You are here: HomeSocial Issues የምረቃ ድምቀት… የሥራ ወጋገን

የምረቃ ድምቀት… የሥራ ወጋገን

Written by  Friday, 18 July 2014 00:00

መረቀ፣አመሰገነ፣ በጎ ተመኘ፣ እሰይ አለ፣ ጎሽ አበጀህ እደግ አለ፣ ኮንግራ ኮንግራጁሌሽን!

 

የተመጠነ የትምህርት ጎጆ ክፍክፋቱ ተጠናቀቀ፣ ዳር ደረሰ፡፡ የሁለት አራት አመታት የሰበዝ የወስፌ ጥልፍልፍ የምርምር አገልግል ከናፍር በቆዳ ክፈፍ በዲፕሎማ ዲግሪ ተለጎመ፤ ተሸለመ፤ አጌጠ፡፡

 

ጌጡ፣ ሽልማቱ አብሮት የሚመጣው ደስታና ፈንጠዝያውስ ይሁን፤ መገስገሻው የት ነው የተባለ እንደ ሆነ ጭምቱ ደልዳላው ሰክኑ ሥራ ነው፡፡ ብንማር ብንመራመር ልንሠራበት ነው፤ መጽሐፍ ብናስስ፣ ጠጠር ብንዳብስ በኮምፒውተር ገጽ ብናፈጥ አይጥ መዘውሯን ብንጨብጥ ልንሠራበት ነው፡፡ ብር ለምነን ወይ ተበድረን በእግራችን ኳትነን ወይም መኪና ተሳፍረን ብንለፋ ብንጥር ልንሠራበት ነው፡፡ ሥራ የሩቅ ሕልማችን መድረሻ ነው፡፡ ለመማር ሌላም ብዙ ምክንያት ቢኖረን የሥራ ብቃት የማግኘት ዓላማችን ዋናው ይመስለኛል፡፡

 

ሥራ ከሰው መፈጠር ጋር ተያይዞ የመጣ ዕፁብ እድል ነው፡፡ በዘመናዊ ኑሮ አወቃቀር ሰበብና በኢኮኖሚው ግራ ተጋብቶት ምክንያት የተፈጠረው ሥራ አጥነት ሁላችንንም የሚያሳስብ ትልቅ አበሳ ሆኖ ፊታችን ቢደቀንም ሥራ መሥራት ግን የጧት እጣችን ነው፡፡ ልዑል አምላክ ሰብዓዊነት ሲያጎናጽፈን የማሰቢያ ልቡና የመሥሪያ እጆችና ሂያጅ እግሮች አበጅቶልን ነው፡፡

 

የአዳም የገነት ውስጥ ትፍስሕት የሚሟላው በአበቦች ሽታ ብቻ ሳይሆን በእጁ በሚኮተኩተው አፈር መዓዛም ነው፡፡ ሰው ሠራተኛ ፍጡር ነው፡፡ ሥራ መሥራት ርግማናችን ሳይሆን ከሰው ውድቀት በፊት “ምድርን ሙሉአት ግዙአትም” የተባልንበት ቡራኬ ነው፡፡

 

እንዲያውም በእውነቱ የሠራተኛነት ጉልህ አርአያ እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናነበው አምላክ ብርቱ ሠራተኛ ነው፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፍ የመጀመሪያ ግስ “ፈጠረ” የሚል የሥራ መግለጫ ቃል ነው፡፡ የሥነ ፍጥረት መድረክ መጋረጃ ሲገለጥ ልዑል አምላክ በሥራ ላይ ሆኖ ነው የሚታየው፡፡ መዶሻውን፣ መላጊያውን፣ መቆፈሪያውን፣ ማቡኪያውን ባናይም በብርቱ ፈቃደ ቃሉ የሌለውን ወደ መኖር ሲያመጣ፣ ባዶውን በፍጥረቱ ሲያጥለቀልቅ ለስድስት  የትጋት ቀናት ሲሠራ ሲያበጅ ይታያል፡፡ በአርአያ ሥላሴ መፈጠር እንግዲያው ሥራ ወዳድ ዓላማ ያዥ ፍጡር መሆን ነው፡፡ በፍጥረተ ዓለም ውስጥ ፈጣሪን ወክሎ አደራውን ተቀብሎ በተጠያቂነት ስሜት ተግባርን ማከናወን ሰው መሆን ይባላል፡፡

 

ሰውንና ሥራን ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ሦስት መርሖች እንቅዳ፡፡

 

አንደኛ፡- ልዑል አምላክ ሥራውን በዘፈቀደ፣ በግብር ይውጣ ሳይሆን፣ በረቂቅ ጥበብ በጥንቃቄ በፍጽምናና በውበት ሠራ፡፡

 “አቤቱ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው 

ሁሉን በጥበብህ አደረግህ” መዝ 104፡24

አልባሌነት፣ ተራነት፣ በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ የለም፡፡ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ አቅሙ ውሱን ቢሆንም በተሰጠው ችሎታ ሁሉ ጥንቅቅ ያለ ሥራ እንዲሠራ ይጠበቅበታል፡፡

 

ሁለተኛ፡- የሁሉ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉ መጋቢ ቸር አምላክ የሚሠራው ለፍጥረት ሁሉ በተለይ ደግሞ ለሰው ልጆች ጥቅምና ደስታ ነው፡፡

“ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች፣

እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ፣

ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፣

ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል፡፡” መዝ 104፡13-14

 ትምህርት ጨርሰን ሥራ ስንይዝ ራሳችንን መቻላችንን ቀዳሚ ዓላማ ብናደርገውም እንደ ክርስቲያን አካቴው ዓላማችን ሌሎችን መጥቀም ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ለመሆን ወዶ ቃል የገባ ሰው የኑሮው ቅኝት አገልጋይነት እንጂ በሌሎች ትከሻ ላይ መፈናጠጥ አይደለም፡፡

 “…ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም” ኤፌ 4፡28

 

ሦስተኛ፡- ብርቱ ሠራተኛ የሆነው እግዚአብሔር ሥራውን እየታከተ እየተራገመ ሳይሆን በደስታ ያከናውናል፡፡

“የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ይሁን፤

እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይለዋል፡፡” መዝ 104፡31

 

ዝርዝር ረቂቅ የሆነ የመፍጠር ሥራውን ሠርቶ ሲያበቃ የሠራው ሁሉ “እነሆ እጅግ መልካም” ከነበረ ሥራ የደስታ የርካታ ምንጭ እንጂ የትካዜና የጉርምርምታ ወህኒ ሊሆን አይገባም፡፡ ሁሉ ቦታ፣ ሁሉ የሥራ ሁኔታ አስደሳች ሆኖ ባናገኘውም በሰማይ አምላክ ፈቃድ መሰማራታችንን እያሰብንና ከእርሱ ዋጋ እንደምንቀበል እያወቅን በደስታ እናከናውነው፡፡

 

ተመረቀ፣ ሸሚዙን አጠፈ፣ ወገቡን ታጠቀ፣ ለሥራ ተነሣ፣ ደስ እያለው፡፡

 

Seen 7780 times Last modified on Friday, 18 July 2014 13:30
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 62 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.