት አይገባንም (ኤፌ 4፡27)፡፡ እርግጥ ነው ክፉ ሰዎች አሉ፡፡ በጥበብ ልንይዛቸውና ከአንዳንዶቹ ደግሞ ልንሸሽ የምንገደድበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም ግን ቢቻለን ወንድሞችንና እህቶችን በመንፈሳዊ ማቅናት ለማቅናት እየታገልንና የመንፈስ አንድነታችንን ለመጠበቅ እየተጋን የጋራ ጠላታችን የሆነውን ዲቢሎስን ነቅተን ልንቃወመው ይገባናል፡፡

 

 

ወገኖቼ ዲያቢሎስ እያዘናጋን ነው! መንቃት ያስፈልገናል፡፡ እንደ ሰጎንዋ ወይም እንደ ህጻናት መታለል አይገባንም፡፡ “የለም ወይም ምንም አያመጣም” ብለን ራሳችንን ከቀበርንበት አመለካከት ውስጥ መውጣት አለብን፡፡ ዲያቢሎስ ዛሬም ያደፈጠና ምቹ ሁኔታን ካገኘ ሊያጠቃን የሚችል ጠላታችን ነው፡፡ በክርስቶስ የቀራንዮ መስቀል ሥራ ዲያቢሎስ መሸነፉ እውነት ቢሆንም መጽሀፍ ቅዱሳችን ዲያቢሎስን ዛሬም ነቅተን እንድንቃወመው ያስተምረናል፡፡ በቀራንዮ መስቀል ላይ በደላችን የተሰረየ ቢሆንም ከክርስቶስ ጋር በቅድስና መኖር በዚህ ምድር ላለን ቆይታም ዘላለም ህወትን ለመውረስ የግድ እንደሆነው ሁሉ የዲያቢሎስንም ሽንገላ ነቅተን ማምከን ይኖርብናል፡፡ በተለይ በዚህ በፍጻሜ ዘመን ዲያቢሎስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በታላቅ ቁጣ የወረደበት ዘመን ነው፡፡ ጊዜው እንዳለቀበትና ለፍርድ ሊቀርብ እደሆነ ያውቃና፡፡ “ዲያቢሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” (ራዕ 12፣12)፡፡ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ነቅተን ልንዋጋው የሚያስፈልገን ጠላት ነው ዲያቢሎስ፡፡ “ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጦር እቃ ሁሉ አንሱ… በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነት ጋሻ አንሱ (ኤፌ 6፣13፣16)፡፡ ይህ ብቸኛው ከዲያቢሎስ ወጥመድ የማምለጫው መንገድ ነው፡፡

 

ዲያቢሎስ ፈጽሞ የሚወገድበትና መሲሁ የሚነግስበት ጊዜ ከፊታችን አለ፡፡ በዚያን ጊዜ ዲያቢሎስና መላዕክቱ በእሳት ባሕር ውስጥ ይጣላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ደግሞ ጌታችንን ፊት ለፊት ልናየውና አብረነው ለዘላለም ልንኖር ቀን ተቆርጦአል፡፡ እስከዚያው ግን ጠንቀቅ፤ ነቃ ማለቱና በቅድስና መኖሩ ይበጃል፡፡ በዚህ የተስፋዬ ጫላ የመዝሙር አዝማች ጽሑፌን ላጠቃልል፡-

 

ታሪክ ሊጠቀለል፣ ዘመኑ ሊዘጋ፣ 
ጌታ በደጅ ነው! የተኛ ሰው ይንቃ
ቀኑ ሳይመሽብን፣ እንንቃ በግዜ፤
ኋላ እንዳይሆንብን ወይታና ትካዜ፡፡

ኢየሱስ ይመጣል! ኢየሱሰ ጌታ ነው!

Seen 10331 times Last modified on Friday, 22 May 2015 21:17
Mesay Matusala

Mesay Matusala is a single (unmarried) man and a member of Hawassa Tabor Mekane Yesus congregations in Hawassa. He is a business and development professional, working employed for the last 7 years. Currently is focusing on writing, translation, and preparing to start a company in children and youth development and entertainment.

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 166 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.