You are here: HomeSermonየቅዱሳን እንግድነት በቤተክርስትያን (I)

የቅዱሳን እንግድነት በቤተክርስትያን (I)

Written by  Wednesday, 27 April 2016 16:49

“ወዳጆች ሆይ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኃለሁ፡፡” (1ኛ ጴጥ. 2፡11) ሲል ሐዋርያው ጴጥሮስ ቅዱሳን ወገኖቹን ይመክራል፡፡ “እንግዲያስ” ይላል ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ገድል እያወሳ በሰው ሁሉ መካከል ያለውን ማንኛውም ልዩነት አስወግዶ ሁሉንም በአንድነትና በሰላም ከእግዚአብሔር አብ ጋር እንዳስታረቀ እየተናገረ የኤፌሶንን ሰዎች ሲመክር “…እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም።” (ኤፌ. 2፡19) ቤተክርስትያን በመሰረታዊ ገጽታዋ ህንጻና በሰው ሥርዓት የሰው ሥራ ሳትሆን ክርስቶስ ፍጹም የበላይና ማዕከል በሆነበት የተወሰኑ ቅዱሳን ቤተሰባዊ ትስስርን እየተከተሉ ሁሉም ኑሮአቸውንና ሕይወታቸውን በመከፋፈል በተወሰነ ቦታና ጊዜ የሚተያዩባት  የህይወት መንገድና ሥፍራ ናት፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን በዓለም እንጂ በቤተክርስትያን “እንግዶችና መጻተኞች” አይደሉም፡፡ ነገር ግን በቤተክርስትያን እንደ “እንግዶችና መጻተኞች” ሆነው ወይም በዓለም የዓለም ወዳጆች ሆነው ቢገኙ “ግርምቢጥ” ይሆናል ማለት አይደለምን?

 

“…እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግስት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ፡፡” (ኤፌ. 2፡11-12) በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ስራ አምኖ የዳነ ሰው ሰላም የተሰበከለትና ጥልን የተወ የሰላም ሰው ነው፡፡ በመሆኑም በቤተክርስትያን ቤተኛ ሆኖ ወዳጆቹንና ቤተሰቡን ይጠጋጋል እንጂ መልሶ እንደቀድሞው እንግዳ አይሆንም፡፡ የኤፌሶን ሰዎች ከመዳናቸው አስቀድሞ ከእስራኤል ሕዝብና መንግስት ጋር ምንም ዓይነት የጋራ የሆነ ነገር ስላልነበራቸው እግዚአብሔርን የማያውቁ ተስፋ ቢስ ፍጥረታት ነበሩ፡፡ በክርስቶስ አንድ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ከመጡ በኃላ ግን ለተስፋxው ሁሉ የተመረጡ ምርጦች ሆኑ፤ እንግድነታቸውና መጻተኝነታቸው አበቃ፡፡ የእግዚአብሔርን መንግስት ከሚወርሱ ጋር የአንድ ሀገር ዜጎችና በቤቱ ከሚኖሩ ጋር ቤተሰብ ለመሆን በቁ፡፡

 

በእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት የሆኑትን ሆነው እንዳይገኙ ግን ፍርሃት ወይም አለማመን ወይም አመጸኝነት ሰበብ ሆነው ሊያስቀሯቸው ይችላሉ፡፡ “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብ. 10፡24-25) በመሆኑም በቤተክርስትያን እንደ እንግዳ የሚኖር አንድ አማኝ የኤፌሶን ሰዎች ከመዳናቸው አስቀድሞ እንደነበሩት አሁንም “በሥጋ” የሚኖርና በሥጋ የሚመካበትንም ሆነ የሚያፍርበትን ያልተወ፣ ከእውነት ይልቅ የሰዎች አስተያየትና ግምት የሚያስጨንቀውና የሚያውከው፣  ከእግዚአብሔር ሥርዓትና አገዛዝ ርቆ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ወደ ዓለም ያደላ ወይም በራሱ ዓለም የተዋጠ (ነጮቹ ‘የቤተሰቡ ጥቁር በግ’ እንደሚሉት ዓይነት)፣ ለተስፋ ቃል ኪዳኑም ሁልጊዜ በግርታ የሚኖር፣ በኑሮውና በድካሙ ውስጥ ብቻ የተዋጠ፣ እግዚአብሔር አብ አባትንና ልጁንም ኢየሱስ ክርስቶስን በቅጡ የማያውቅ ምስኪን ሰው ሆኖ ሊገኝ  ይችላል፡፡

 

ምንም እንኳ በክርስቶስ በማመን የጽድቅ ጉዞን መጀመር እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር ጸጋና ረድኤት ለብቻው በአምላኩ ፊት የሚፈጽመው የእምነት መታዘዝ ቢሆንም ቅሉ ፈጽሞ በእግዚአብሔር መንግስትና ቤተሰብ ውስጥ ከመወለድ ውጭ ደግሞ ሊሆን አይችልም፡፡ ወንድሞች አሉ፤ እህቶች አሉ፡፡ አባቶች አሉ፤ እናቶች አሉ፡፡ ክርስቶስን ስንመርጥ ሕዝቡን እንመርጣለን፡፡ ክርስቶስን መርጠን ሕዝቡን የተውን እንደሆነ ግን ከእርሱም እንጎድላለን ምክንያቱም ወደ ክርስቶስ መምጣት አካሉ በሆነች በቤተክርስትያን ውስጥ መገጠምም ነውና፡፡ “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና።” (ዕብ. 11፡24-25) ለሙሴ ስለክርስቶስ መነቀፍን ማሰብና ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ለመቀበል መምረጥ አንድና አንድ ምርጫ ነበር፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱን ከሕዝቡ ጋር አንድ አድርጓልና፡፡ ሳውል የነበረው ጳውሎስን ጌታ እንዴት በመጀመሪያ እንደተገናኘው ልብ ይሏል!! (ሐዋ. 9፡1-9) ሲ.ኤስ.ሌዊስ “ሁላችንም ያለማቋረጥ የምናስተምርና የምንማር፣ ይቅር የምንልና ይቅር የምንባል፣ ለምንማልድላቸው ሰዎች ክርስቶስን የምንወክል ሌሎች ደግሞ ስለእኛ ሲማልዱ በክርስቶስ ፊት ረድኤቱን የምንሻ ሰዎች ነን።ከራስ ወዳድነት የተነሳ የሚመነጨውን ግለኝነት በየዕለቱ መሰዋት የአካሉ ኑሮ የሚያበረታታውን የእውነተኛ ማንነታችንን እውነተኛ እድገት በመቶ እጥፍ እንድንቀበል ያስችለናል፡፡ በአካል አንድነት የተሳሰሩ እንደ እጅና ጆሮ ያህል ልዩ ልዩም ናቸው።ለዚህም ነው ከቅዱሳን እጅግ ውብ የሆነ ልዩ ልዩነት አንጻር የዓለም ወዳጆች የሆኑቱ በጣሙኑ አሰልቺ ተመሳሳይነትና ድግግሞሽ ያለባቸው ዓይነት የሚሆኑት፡፡ መታዘዝ ነጻነትን የምናገኝበት መሄጃ ነው፣ ትህትና ወደ ደስታ የምንገሰግስበት ጎዳና ነው፣ አንድነት እውነተኛ ማንነታችንን የምናገኝበት መንገድ ነው፡፡” ሲል የክርስቶስ አካል በሆነችው በቤተክርስትያን በቅዱሳን መካከል ያለውን ትስስሮሽ ይገልጻል፡፡ 

 

አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።” (ኤፌ. 2፡13-18) ልዩነትንና ጥልን ሁሉ ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ሞቱ አስወግዶ አዋሐደን፤ ሰላማችንም ሆነ፡፡ አሁን እርሱ ከእኛ ከሁላችን በራሱ አንድን አዲስን ሰው ብቻ ሊፈጥር ይፈልጋል፤ ያውም እርሱን እራሱን፡፡ የእርሱ መልዕክት ሩቅ ለነበሩትም ሆነ ቅርብ ለነበሩት አንድ ነው - “ሰላም”!! “እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ” (ኤፌ.6፡14) ማንም የተለየ ወንጌል የተሰበከለትና የዳነ የለም፤ የክርስቶስ ወንጌል “የሰላም ወንጌል” ነው፡፡ “ሰላምን የምስራች ብሎ” ሰበከ፤ መልእክቱ የምስራች ነው - “ሰላማችሁ እኔ ነኝ” ነው፡፡ በቤተክርስትያን ከእርሱ ያልተጣላ ይጠላ እንደሆን እንጂ ከሰው አይጣላም፡፡ አሁን ለሁላችን የቀረልን የነፍሳችን እረሃብና የልባችን ጥማት ወደሆነው ወደ አብ በአንድ መንፈስ ከክርስቶስ ሥራ የተነሣ ሳንደናቀፍ መገስገስ ነው፡፡ በመሆኑም ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል የከፈለውን ከፍሎ ተጋድሎውን ፈጽሞ ሳለ ቅዱሳን ግን በቤተክርስትያን በማንኛውም ዓይነት ምክንያት ግድግዳን አቁመው እንግዶችና መጻተኞች ሆነው ቢኖሩ እርሱንና ስራውን ማቅለል ይሆናል፡፡ ሰው በተወለደበት፣ በገዛ ቤቱ፣ በቤተሰቡ መካከል እንዴት እንደ እንግዳና ባዕድ ሰው ይቀመጣል? ቅዱሳን በቤተክርስትያን እንግዶች ሆነው ከተገኙ በከንቱ ወይ ዓለምን ቤታቸው አድርገዋል አለበለዚያ ራሳቸውን የዓለማት ሁሉ ማዕከል አድርገውታል፡፡ ከዓለም የተወዳጀ ወይም ከራሱ ጋር ብቻ የተቆራኘ አማኝ ነው ከቅዱሳን ጋር በቤተክርስትያን ቤተኛ ሊሆን የሚያዳግተው፡፡ ከቅዱሳን ጋር ቤተሰብ የሆነው ግን ስለክርስቶስ ዓለምንና በዓለም ያለውን ሁሉ የናቀ ራሱንም የጠላና የካደ ቡሩክ ሰው ነው፡፡ ጸጋ ይብዛልን!! 

Seen 6426 times Last modified on Monday, 02 May 2016 06:43
Henok Minas Brook

ሔኖክ ሚናስ ከሁለት አሥርት አመታት በላይ ለእግዚአብሔር መንግስት በመቅናትና የቤተክርስትያንንም አንድነትንና ፍቅርን በመሻት በተለያየ መልኩ ጽሑፎችን የሚያዘጋጅና ከሁሉ አብልጦ ከቅዱሳን ጋር እንደቤተሰብ መኖርን የሚከታተል፥ በሙያው የፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር አማካሪ ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ሴት ህጻናት ልጆች አባት ነው።

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 86 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.