You are here: HomeSermonለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች!

ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች!

Written by  Wednesday, 06 January 2016 08:13
Yared Tilahun (Eva.) Yared Tilahun (Eva.)

“በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡ የጌታ መልአክ ወደ እነሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ ታላቅ ፍርሀትም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲሁ አላቸው እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድሀኒት እሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡” ሉቃስ 2፤8_11

በዚህ የጌታን ልደት በምናከብርበት ዋዜማ ከቅዱስ ቃሉ ጥቂት ላካፍላችሁ

 

1. ተዋርዶም እንኳ የከበረ

ጌታ ኢየሱስ የተወለደባት ገጠራማዋ የቤተልሔም በረት በየትኛውም መመዘኛ ዛሬ በዓል ለማድመቅ የሚሰሩትን በረቶች አትመስልም፡፡ ደንበኛ የከብቶች በረት ናት፡፡በዚህ ስፍራ በመወለዱ ብቻ ሳይሆን ሰው በመሆኑ፤ የባርያን መልክ በመያዙ ጌታ የመጨረሻው ወለል ድረስ ወርዷል ፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል ራሱን ማዋረዱ የክብር ጌትነቱን አልሸፈነውም እርሱ፥ በበረት በጨርቅ ተጠቅልሎ ሳለ መልአክት ለእረኞች በተገለትጡ ጊዜ በዙሪያቸው ያበራው ክብር ‹‹የጌታ ክብር›› ነበር፡፡ መላአክቶቹም የእርሱ ‹‹የጌታ መልአክ›› ነበር፡፡ ሉቃስ ‹‹ጌታ›› ብሎ የሚጠራው ስጋ ለብሶ ጨቅላ ሆኖ የተወለደውን እየሱስ እንደሆነ የምንረዳው ‹‹ዛሬ በዳዊት ከተማ መድሀኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዷል›› በማለቱ ነው፡፡ ይህም ኢየሱስ የመጨረሻ ዝቅ ብሎ እንኳ ማንነቱ የማይለወጥ የክብር ጌታ መሆኑን ያሳየናል፡፡

2. ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን የምስራች

በዘመናችን የገንዘብና የቁሳቁስ ብልፅግና ፤ የስጋ ጤንነት፤ ምድራዊ ምቾት ፤ ስኬት ወዘተ… እንደወንጌል ተቆጥረው የቤተ-ክርስቲያንን መድረክ፥ የመገናኛ ብዙሀንን እና የህትመቶችን ገጾች አጣበዋል ፡፡ እነዚህ ነገሮች በራሳቸው መልካምና እግዚአብሔርም የሚሰጣቸው ነገሮች መሆናቸው ጥርጥር የለውም ነገር ግን የፈለገውን ያህል ቢገኑ ወንጌል [የምስራች] መሆን አይችሉም፡፡ ለምን?

 

ወንጌልን ወንጌል ያሰኘው ደስ የሚያሰኝ ዜና መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለሰው ሁሉ የሚሆን በመሆኑ ነው፡፡ የገንዘብና የቁስ ሀብት የምስራች የሚሆነውና የሚያስደንቀው ለደሀ ብቻ ነው፡፡ ሀብት ለሀብታሞች የምስራች ሊሆን አይችልም፡፡ ስንት ሀብታሞች ናቸው ዛሬ የሀብታቸውን እኩሌታ ሰተው ሰላም፤ ደስታ፤ ፍቅር፤ እንቅልፍ ቢያገኙ የሚመርጡት? ጤናም ቢሆን የምስራችነቱ ለበሽተኞች ብቻ ነው፡፡ ፈውስ ለጤነኞች የምስራች ሊሆን አይችልምና። ትምህርትም በቤተ መጽሐፍትንና ላብራቶሪን መኖሪያቸው ላደረጉ ምሁራን የምስራች ሊሆን አይችልም እነዚህ ሁሉ ለተወሰነ ሕዝብ ወይም የህብረተሰብ ክፍል የሚሆኑ እንጂ ለህዝብ ሁሉ የሚሆኑ የምስራች አይደሉም። ነገር ግን እየሱስ ክርስቶስን መወለድ የምስራች ያደረገው በዋነኝነት ለሁለት የሰው ልጆች መሰረታዊ ችግሮች መድሀኒት መድሃኒት ሊሆን ስለተወለደ ነው። አነርሱም ሀጥያትና ሞት ናቸው። ሀጥያት እና ሞት ከላይ እንደዘረዘርናቸው እንደሌሎቹ ችግሮች የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ጉዳዬች አይደሉም፡፡ የሰው ሁሉ! የሕዝብ ሁሉ! የአለም ሁሉ! ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በዚህ አለም የኖሩ፤ እየኖሩ ያሉና ወደፊትም የሚኖሩ ሰዎች መሰረታዊ ችግሮች ናቸው። ጌታ እየሱስ በመስቀል ላይ በሰራው ስራ ሀጥያትን በተመለከተ የማያዳግም መፍትኤ ሰጥቷል፥ በትንሳኤው አማካይነትም ለሞት መድሀኒት ሆኗል፡፡ ለህዝብ ሁሉ የሚሆን የምስራች ይሏል ይህ ነው፡፡ 

3. የተወለደ መድሀኒት

መድሃኒቶች ዘመናዊ ላብራቶሪ ውስጥ ተቀምመው፥ በፋብሪካ ተመርተው ለገበያ መቅረብ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ሰው በምድር ላይ በኖረበት ዘመን ሁሉ መድሀኒት ይቀምማል። አሁን ድረስ በየገጠሩ ሰዎች ለመድሃኒትነት ቅጠል ይበጥሳሉ፥ ስር ይምሳሉ፤ አንዱን ከአንዱ አዋህደው መድሀኒት ይቀምማሉ፡፡

 

በዚህ ክፍል ግን አለም አይታው የማታውቀው ዓይነት መድሀኒት ተገለጠ፥ ይህ መድሀኒት የተቀመመ ሳይሆን የተወለደ ነው። እርሱ መድሀኒት ቀማሚ ሳይሆን ራሱ መድሀኒት ነው። ለዚህ ነው መልአኩ ‹‹መድሀኒት ተወልዶላችኋል›› በማለት በሜዳ ላሉ አረኞች ያበሰረው። ለስጋ በሽታ መድሀኒት ይቀመማል ለሐጥያትና ለሞት ግን መወለድ ነበረበት። አንደ ሌሎች መድሃኒቶች ሁሉ መድሃኒት ለመፈወስ ወድደ ውስጥ ዘልቆ መግባት አለበት የዛሬ 2000 ዓመታት በስጋ የተወለደው ጌታችን ኢየሱስ በአኛ ልብ ተወልዶ አድኖናል፡፡

 

መልካም የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል!

Seen 6990 times Last modified on Wednesday, 06 January 2016 08:45
Yared Tilahun

President, Golden Oil Ministry

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 68 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.