You are here: HomeOpinionsይኼ የኛ ስብከት፦ መታከም ይኖርበት ይኾን? - Part Two

ይኼ የኛ ስብከት፦ መታከም ይኖርበት ይኾን? - Part Two

Written by  Friday, 05 December 2014 00:00

<< Part One

ምገባ ወይስ ምደባ

ለመልእክት መሳከርና መንጠፍ ሌላው ዋነኛ መንሥኢ ገደብ ያለፈ የምደባአባዜ ይመስለኛል። ከዓመት እስከ ዓመት በተጋባዥ አገልጋይ ብቻ መንጋውን ለመመገብ ማሰብ ተገቢ አይደለም። ማኅበረ ምእመኑ ያለበትን አጠቃላይ ኹኔታ በመመልከት ክብካቤና ምሪት መስጠት ያለባቸው መሪዎች ድርሻ ወደየት አለ? መላው ሰንበት በደርሶ ሂያጅ አገልጋይ ተጣቦስ እንዴት ይዘለቃል? አንዲት ስብከት ይዞ ሀገር ካገር መዞርስ ለመንጋው ድርቆሽ ከሚመግብ እረኛ በምን ይለያል? እንደ ወጥ ቀማሽ ጡል ጡል ብለን በቃረምናቸው የሐሳብ ነቍጦች ላይ ብቻ የተደገፈው ክርስትናችን ረጋ ሠራሽ ቢኾን ምን ይደንቃል? ተሠግዎኣዊ ኅብር የሌለው ስብከት መላምታዊ ነው፤ በመደዴ ግምትና ላይ የተመሠረተ ይኾናልና።

 

ይህ ልማድ የጥርስ ሕመም የሚያሠቃየውን ሰው ሽብልቅ፣ መሮና ዲጅኖ ለተሸከመ ድንጋይ ፈልፋይ አሳልፎ ከመስጠት አይተናነስም። ያነከሰው እንዳይሰበር፣ ሥንጥቁ ተደርምሶ እንዳይፈርስ ብልኀተኛ ጠጋኝ ይሻ የለም ወይ? መጋቢያዊ ዐደራስ ከዚህ ሌላ ምንድነው? በተጋባዥ ደራሽ ምድብተኞች ከዓመት ዓመት የአንዲትን አጥቢያ መድረክ ማጣበብ የምእመናኑን ሕይወት በእርካታ ዕጦት ጥማት ከማንገብገብ በምን ይለያል? ጋሽ ንጉሤ በአጸደ ሥጋ እንደማይኖር ተመላላሽ የሙት መንፈስድንገት መድረክ ላይ የምንከሠት እንዴት እንኾናለን?”62 ያለው ለዚህ ይመስለኛል።

 

 

“ቦ ጊዜ ለኵሉ”

ሌላው ከስብከቶቻችን አንጻር መነሣት የሚገባው ነገር የጊዜ አጠቃቀማችንን ይመለከታል። በእኛ ዘንድ ስብከት በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊተላለፍ መቻሉ ብቻ ሳይኾን፣ ተገቢነቱ መንፈሳዊነት የጐደለው ሐሳብ ተደርጐ የሚቈጠርበት ጊዜና ቦታ አለ። ስብከት ሰዎች ሊሰሙ በሚችሉበት ልክ ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ ሰው መኾናችን ራሱ ሊያስተምረን በተገባ ነበር። በአንድ ክፍለ ጊዜ ውስጥ የአንድ ሰው የመስማት ዐቅም በጊዜ የተወሰነ ነው። ከሰው ሰው ልዩነት ቢኖርም፣ ትኵረቱን ሳያጣ አንድን ሐሳብ በአማካይ ከዐርባ ደቂቃ በላይ እያዳመጠ መቈየት የሚችል ብዙ ሰው እንደማይኖር ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ጥናቶች ባይኖሩስ የራሳችን ማንነት አይነግረንም እንዴ? “ቦ ጊዜ ለኵሉእንዲል መክብብ፤ ለሁሉ ጊዜ አለው” (መክ. 31-8)

 

ዐልፎ ዐልፎ በየመድረኮቻችን የምንመለከተው ግን አሳዛኝ ነው። አንዳንድ ሰባኪዎች ለመግቢያ አንድ ሰዓት ያህል ጨርግደው ከወሰዱ በኋላ፣ ወደ ዋና መልእክታቸውሊገቡ መዘጋጀታቸውን ያበሥራሉ። በዚያ ላይ ሲጀምሩም ኾነ በየመኻሉ፣ እነርሱ በፈለጉ ጊዜ፣ የአምልኮ መዝሙር እያቀጣጠሉያዘልሉናል፤ ያዝሉናልም። ምነው?

 

እንዴት አንድ ሰባኪ አራት ሰዓት ሙሉ መድረክ ላይ ያረፍዳል? ሳስበው፣ ሳስበው ኅልቀተ ዓለም (ያለም መጨረሻ) እውን ከመኾኑ በፊት የመጨረሻውን ስብከት የምታቀርበው አንተ ነህና፣ ዐደራህንየተባሉ የሚመስሉ ሰዎች አሉ፤ ማቋረጫም የላቸውምና።

 

ማቋረጫ ለማጣታችን ደግሞ ሰበብ አናጣም፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ እናመካኛለን። በአንዲት አጥቢያ እንዲህ ኾነ። ጉባኤው ለሁለት ተከታታይ ሰዓት በዝማሬ ካመለከ በኋላ ማስታወቂያ ለመስማት ተቀመጠ። ከመድረኩ ጀርባ በተሰቀለ ሸራ ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ መርሐ ግብሮች በፓወር ፖይንትተለቀቁልን፤ እኛም ተመለከትን። አፍታም ሳይቈይ ወደ መድረኩ የወጣችው የዕለቱ አስተናባሪ እኅት፣ አምልኳችንን እንቀጥላለንየሚል ረጅምና ንዝንዝ የተቀላቀለበት ምክርና ተግሣጽበማኅበረ ምእመናኑ ላይ አወረደችበት። ይህ ዐይነቱ ወቀሣእና ዘለፋ የትም ቦታ የሚደረግ ስለኾነ ለምጄዋለሁና ዐዲስ አልኾነብኝም፤ የገረመኝ ግን አለ፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱን መርሓ ግብር ዝርዝር ነግረውን ነበር። ነገር ግን፣ ልጅቱ እኛ በመንፈስ እንጂ በሜኑ አንመራምበማለት ስታረዳን መስማቴ አስገርሞኛል። በዐናቱም ሌሎችስትል በጠራቻቸው አብያተ ክርስቲያናት ልማድ እንደ ኾነው ከ፣ እስከ በሚባል የሰው ሥርዐትእንደማይመሩ በስፋት አስተምራናለች

 

እንግዲህ አንባቢዬ ሆይ፣ ልብ አድርግልኝ! ለዐዲስ ልደት በሚኾነው መታጠብና በመንፈስ መታደስ ዳግመ ልደትን የተቀዳጀ ሰው፣ የተቀበለው የልጅነት መንፈስ ነው። አንድ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ካላደረበት ከናካቴው ወገኑም አይደለም። የእርሱ ከኾነ ደግሞ በመንፈሱ ከመመራት የሚልቅ ምንም ደስታ የለውም (ሮሜ 814)። በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ተዋጅቶ ከኀጢአቱ በመንጻት የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ የኾነና በቅዱሱ መንፈስ ታትሞ የርስቱን መያዣ የተቀበለ ክርስቲያን፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከመመራት ውጭ ምን የሚያስደስተው ነገር ይኖራል? ምንም! እናም በቅዱስ መንፈሱ እንመራ ሲባል እሺ እንጂ አሻፈረኝ ይል ዘንድ እንዴት ይቻለዋል? ግን አንድ ሐቅ አለ፤ አዎን! ማኅበሩ ለመንፈስ ቅዱስ ምሪት ይለቀቅ፤ በእርሱ ግን አይሳበብ

 

ምላስ ሲያድጥ፦ ቃልና የመድረክ ሥነ ምግባር

ደግሞ ሌላም ልማድ አለላችሁ። የአፍ ዐመል ይኹን የምላስ መሳት ፍርዱን ለአንባቢ ትቻለሁ፤ ለምሳሌ፣ ይህ በየጣልቃው በተለያዩ ቃላትና ሐረጎች የተሞሉ ሐሳቦችን ለማኅበሩ በማቅረብ፣ በለው፣ በዪው፣ ተነጋገሩ፣ ተባባሉየሚሰኝን ነገር እንዴት አያችሁት? “ከጐናችሁ ያለውን እወድሃለሁእያላችሁ ዕቀፉብሎ ነገር ምንድር ነው? አባባሉ በራሱ ክፋት ባይኖረውም እንኳ ተያያዥ መዘዙን አጢነነዋል ወይ? የአሜንታው ነገር ለጊዜው ይቈይ፤ ተመክረን ተዘክረን አሻፈረን ያልንበት ነውና። ለሰማነው እውነት አሜንብሎ የመተባበርን ሐሳብ ብስማማበትም፣ በሰባኪው ውትወታና አስገዳጅ ትእዛዝ እንደ ዶፍ በሚወርዱት አሜንታዎች ላይ ግን ጥያቄ አለኝ፤ ምንም ዐይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የላቸውምና።

 

ከዚህ የከፋ ልማድም አለላችሁ፤ ጌታ እግዚአብሔር የቈሎ ባልንጀራቸውያህል እንዲታሰብ የሚያስገድዱ ደፋሮች በየስፍራው ይደመጣሉ። አንድ ሰባኪ ያሣመረ መስሎት ሲወበራ የተናገረውን አልረሳውም። አምላክ በመንበረ ሥልጣኑ ተቀምጦ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የመጡ ሰዎችን ያስተናብር ነበር አለ። ሁሉንም የፈረንጅ ዘር ከመንበሩ ተነሥቶ እየጨበጠ አሳለፈና፤ የኢትዮጵያዊው (አፍሪካዊው) ተራ ሲደርስ ግን በዙፋኑ ተመልሶ ተቀመጠ። ኢትዮጵያዊውም ተናቅሁብሎ ያለቃቅስ ጀመር። ፈጣሪም፦ ቆሜ ያልተቀበልኩህ በንቀት ነው ብለህ እንዳታስብ፤ እናንተን በወንበር ጕዳይ ስለማላምናችሁ ነውሲል እንደ መለሰለት ሰባኪው በመቀባዠር አስረዳ። በዚህ ምሳሌ የሣቁ እንጂ የተሣቀቁ ወገኖች ለማየት አልታደልሁም። ከእኔ ርቀው የተቀመጡና የተሣቀቁ እንደሚኖሩ ግን ርግጠኛ ነኝ።

 

አንድ እውነት ግን አለ፤ ይህ የባልቴቶች ተረት አስተማሪ ሳይኾን አክሳሪ ነው (አሁን እንኳ ለአስረጅነት ለጻፍኩት ምን ያህል እንደ ተሣቀቅሁ!)። ቃል በበዛበት በዚያ ከንቱ ነገር አይጠፋም። አማረብን ብለን በምንዘባርቀው መካከል ምላሳችን አድጦት መለኮትን ወደ መጻረፍ አዘቅት እንዳንንሸራተት ብርቱ ጥንቃቄና ቍጥብነት ማሳየት ይኖርብናል። ወንጌላዊ ደሉ ጸጋዬ በአንድ ወቅት፣ በመለኮትና በመለኮቴ መካከል ልዩነት መኖሩን መረዳት ይኖርብናልበማለት በጥበብ የሰነዘረው ምክር ሊጤን የሚገባው በእንዲህ ያለ ጊዜ ይመስለኛል።

 

በተጨማሪም የማኅበሩን ክብር የሚዳፈሩ፣ የማመንና የማሰብ ነጻነቱን የሚገዳደሩና በእግዚአብሔር ቃል የተሰጠውን የትኛውንም መልእክት ፈትኖ የመቀበል ዐርነቱን ባፍጢሙ ደፍተውሕዝብ የሚያስበረግጉ ጥቂት አይነኬዎችም እየከበቡን ነው። በአረማውያን አምልኮ እንደ ተለመደው ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኅብረት የእንካ-በእንካ መስተጋብር ሊያደርጉት የሚዳዳቸው እንደ አሸን ፈልተዋል፤ በኪሳችሁና በቦርሳችሁ የያዛችሁትን ሁሉ ለእግዚአብሔር ካልሰጣችሁ ነቀዝ ይለቀቅባችኋልብሎ ማሟረትን የትኛው መጽሐፍ ነው ያስተማራቸው? የሠርግ ቤት ድንኳን ሰባሪን እጅ ከፍንጅ እንደ ያዘ ቈራጥ ዘብ አድማጩን፣ ካልፈለግህ ተነሥተህ ውጣእያለ የሚዳንት ሰባኪስ ምን ሊባል ነው?

 

ሌሎች ደፋሮች ካልገባህ አይገባህም፣ ሊገባህም አይችልምሲሉ አልሰማችሁም? “በሩን ዝጉ፤ አንድም ሰው እንዳይወጣ ከልክሉ፤ እኔ ሳልጨርስ ተነሥቶ የሚወጣ ካለ አጋንንት ስላሉበት አንጠልጥላችሁ መልሱትማንም ሰው እንዳይንቀሳቀስ በኢየሱስ ስም አስሬአለሁየሚሉና ሌሎች አስበርጋጊ ማስፈራሪያዎችን በመጠቀም በድንገት የሴት ወግ የደረሰባትን ማሳቀቅ፣ በኵላሊት ሕመም ወይም በሌላ አስገዳጅ ምክንያት ቶሎ ቶሎ ወደደጅ ለመውጣት የተገደደን ሰው ማስደንበር ምን ዐይነት መጋቢነት ነው?

 

አሜን የማትሉ ከኾነ ጉባኤውን ጥዬ እወጣለሁ፤ ዕዳ የለብኝምእያለ የሚገበዘውን ስትሰሙስ አትሣቀቁም? “ኑሮ ተወደደ ብላችሁ የምትጨነቁ አላችሁ፤ ቀድሞውኑስ መች ኖራችሁና ነውየሚልን ሰባኪ ምን እናድርገው? በአጠቃላይ፣ በመድረክ ላይ በተናገሩትና በሠሩት የትኛውም ዐይነት ተግባር በእግዚአብሔርና በሰው የመጠየቅን ኀላፊነት ከላያቸው ላይ አምዘግዝገው የጣሉ የሚመስሉ ሰባክያን ሀገሩን ሞልተዋል። በአደራ በተሰጠን ምስባክ ላይ ባለቤት የሌለው ይመስል ያሻንንን ሁሉ ለማድረግ መዳፈራችን በጣም አሳዛኝ ክንውን ነው።

 

የመድረክ ሥነ ምግባር የሚባልን ወግ ለሰባኪዎቻችን የሚያስተምርልን አባት በዚህ ሀገር የለም ወይ? የጫማቸውን ሶል ወደ ሕዝብ እያሳዩ የሚፈነጥዙትን፣ ቦታ አልበቃ ብሏቸው ላባቸውን እያዘሩ የሚራወጡትን፣ ገመድ አልባ የመነጋገሪያ መሣሪያዎችን በመጠቀም እየለፈለፉ በሕዝብ መካከል ገብተው፣ ባልተገባ መንገድ ታዳሚውን የሚነካኩ ደፋሮችን መምከር አይገባም? “በቃሉ ላይ ቁሙየሚል ሐሳብ በምሳሌ ለማስረዳት በመጽሐፍ ቅዱሱ ላይ በሁለት እግሩ ቆሞ የሚያስተምረውንምን እንበለው?

 

ለአንዳንዶቹ ደፋር ሰባክያን ጸያፍና ብኩን ቃላትን (ምሳሌ ባንጠቅስም) በመድረክ ላይ እንዳሻቸው ለመናገር መብት የሰጣቸው የትኛው ጐበዝ ነው? ተሳዳቢዎቹስ? በቀጥታ የሚሳደቡት ማለቴ ነው። ሕዝቡ አስቀድሞ እግዚአብሔርን፣ ቀጥሎ ቃሉን፣ በዚያ ላይ ጨምሮም አገልጋዮቹን አክብሮ ከእግራችን በታች ስለ ተቀመጠ አላግባብ መዘለፍ አለበት ወይ? ሕዝቡ ከስሕተቱ እንዲታረም፣ ከዐመፃው እንዲመለስና ንስሓ እንዲገባ በእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ መገሠጽ ይገባዋል፤ ይህ አያከራክርም። ነገር ግን፣ እያበሻቀጥን እንድንዘልፈው የላከን ማን ይኾን? እንዲህ ዐይነቱን የዐወቅሁሽ ናቅሁሽግልምጫና ማንጓጠጥ እነዚህ ሰባክያን ከወደየት ነው የተማሩት? ስድብ ከመድረክ ላይ ሲናገሩት ቅዱስ ይኾናል እንዴ? ኀይሉ ቸርነት የዚህ ሁሉ መንሥኤ መድረክ የተከበረ የአምላክ ቦታእንደኾነ ካለመረዳት እንደሚመጣ ይናገራሉ።

 

… ከችኩልነት ወይም ከጥድፊያ የጸዳ ንጹሕ ፍርሃት በውስጣችን እንዲኖር የበኩላችንን ጥረት ማድረግ [አለብን]። መድረክ ክቡር የኾነው ባለቤቱ ፍጡር ሳይኾን ፈጣሪ በመኾኑ ነው። … በድፍረት ‘እችለዋለሁ፣ የረጅም ጊዜ ተመክሮ አለኝ’ በሚል ትምክህት የሚከወን ማንኛውም ድርጊት የአምላክን መድረክ እንደ መዳፈር ወይም እንደ ማቃለል ይቈጠራል። … መገለጥ የሚባል አውራ ክሥተት በመንፈሳዊ ርምጃ ውስጥ እንዳለ መረሳት የለበትም። … በችሎታችን ከመታመን በችሮተው ለመደገፍ ንጹሕ ፍርሃት ቢኖረን ለመድረኩ አክብሮት ሰጠን ማለት ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ግንዛቤ በሁሉ ዘንድ አይገኝም።63 

 

ኑሮ የከዳው ቃል

ሌላው ችግራችን ደግሞ የሕይወትና የትምህርት መጣረስ ነው። ርግጥ ነው፣ ከቃል ይልቅ ኑሮ ጮኾ ይናገራል። በመድረክ ላይ የምንጮኸውን ያህል ኑሮአችን ካላወጀ፣ ይልቁኑም ሌሎች እንዲኖሩበት ጮኸን ያስተላለፍነውን እውነትከመድረክ በታች በኑሮአችን ጥፋት የምንቃወመው ከኾነ፣ ከነዚያ ዝነኛ ፈሪሳውያን መለየታችን ምኑ ላይ ነው? ከመድረክ ላይ እጆቻንን እያወናጨፍን ሰለሌሎች ለውጥ እንጮኻለን፤ ነገር ግን የራሳችንን ሕይወት በተናገርነው መልእክት ካልገራነው ኪሳራ ነው። ሊዎ ቶልስቶይ ከረጅም ጊዜ ትዝብት በኋላ በአንድ ወቅት የተናገረው እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ይመስለኛል። እያንዳንዱ ግለ ሰብ የሰውን ዘር ሁሉ ስለ መለወጥ አጥብቆ ይጨነቃል፤ ነገር ግን ራሱን ስለ መለወጥ አስፈላጊነት የሚያስብ ሰው ያን ያህል አይደለም” ብሎ ነበር። ወይ አለመታደል!

 

ወንጌላቱ እንደሚያስተምሩን፣ ጌታችን ኢየሱስ በተቃዋሚዎቹና በቃል ሊያጠምዱት በሚያሸምቁበት ክፉ ሰዎች አሽክላ አልተያዘም ነበር። ጻፎችና ፈሪሳውያን በአፉ የተናገረውን ሊነጥቁ ሲያደቡ(ሉቃ. 1153) ያልተሳካላቸው፣ በቃልና ኑሮው ምንም ዝንፈት ስላልተገኘበት ነበር። እንዲይዙት የተላኩ የአይሁድ ሸንጎ ሎሌዎች ከሰሙት በኋላ በትምህርቱ ተመስጠው ነበርና፣ እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም (ዮሐ. 746) በማለት የላኳቸውን አስደንግጠው ነበር። ስለዚህ ወዳጅ ጠላት በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ(ሉቃ. 2419) ከማሰላሰል ማምለጥ አልተቻለውም። ኢየሱስን ለማጥፋት የቋመጠው፣ ነገር ግን ኑሮውና ቃሉ የተሳከረበት የጸሐፍትና ፈሪሳዊ ወገን ግራ የተጋባው ታይቶ የማይታወቅ የቃልና ሕይወት ጥምረት ዐመፃና የግብዝነት እርሾ በከደነው ዓለም መካከል በተሠግዎ ብርሃን ሲመላለስ በማየቱ ነበር። ሉቃስ ይህንን እንደዚህ ዘግቦልናል፡-

 

ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ ታላላቆችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፥ የሚያደርጉበትንም ዐጡ(ሉቃ. 1947-48)፤ ለምን? ያልን እንደኾን ኢየሱስ ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና(. 48)። ስሙ ቡሩክ ይኹን!

 

ዛሬም ከወንጌሉ ሰባክያን የሚጠበቀው ነገር ይኸው ነው—የቃልና ኑሮ መጣጣም። አንድ ሰባኪ መናገር ብቻ የለበትም፤ ትምህርቱን በኑሮ መግለጥ አለበት። የሰባኪው የኑሮ ጠባይ ከሁለት ነገሮች አንዱን እውን ያደርጋል፦ ወይም ስብከቱን ሰልቦ ያመክነዋል፤ አሊያም ለስብከቱ መልእክት ሥጋና ደም ያለብስለታል።64 ማኅበረ ምእመናኑ መንፈሳዊ ብስለት እንዲኖራቸው ተግቶ እየተናገረ፣ ከሕይወቱ የመንፈስ ፍሬዎች የጐደለው ሰባኪ ጥረቱ ውሃን እንደ መውቀጥ እንቦጭብቻ ነው።

 

ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስና ቲቶን ሲመክር በክርስቲያናዊ ባሕርያት ለቅዱሳን አርኣያ እንዲኾኑ ነግሯል (1ጢሞ. 412፤ ቲቶ. 27)። ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ለመንጋው ምሳሌ እንዲኾኑለት ይመክራል (1ጴጥ. 53)። ሌሎች ያደርጉት ዘንድ የወተወትነውን ነገር እኛ እየሸሸነው፣ በስብከታችን የተጸየፍነውን መልሰን ካደረግነው፣ ምን ያህሎቹን እንዳሰናከልን ጌታ ብቻ ነው የሚያውቀው። አንድ የማሀታማ ጋንዲ ንግግር አለ፤ ክርስቶስን እወደዋለሁ። ግን ክርስቲያኖች መሲሐቸውን ስለማይመስሉ ክርስትናን አልሻውምየሚል። ከዚህ በላይ ማሰናከል ወደ የት አለ?

 

ዓለማችን የተራበችው ሐቀኛ ሕይወት ነው። እውነተኛ ሕይወት ሰዎችን ይማርካል፤ ማስመሰል ግን ያርቃቸዋል። በጠርጣራነት ሞገድ ስለ ተመታ በክርስትና ላይ ጥላቻ ዐድሮበት የነበረው ፈላስፋው ዴቪድ ሂዩም፣ በለንደን ጐዳና ላይ ሲጣደፍ ጓደኛው ያገኘውና ወደየት ነው የምትከንፈው?” ሲል ይጠይቀዋል። ሂዩም ሲመልስ ጆርጅ ዋይትፊልድ ሲሰብክ ለማዳመጥ እየሄድሁ ነውይለዋል። ጓደኛውም በአግራሞት ስሜት ተሞልቶ፣ እንዴ፣ ሂዩም! ዋይትፊልድ የሚሰብከውን ታምናለህ እንዴ?” በማለት በጠየቀው ጊዜ፣ ሂዩም፣ ኧረ በጭራሽ አላምንም! ነገር ግን ዋይትፊልድ የሚናገረውን ያምናልና ነው65 ሲል መለሰለት። ለመኾኑ በስብከታችን አጽንዖት በመስጠት የምንናገረውን ነገር እኛው እናምነዋለን የምናምነው ከኾነ ከኑሯችን ውጭ ደምቆ የሚታይበት አደባባይ የለውም።

 

 

62 ንጉሤ ቡልቻ፣ የሰባኪው ጥሪና ባሕርይ፣ ያልታተመ ጽሑፍ፣ ላንግሃም ፕሪቺንግ፣ ደብረ ዘይት 1997 ዓ.ም.

63 ኀይሉ ቸርነት፣ መድረኮቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ (አዲስ አበባ፡- ራእይ፣ 1997 ..) 52

64 J. H. Bavinick, An Introduction to the Science of Missions (Philadelphia: Prysbyterian and Reformed, 1960) 93.

65 James Black, The Mystry of Preaching (London: Marshall, Morgan & Scott, 1977) as quoted in John Stott, The Challenge of Preaching (Carlisle: Langham Preaching, 2011) 72. 

 

Seen 8934 times Last modified on Friday, 05 December 2014 05:40
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 54 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.