Print this page

የአገር ያለህ!

Written by  Friday, 11 July 2014 00:00

የአገራችን ሕሊናዊ በር ለሁሉም ክፍት ሆነ፡፡ በፍርሃት ይሁን በድንቁርና በጀብደኝነት ይሁን በአርቆ አስተዋይነት ለብዙ ዘመናት መክተን ያያዝነው መዝጊያችን ገርበብ ብሎ ሳይሆን ብርግድ ብሎ ተከፈተ፡፡ አሁን ወልጋዳም ጎፋፋም፣ ሃምሳ ቀንድ ያበቀለም ጭራቅ እንዳይገባ የሚከለክል ምንም ዘበኛ የለም፡፡ ደግሞ ለክፋቱ በገፍ የሚገባው የተቃናው የለዘበውና የተገራው ሳይሆን ጉዳጉድ ግሳንግሡ ነው፡፡

 

ድንበራችንን ዘልቆ ሲገባ በእንግዳ አክባሪ ባህላችን ተሳስቀን ተቀብለነው አገሩን ይሄዳን ስንል እዚሁ ተንፈራጥጦ ተቀመጠ፡፡ ጭራቁ ሁሉ ቤተኛ ሆነ፡፡ ለመሆኑ እዚህ አገር ክፉ አስተሳሰብና ዝቃጭ የሥነምግባር አተላ እንዳይደፋ የሚከለክል ሃይ ባይ ይገኛል?

 

እስኪ ደግ ደጉን እንናገር፡- ከዓለም ኅብረተሰብ ሥልጣኔ ተራርቃ፣ በዚሁም ምክንያት ኋላ ቀር ሆና የኖረች ኢትዮጵያ ለዕውቀት፣ ለሥልጣኔ፣ ለሥራ ትጋት፣ ለቴክኖሎጂ ቀሰማ፣ ለትውውቅ ለቅርርብ፣ በዚሁም ሳቢያ ለሚገኝ የሸመታ በሯን ብትከፍት ምን አለበት? ምንም፡፡ ሉልአቀፋዊ (ግሎባል) በሆነ ዓለም ውስጥ በሬን ከርችሜ ስለ ዕድገት ማለም የትም አያደርስም፡፡

 

ገበያው ላይ ያለው ዕቃና አገልግሎት ብቻ በሆነ ኖሮ እጅግም አያሳስብም ነበር፡፡ አሁን ግን እየተሸጠ፣ እየተሸመተም ያለው የአስተሳሰብ ዐይነትና የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡ ከዚሁም አብዛኛው መሠረታውያን የሆኑትን የስብእና ማልሚያ እምነቶች የሚንድ፣ ሠናያት ምግባራትን የሚያኪያኪስ፣ መለኪያ የለሽነትን የሚያራግብ፣ እብደትን የሕይወት ፈርጥ አድርጎ የሚሳይ፣ የሞራል ልቅነት ሲያይ ብራቮ! እያለ የሚያጨበጭብ፣ ከማኅበረሰብ ጤና ይልቅ ፈንጠዝያን የሚያከብር፣ አዳዲስ የርኩሰት አራዊት የሚያራባ የክፋት ሸቀጥ ነው፡፡ ይህ ብዙ መደብሮች ቢኖሩትም የጅምላ መሸጫው ሚዲያ የሚባለው የሕዝብ መገናኛ ነው፡፡ ፊልሞቻችን፣ ሙዚቃው፣ መጻሕፍቱ፣ ሬድዮው፣ ቴሌቪዥኑ፣ መጽሔቱ በየጓዳው፣ በየአዳራሹ፣ በሜዳው ሁሉ የሚዘራው ንጽሕና አምካኝ ዘር፣ ከልካይና አስተዋይ በሌለበት ሁኔታ እያጎነቆለ ነው፡፡

 

ዓለሙ ሁሉ በእብደት ሲሮጥ የቀደመን ስለመሰለን እነሱ በሶምሶማ የሚሄዱበትን ሁሉ እኛ ኢትዮጵያውያን በሽምጥ ጋልበን ደረስንበት፤ በአንዳንድ በኩል እንዳንቀድማቸውም ያሰጋል፡፡ መለኪያ የለሽነት ልክ ሆነ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ይህ ነጭ፣ ይህ ጥቁር ማለት ይቻል ነበር፡፡ “ኧረ ነውር ነው!” ሲባል አዎ ነውር ነው ይባል ነበር፤ ወይም ቢያንስ መሬት መሬት እያየን ፀጉር እያሻሸን እንለማመጥ ነበረ፡፡ ክፋት ዛሬ የተፈጠረ ባይሆንም በስሙ ተጠርቶ ክፉ ይባል ነበር፤ ተጻራሪውም ሠናይ፣ ዕጹብ፣ ግሩም፣ ድንቅ፣ ማለፊያ፣ በጎ፣ መልካም ይባል ነበረ፡፡ አሁን ግን የሥነ ምግባር ዛፍ ከነሥሩ ተመንገሎ ባየር ላይ ሰፈፈ፡፡ እኩይና ሠናይ የሚዳኙበት ችሎት ተዘጋ፡፡

 

“እንዴ ምን ጉድ ነው የምታወራው ምን ዓይነት የመዓት ነቢይ መጣብን” የሚል ሰው ይኖር ይሆን? “እንዴ የስንት ታቦት የስንት ደብር አገር፣ የስንት መስጂድ የስንት ሼህ አገር፣ የስንት ጸሎት ቤት የስንት ምዕመናን አገር፡፡” ይሁና! ይህ ሁሉ ሆኖም ሙት ሃይማኖታዊነት እንደ ሰደድ ለተዛመተው የሥነምግባር ዝቅጠት፣ እንደ ካንሰር ለሚራባው ሚዛን የለሽ ባህርይ በቂ መልስ ሊሰጥ አልቻለም፡፡ ይልቁን ወርቀዘቦ የግብዝነት ካባ ስለደረበለት ውስጥ ውስጡን እየበተበተ እንዲበላን ጉልበት ሰጠው፡፡ ቤተቅዳሴ ተጣበበ እንጂ ቅዱስ ልቡና አልተገኘም፤ ማተባችን ወፈረ እንጂ ከቆዳችን አልዘለቀም፤ ቤተጸሎት የወንበዴዎች ዋሻ ሲሆን ልበ ቅኖች በፍርሃት ተሸሸጉ፣ ጮሌዎች መንበሩን ተቆጣጠሩ፡፡ እውነት በመንገድ ጥራጊ አሰስገሰስ ታፈነች፣ ተዳፈነች፡፡ ቤተክርስቲያን ለዘመናዊነት እና ለድኅረ ዘመናዊነት የወርቅ ጥጃ ማሠሪያ ጉትቻ አዋጣች፤ ተሠርቶ ሲመጣላትም እልል አለች፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ሕዝብና አገር ያለን ሰዎች ነን እያልን ስናውጅ ኖረናልና መሆን አለመሆናችንን ረጋ ብለን እንጠይቅ፡፡ ታላቅነት በምን መስፈርት?

 • ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ ምድር
 • ኢትዮጵያ የአልደፈርባዮች፣ የጀግኖች አገር
 • ኢትዮጵያ ባህሏን ጠብቃ የቆየች የበለጸገ ባህል ያለው ሕዝብ አገር
 • ኢትዮጵያ ድብልቅ ማንነቷን በአንድ በብሔራዊ ጥላ ሥር ይዛ ለመዝለቅ የቻለች ኅብረብሔራት ምድር የራሷ የጽሕፈት ባህል፣ የሚያኮራ ቅርስ ያላት አገር

በዚህ በዚህ ሁሉ ሲለካ እውነትም ይህ ሕዝብና አገር ታላቅ ነው፡፡ በማንነታችን ደስ ልንሰኝ፣ ሳንሸማቀቅ ኢትዮጵያዊ ነኝ ልንል ይገባል እላለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ሌላም ገጽታ አለን፡፡

 

 • ከሥራ ይልቅ ለወሬ የተጋን
 • መቆራቆስን እንደ ወግ የያዝን
 • ለበጎ ለውጥ አፈፍ ብለን የማንነሳ
 • በሥልጣኔ ስም ለሚመጣ መርዝ ማጥለያ የሌለን
 • ቤት ውስጥ ካለው ወርቅ ይልቅ ማዶ ያለው ብረት የሚስበን መሆናችንን ስናስበው እጅግም ታላቅነት አይሰማንም፡፡

አንድ ሌላ ሕዝብ ነበረ፤ እስራኤል የሚባል፡፡ ምሳሌነቱ ስለሚጠቅመን ለታላቅነቱ የተነገረለትን መለኪያ እስኪ እናትኩርበት፡፡

 

ተናጋሪው የሕዝብ መሪ የነበረው ሙሴ ነው፣ መቸቱ እስራኤል ከግብፅ ባርነት ነፃ ወጥተው ወደ ተስፋይቱ አገር ሲጓዙ ሳለ በሙሴ ዘመን ማብቂያ ላይ ነው፡፡

 

“ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ፡፡ በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና፡፡ በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ቅርብ እንደ ሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው? ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ፣ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው? (ዘዳ 4፡5-9)

 

ለሕዝብ ታላቅነት ሁለት መለኪያዎች ጎልተው ይታያሉ፡፡

 • ሕገ እግዚአብሔር
 • ሀልዎተ እግዚአብሔር

ወይም በሌላ አነጋገር

 • ሕዝብ የሚተዳደርበት የጽድቅ ሥርዐትና 
 • ከሕዝብ ጋር ግንኙነት የሚያደርግ ሕያው አምላክ

 

እንግዲያው ታላቅ ሕዝብ ሙት ሃይማኖታዊነት ይዞ የባህል ገባር ሆኖ ደመነፍሱን የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ዛሬ ሲጠሩት ከሚሰማና ከሚናገር ሕያው አምላክ ጋር ትኩስ (ፍሬሽ) ግንኙነት ያለው ሕዝብ ነው፡፡

 

ታላቅ ሕዝብ ማለት መለኪያ የለሽ፣ ሥርዐት የለሽ፣ ከየጎዳና የሚነፍሰው ነፋስ ሁሉ የሚያንገዋልለው ካስማ አልባ ድንኳን ሳይሆን - ለፈሪሃ እግዚአብሔርና ለሕዝባዊ ልማት የሚያሠለጥነው ርቱዕ ጽድቅ የሆነ ሥርዐት ያለው ሕዝብ ነው፡፡ የዚህ ሥርዐት ምንጩ ቃለ እግዚአብሔር ነው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው የእውነትና የብርሃን ሀብት ነው፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን የዚህ የጽድቅ ሥርዐት ዐዋጅ መደብ ናት፣ የጽድቅ ሥርዐቱ ዐዋጅ ነጋሪትም ናት (ከነስሙ ነጋሪት) “የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ” ተብለናልና ድምጿን ከፍ አድርጋ ከዳር እስከ ዳር የሚያስተጋባ የጽድቅ አዋጅ ማወጅ ጥሪዋ ነው፡፡

 

ይህ የጽድቅ ሥርዐት የሚፈተሽባት መደብ፣ የሕያው አምላክ ሀልዎት የሚከሰትባት መቅደስም ናት፡፡ እርሷ ዘንድ የታየ፣ የተደመጠ፣ የሠራ፣ ባገር ሁሉ እንዲናኝ የእውነትና የበጎ ምግባር ሠርቶ ማሳያ ሞዴል ናት፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ታላቅነት የምታበረክተው አስተዋጽኦ አላት፡፡ ኢየሱስ ጌታችን ሁለት ደማቅ ስዕሎችን እፊታችን ዘረጋልን፡፡› 

 • “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤
 • እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡”

 

ይህን ማንነት ዘነጋን ማለት የራስ በራስ ውድመት ጨዋታ ውስጥ ገባን ማለት ነው፡፡ ወደ ውጭ ተጥሎ መረገጥ፡፡

 

ባጭር ቃል ጌታችን እየነገረን ያለው በኅብረተሰቡ መካከል ግቡ፣ግቡ፣ግቡ፣ ግቡ ዳር አትቁሙ፣ በትዝብት አትመለከቱ እያለን ነው፡፡ ገብታችሁ ያለ ምልክት ያለ ዓላማ ጥፉ ግን አላለንም - ገብታችሁ አስሙ (መልካም ጨው እንደሚያሰማ ሁሉ) ለውጥ አምጡ፣ ስትገቡ ማንነታችሁን አትሽጡ፤ ነፍስ አድን ማንነታችሁን ይዛችሁ፣ ጠብቃችሁ፣ አዳብራችሁ ግቡና አድኑ፤ የሕዝቡን ነፍስ ከሚቦጫጭቁ የክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት አትርፉ ነው የሚለን፡፡

 

ዓለሙ ጣም ያጣ፣ ውሃ ውሃ የሚል፣ የደነዘ የፈዘዘ ነው፤ ይህ ዓለም ግስም ያለ ጨለማ የወረሰው ሕዝቡም በታላቅ ዕውርነት የሚርመሰመስ ነው አታዝኑለትምን? አትታደጉምን? የእኔን ብርሃን አትፈነጥቁምን? የእኔን የሕይወት ጣዕም አታስተዋውቁምን? መዓዛዬንስ አትናኙምን? እያለን ክርስቶስ መድኃኒታችን ይጠይቀናል፡፡ 

Seen 36670 times Last modified on Wednesday, 25 May 2016 07:28
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Latest from Negussie Bulcha