You are here: HomeOpinionsእንባዬን ተዉልኝ

እንባዬን ተዉልኝ Featured

Written by  Friday, 09 June 2017 13:50

ወገኖች፥ አንዳንድ ጊዜ አልቅሱ፥ አልቅሱ አይላችሁም? የተትረፈረፈ የእንባ ምንጭ አይናፍቃችሁም? የምን የእንባ ዚቅ ነው የምታወራው ካልተባልሁ ነው እንግዲህ። “የሣቅ ነው ዓመቱ” በተባለበት ዘመን ልቅሶን ምን አመጣው? ዐውቃለሁ፤ አንዳንድ አንባቢዎች “ውይ፥ ሲያሳዝን! ... ያልገባው ምስኪን! ... ዝም ብሎ ያላዝናል ...” ማለታቸው አይቀርም። “የከፍታ ዘመን”፥ “የመስፋፋት ዓመት”፥ “የጥርመሳ ጊዜ”፥ “የማለፍና የመብረር ቀናት”፥ “የእልልታ ወራት”፥ “የብዝበዛ ዓመት”፥ “የመውረስና የመሻገር ዘመን”፥ “የሞገስና የቅባት ዓመት” ወዘተ. እየተባለ በተነገረበትና በሚነገርበት ዐፍላ እብደት ውስጥ “እናልቅስ ብሎ ጥሪ ምን ይሉት ቀፋፊ ንግርት ነው?” ይሉም ይኾናል።

 

ግና ለምን አናለቅስ? በኾነልንና ባለቀስን፤ ጨምረንም በአነባን እላለሁ። እውነት በአደባባይ ሲወድቅ፥ ማለዳ ለምልሞ የታየው ምሽት ላይ ሲደርቅ የእንባ ማድጋ እንሰብራለን። በበጎች መስክ ተኵላ ሲርመሰመስ፥ ግርግሩ በዝቶ ነውር በአናት ሲፈስ ዐመድ እንነሰንሳለን። ዘመን ከፍቶ ቃሉ ሲደፈር፥ ጻድቅ ቀን በሰጠው አባጭ ሲሰበር፥ ማቅ እንለብሳለን። የሰው ምንነቱ በሀብት ሲለካ፥ አምልኮተ እግዚአብሔር ድል ባለ የዳንኪራ መንጦልጦል ሲተካ መሣቅ ይገኝ አይመስለኝም። ድኾች ሲነቀሉ፥ መሪዎች ሲበድሉ፥ ባለ ጠጎች ሲፏልሉ፥ ለእውነት የቆሙ ሲገለሉ ... እንባ ማፍሰስ ቢያንሰን እንጅ ለምን አይባልም። ፍርድ ሲዛባ፥ ግፍ ሲገነባ፥ ስንፍና ሲናኝ፥ ትጋት ሲናናቅ እንዴት ዝም ይባላል? “ዐይኖቻችንም እንባ እንዲያፈስሱ፥ የዐይናችንም ሽፋሽፍቶች ውሃን እንዲያፈልቁ ፈጥነው ለእኛ ልቅሶውን ይያዙ” (ኤር. 9፥18) ብለን የአልቃሾችን መነሣት እንመኝ ይኾናል።

 

ለምንስ አንመኝ? በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ መኼድ ቀላል ነገር እንደ መሰለችው እንደ አክዓብ፥ በኤልዛቤል ክፋት እየተነዱ፥ ናቡቴን በገዛ ርስቱ ላይ ደሙን ከድቤ ጋር የሚቀይጡ “ጊዜ የሰጣቸው ቅሎች ዐለት ድንጊያ ሲያንኰታኵቱ” ዐይን መርጠቡ መች ይቀራል። አያለቅሱምን? መስቀል ባልፈተነው ጕብዝና የሚያቅራሩ አንዳንድ “መሥራችና ባለ ራእዮች” በየሰፈሩ መዓት ሲመሠርቱ ዐይን አይቈጠቍጥም? ቀለብ የሚዛቅበት እስከ ኾነ ድረስ፥ መንገደኛው ኹሉ ከነኑፋቄው የቅዱሳንን ጉባኤ ሲወር አይተክዙም? ትዳር ሲፈርስ፥ ቤት ሲታመስ፥ ሕፃናት ጎዳና ወጥተው ሲበተኑ አይቃትቱም? መበለቶች ሲገፉ፥ ደኻ አደጎች ሲሰናከሉ ልብ እንዴት ጸጥ ይላል? የማኅበረ ሰቡን ድጋፍ የሚጠባበቁ ድኵማን ሲዘረፉ ምላሻችን ዝም ይኹን? ቀዳሚባለ ውለተኞች ከታሪክ መዝገብ ሲፋቁ አይጐመዝዝም? አረጋውያን ሽበታቸው ሲደፈር አያስተክዝም? ቀን የሰጠው ጨካኝ፥ ተሽቀዳድሞ “የመሰዊያውን ቀንድ ስለ ያዘ”፥ በንጹሐን ላይ ሲያላግጥ አንጀት አይታወክም? በወገኔ ሴት ልጅ ድንኳን ግፈኛ እንደ እሳት መዓቱን ሲያፈስስ ልብ በውስጥ አይገላበጥም? ድሪቶ በለበሰ ዘመን የአገር-ዐደራ-በል የምሁር ገመሬ በአደባባይ ዋሽቶና በሕሊናው ላይ በሆዱ ተኝቶ ሲመላለስ አሽቈልቊዬ ሮጬ አቀበት ቧጥጬ የእንባ ዘር ብበትን ሰሚ አይኖረኝም ወይ? ሰማይ ዝናብ ማውረድ ብቻ ሳይኾን የረጩለትን እንባም ይቀበል የለም ወይ (ዘጸ. 3፥8)? ሕጻናት “ታርደው ሲበሉ” (ማለቴ፥ “አንድ ፍሬ” ሕፃናት ክቡር ሥጋቸው በብር ተተምኖ ትፋታም ኹሉ ሲያድርበት) ማልቀስ ያልቻለ ዐይን ለምን ተፈጠረ? እንጀራ ይጠግቡ ዘንድ “ነፍስ ያላወቁ” ዐፍላዎቻችንን በገፍ እያስጫኑ የሚነግዱ ዐረመኔዎች በዐመፃ ደመወዛቸው ሲሰቡ ያልዘገነነው ነፍስ ምኑን አለ ይባላል? ከሚያቃጥል ብርቱ የረኃብ ትኵሳት የተነሣ ቍርበታችን አልከሰለም? ዐጥንታችን አልገጠጠም? ውበታችን አልሟሸሸም? የነድንቡሼ ፊት በክሣት አልሞገገም? ዐንገታቸው አልሠገገም? ምኑ ቅጡ! የእንባ ማድጋው ያልተሸነቈረለት፥ አወይ ሞቱ!

 

መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያለቅሱ ሰዎች የራቀ አይደለም። ከላይ ባነሣናቸው ችግሮች ጊዜ ሊደረግ ስለሚገባው ነገር ይመሰክራል። ኤርምያስ ነቢዩ፥“ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዐይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ” (ሰቈ.2፥11) እያለ አምጧል። አለቆች ጊዜ ላመጣው ፈሊጥ እያሸበሸቡ ለበኣል ሲያረግዱ ቅስም ይሰብራል። መራር ዘመን ሲመጣ ማልቀስ ምርጫ እንጂ አማራጭ አይደለም፤ ወደ ሰማይ ይጮኹታል፤ ወደ ልዑል ያለቅሱታል።ለባቢሎን ምርኮ ተላልፎ በተሰጠው እስራኤል ላይ በወረደው መዓት ለተበሉ ልጆቿ ራሔል አለቀሰች ብቻ አይደለም፤ መጽናናትን እምቢ አለች እኮ! የሉምና (ኤር. 31፥15፤ ማቴ. 2፥17-18)። ትውልድ የሚያመክን ጨካኝ እንደ አሸን ሲፈላ ወደ ልዑል እግዚአብሔር የሚደርስን እንባ ይረጩታል። ውለታ ቢሱ ፈርዖን ትናንትን ረስቶ በማበድ ነገን የሚያጨልም ዐዋጅ ሲደነግግ (ዘፍ. 41፥56-57፤ 50፥20፤ ዘጸ. 1፥8-22)፥ “እኔን ከንበል ያርገኝ” ባይ ሙሾ አውራጅ ያስፈልጋልማ። ሄሮድስ ስለ ሥልጣኑ ሥሥት በርግጎ ሲጨክን፥ በሰይፍ ስለቱም ንጹሐንን በክፋት ሲያርድና ጨቅላውን ኹሉ እየመተረ ለመደምሰስ በዘንዶ ቍጭት ተሞልቶ በአሸዋ ላይ ሲቆም የቅዱሳንን ኤሎሄ ወደ ብርሃን አባት ይልኳል። መሲሑን እገድላለሁ ባይ ደንፍቶደኻ በመደዳ በእሳት ሲማግድ ሰማያት እንዲቀደዱ መጠባበቅ የወግ አይደለምን? ሰማይ ያያል፤ በሰማያት ሚዛን የሚሰፈር እንባ አለ።

 

ሰቈቃወ ኤርምያስ የተባለ አንድ የእንጕርጕሮ መጽሐፍ በቅዱሳት መጻሕፍት የቀኖና ዝርዝር ውስጥ የተካተተው በከንቱ አይመስለኝም። ኤርምያስ በኢየሩሳሌምና በነዋሪዎቿ ላይ የተነበየው ሲከሠት ያየ ብቻ ሳይኾን መከራውንም ዐብሮ የጨለጠ ነቢይ ነበር። የባቢሎናውያን አሠቃቂ ግፍ በሕዝቡ ላይ ሲወርድ፥ ቅድስት ከተማ ስትፈርስ፥ መቅደሱ ሲናድ እያየ በገዛ እንባው ውስጥ ሊሟሟ ምንም አልቀረው ነበር። ይህ አልበቃ ብሎት “ስለታረዱት ወገኖች ቀንና ሌሊት አለቅስ ዘንድ፥ ምነው ራሴ የውሃ ምንጭ በኾነ! ምነው ዐይኖቼ የውሃ መጕረፊያ በኾኑልኝ!” (ኤር. 9፥1 ዐመት) በማለት ተማጽኗል። በውኑ፥ እያነቡ ባሉበት ገና ማልቀስን ይመኟል?

 

ማልቀስ ይህን ያህል ብርቅ ነው ወይ? አትሉኝም፥ መቼም። ርግጥ ብርቅ አይደለም፤ ግን አንዳንድ ጊዜ ይብሳል። አንተ ባለፈው “ይኸ፥ ቢቢሲ አበዛው፤ ጕድለታችንን እየለቃቀመ ገጽታችንን ለማበላሸት ይዳክራል” በማለት የተበሳጨኸው ሰባኪ፥ ይሰማሃል? አንተ እኮ! ገጽታችን የሚያማልልህ ቦሌ፥ ሲ.ኤም.ሲ፥ ጃክሮስ፥ ቤቴል፥ አያትና ... ተመሳሳዮቹ ሰፈር ኾነህ ስለምታስበን ነው። “የመጐብኘት ዘመናችሁን አላወቃችሁትም” ብለህ የምትነድፈን። ጕብኝቱ ምኑ ላይ ነው? አንድ ሰውዬ መጥቶ፥ “አገራችንን ካልባረከ ወዮላችሁ” በማለት የምታስፈራራን እንዴት ብታየን ነው? ራስህን እንደ ነቢይ ቈጥረህ ኵራት የሚያንጠራራህ ምን አቅምሰውህ ነው?

 

ርግጥ ስለ ተሳካላቸው ሰዎች ደስ ይለናል፤ እንኳን ኾነላቸው። ግና ማኅበራዊ ድቀት ስላቈራመዳቸው ወገኖች በጸሎት የሚማልደውን ሰው ዐይን አንጓጕጥም። ማኅበሩ እያቃሰተ ሆዳችን ስለሞላ “ጅብኛ አንዘምርም”። የፍንጠዛ ጡዘትን የሚያረግቡና ኀዘነ-ልቡናን የሚያንቀሳቅሱ ብዙ ነገሮች በዙሪያችን አሉ። ምሳሌ እንምዘዝ እንዴ? ይኸውላችሁ፥ እኔ ሰውዬው (ወይስ ልጅየው?) ላለፉት ዐምስት ዓመታት ቈሼ ከሚሉት ዘግናኝ ሰፈር ብዙም ሳልርቅ እስሩ ነው የምኖር፤ ቤት ይሉትን መጠለያ እከራይ ዘንድ ተሰድጄ፥ ኼጄ። አንዳንድ ቀን ታዲያ ሲሳካልኝ ብድግ እልላችሁና እየተወናከርሁ ወደ ቈሼው መኻል አመራለሁ፤ በያን ሰሞንም ብቅ ብዬ ነበር። “ምን ይጠበስ?” አትሉኝም፥ መቼም። ኀዘንና ብግነት አንጀቴን የጠበሰኝ በመኖሩ እሱን እነግራችኋለሁ።

 

እናማ፥ ይኸ የአገር ጕድፍ መጣያ ገሃነም ስንት የምድር ላይ ጕድ አዝሏል መሰላችሁ።የዐዲስ አበባ ግማትና ክርፋት በዘመናዊ ማጓጓዣ እየተጫነ መጥቶ ቈሼ ላይ ይዘረገፋል፤ ላለፉት አርባ ዓመታት የተከማቸውን የግባስ ተራራ ጨምሮ ማለት ነው። በዚህ የምድር ላይ ገሃነም ጥንብ አንሳ ይራኰትበታል። የውሻ መንጋ ይልከሰከስበታል፤ የምድር ሞገጥ ይንጐዳጐድበታል። ደግሞም፥ የእኔና የእናንተን የዕድሜ እኩዮች ጨምሮ፥ ወጣት፥ አሮጊት፥ ሽማግሌ፥ ጐረምሳና ሕፃንን ያካተተ የሰብአዊ ፍጡር መንጋ፥ ሆድ የተባለውን የውርደት ጕድጓድ ለመድፈን፥ ጥራጊና ፍርፋሪ ይሻማበታል። የተቈረሰ መሬት የሚመስሉ ጕስቍል ልጆች ከወዲያ ወዲህ ይንከላወሱበታል። እና ይህን ማየት አያምም? ኹለንተናን አያጥወለውልም? አኹን እንኳ ሳስበው ዐይኔ ጭጋግ ለበሰና ዐረፈው ... ።ይኸን ኹሉ የነፍስ ማንቋረር ለምንሰማው፥ የልማት ሰባኪው የሚነግረን ዜና “እጅ ያስቈረጥማል”። ዘመነኛው ሰባኪም፥ የእንባ ቆቤን አውልቄ ከእልፍኜ ከመመሸግ ሊያዘናጋኝ ሲሻው፥ “ድኽነት ወንጀል ሲኾን፥ ድኻ መኾንም ኀጢአት ነው” እያለ ይሳደባል። “እያለቀሱ መጸለይ የእምነት ጕድለት ነው፤ ጥሪአችን እያዘዝን ለመፍጠር ነው” በማለት “ይፈላሰማል”። ጌታው! ምነው ታዲያ ወደ ቈሼ መጥተህ ቍራሽ “አትፈጥርም”? ይህን ኹሉ ወፈ ሰማይ “እንደ ፍጥርጥርህ” ብለህ የምትፈጥረው ምንድር ነው? ከየቦታው በብልጠትም በድፍረትም በዘገንኻቸው የመንፈስ ምርኮኛ “ምእመናንህ” መካከል በመመላለስ “ድኻ በመኾናችሁ ንስሓ የምትገቡ እጆቻችሁን አውጡና ውጡ” ማለትህ አንተን ባይዘገንንህም እኛን ማስለቀሱ ይቀራልን? አወይ መሳትና ማሳት! የአታላዮች መንጋ በልባቸው እልኸኝነት በመኼድ የትምህርት አባቶቻቸው ያስተማሯቸውን ክፋት ተከተሉ። ይህም ኹሉ ኾኖ ገና በጭፈራው እያለከለክን እንገኛለን። እሽሽ ... ትንሽ ጸጥታ፥ ትንሽ ጽሙና እንዴት እናጣለን?

 

ለነገሩማ መሣቅን ማን ይጠላል? የኀዘን ማቅ መከናነብ ምኑ ይወደዳል? የምስጋና መጐናጸፊያ ቢገኝና የመጽናናት ዘመን ቢመጣ የማይፈልግ ሰው የለም። ይኾነኝ ብሎ በትካዜ ለመቈራመድ የሚተጋ ጤነኛ ሰው ማግኘት ይከብዳልና። ኀዘን እኮ ልብ ያደክማል፤ ጕልበት ያልፈሰፍሳል። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ያልኾነ ኀዘን ጭራሽ ሞትን ያመጣል (2ቆሮ. 7፥10)። ንስሓ አልባ ኀዘን የደጋ ውርጭ እንዳጨማደደው ጮርቃ-እሸት መንፈስን ክው አድርጎ ባዶ ማስቀረቱን አላጣነውም። ወደ ሕይወት ጌታ መማለል የማይታይበት ልቅሶ ብቻውን ምንም አይፈይድም። ነገር ግን ወደ ልዑል እግዚአብሔር የሚላክ ምልጃ፥ የድረስልን ምጥንታ ሰማያትን ዝቅ ያደርጋል፤ ልብን ያለዝባል፤ ታሪክ ይቀይራል፤ ሕይወት ይለውጣል፤ ... ብለን እናምናለን።

 

ዳሩ ግን እግዚአብሔር በምሥጢር የሚያነቡትን ወገኖችም የሚያይ አምላክ ነው፤ እርሱ ሕመማችንን ይመለከትልናል። ፍላጎታችንና ጥማታችን የሚገባው እንጂ “ምን ግዴ” ባይ ቸልተኛ አምላክ አይደለም። እንዲያውም ዐብሮን ባያለቅስ አይደል! ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት የጻፈው በዋዛ አልነበረም፤ “በጭንቃቸው ኹሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ኹሉ አንሥቶ ተሸከማቸው” (ኢሳ. 63፥9)። ልክ እንደ አባት ማለት ነው፤ በጭንቃቸው ተጨነቀ! ቅዱስ ስሙ ቡሩክ ይኹን።

 

በመጨረሻ አንድ ታላቅ ተስፋ እንዳለን መርሳት አይገባንም። ይኸውም፥ የቅዱሳን እንባ ለዘላለም ይታበሳል። በሕመምና በኀዘን የተከበብን ከመኾናችን የተነሣ፥ ወደ ፊት ጨርሶውኑ የማናለቅስበት ዘመን ይመጣል ብሎ መናገር ተምኔታዊ ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን ጌታ ለሚወዳቸው ባዘጋጀው በእግዚአብሔር ዘላለም ቅዱሳን እንባቸው የሚታበስበት የከበረ ስፍራ ይጠብቃቸዋል። በዚያ ኀዘንና ልቅሶ የሉም፤ የማያቋርጥ ደስታና ሐሴት የሰፈነበት የዐዲስ ዓለም ሥርዐት በክርስቶስ ዳግም መመለስ እውናዊነቱ ይደመደማል።

 

በዚያ ልቅሶ ሊገኝ ቀርቶ መኖሩን እንኳ አንመኘውም፤ አስፈላጊ አይደለምና። በዚያ የሀለዎተ እግዚአብሔርን ክብር እያደነቅን ሐሴት በምናደርግበት ፍጹም የደስታ ዓለም እንኖራለን። እርሱ የርስታችን ዕድል ፋንታና የማይጠፋ ሕይወታችን ምንጭ ነው። ጕድለት የለም። እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “እንባዎችንም ኹሉ ከዐይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይኾንም፤ ኀዘንም ቢኾን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኾንም፤ የቀደመው ሥርዐት ዐልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ” (ዮሐ. 21፥4)። አሜን! ለይኩን፥ ለይኩን! እስከዚያው ግን፥ እንባውን ተዉልን።

 

ርግጥ፥ የታመቀ እንባ ፈንቅሎ መውጣቱ ፈውስ ነው። ጊዜም የሚሰጠው ፈውስ ሊኖር ይችላል። ጊዜ ኪሳራችንን ሊያካክስልን ባይችልም፥ የኀዘኑን የመውጊያ ብረት ግን ለጊዜው ሊያዶለዱመው ይችላል። ኾኖም ከጊዜ ይልቅ በኀዘን የቈሰለ የሰዎችን ልብ የመፈወስ ታላቅ ኀይል የተሰወረው ከራሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በምንቀበለው መጽናናት ውስጥ ብቻ ነው። ጊዜና እንባ የማያጥቡት የነፍስ ጕድፍ ሞልቷል። ጥልቅ እፎይታ እግዚአብሔር በጸጋው ሲዳብሰን ብቻ ይገኛል። እምባውን ተዉልን ማለታችን ለዚህ ነው። ለምን ቢባል፥ “በዚህ ዓለም በሚያየው መከራ ሰበብና በገዛ ራሱ ኀጢአት ምክንያት ልቡ የተሰበረ ሰው፥ ምንኛ ዕድለኛ ነው፤ ምክንያቱም፥ በፍጻሜው፥ ከኀዘኑ ውስጥ የአምላኩን ደስታ ያገኘዋል።”


ከመጽሐፉ የተወሰደ -እሑድ ሰኔ 18-2009 በዘፀአት አፖስቶሊክ ሪፎሜሽን ቤተክርስቲያን 8፡30 በይፋ ይመረቃል።

Seen 5023 times Last modified on Friday, 09 June 2017 16:21
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 94 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.