You are here: HomeTheologyዛሬም መኃይምነት የጨለማ ጕዞ መሆኑን እናምናለን

ዛሬም መኃይምነት የጨለማ ጕዞ መሆኑን እናምናለን

Written by  Tuesday, 16 September 2014 00:00

የክቡር ሐዲስ ዓለማየሁን ስመ ጥር መጽሐፍ፣ ፍቅር እስከ መቃብርን በቅጡ ለመረዳት፣ መጽሐፉ የተጻፈበትን የአማርኛ ቋንቋ፣ ትረካው የተዋቀረበትን የታሪክ ዘመን፣ መጽሐፉ በምፀት የሞሞሸልቀውን ሥርዐተ ማኅበር፣ የድርሰቱ ባለቤት የሆነው ሕዝብ የሚጋራውን ባህል፣ የሰሜኑ የአገራችን ሕዝብ የሚኖርበትን መልከዐ ምድር፣ በዘመኑ የነበረውን የቤተ ክህነት ሥርዐትና የነገረ መለኮት አስተሳሰብ እንዲሁም እነዚህ መሰል ጕዳዮች በሚገባ ማወቅ የግድ ይላል፡፡ አልያ ግን ፍቅር እስከ መቃብን አንብቤ በሚገባ ተረድቼዋለሁ ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ይህን መጽሐፍ እኔ በምረዳው መጠንና ጕልበት፣ የበኲር ልጄ አትናቴዎስ አንብቦ ይረዳዋል ማለት ሸፍጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ የዘረዘርኋቸው ነገሮች በአብዛኛው ለልጅ አትናቴዎስ ባይተዋር ናቸውና፡፡  

 

የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ከብዙ ሺህ ዓመት በፊት የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው፡፡ የዘመኑ ርቀት ብቻ ሳይሆን የሥልጣኔውም ምጥቀት፣ የሕዝቡ አስተሳሰብ ልቀት፣ የመልከዐ ምድሩ ርቀት፣ ወዘተ ከእኛ አስተሳሰብና ማንነት የትዬለሌ ነው፡፡ ቋንቋውን ብቻ እንኳ በአብነት ብምንለከት፣ ጸሓፍያኑም ሆኑ ቀዳማይ ተደራስያኑ የሚግባቡበት ቋንቋ፣ ይጠቀሙበት የነበረው ፈሊጣዊ አነጋገር፣ ቋንቋው የተዋቀረበትን ሰዋስዋዊ አንጓ፣ ቅኔአቸውን የሚሰትሩባቸው ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጾች፣ የቃላቶቻቸው አማራጭ ትርጓሜዎች እንዲያው ብቻ ነገረ ዓለማቸው ሁሉ ከእኛ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ 

 

ይህ ሁሉ እውነት ከሆነ ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብቦ መረዳት ምን ያህል ፈታኝ ጕዳይ መሆኑን፣ መገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ነገረ መለኮትን በኮሌጅ ወይም በዮኒቨርስቲ ደረጃ ማጥናት አስፈላጊ የሆነው፣ እነዚህ እልቊ መሳፍርት የሌላቸውን ክፍተቶች ዐቅም በፈቀደ ሁሉ ለመሙላትና የመልእክቱን ትክክልኛ ሐሳብ መጨበጥ ይቻል ዘንድ ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ቅዱሳትን መጻሕፍት አንብቦ መረዳት ይህን ያህል ፈታኝ ለምን ሆነ? እርሱን እንድናውቅና እንደ ሐሳብም እንኖር ዘንድ ቃሉን የቸረን አምላክ፣ እነዚህን ጋሬጣዎች ከፊታችን ገለል ለምን አላደረጋቸውም? እርሱ ልዑል እስከ ሆነ ድረስ ቀሊልና ልዝብ አማራጮችን ለምን አልፈለገም? ጥሩ ጥያቄ ነው፤ አምላክ ይህን መንገድ ለምን እንደ መረጠ በእውነቱ አላውቅም፡፡ አንድ ነገር ግን በርግጠኝነት መናገር እችላለሁቃሉን የሰጠን አምላክ እነዚህን ክፍተቶች ሁሉ በመሙላት የመጻሕፍቱን ሐሳብ ለዘመኑ ተደራስያን የሚያሸጋግሩልንን የነገረ መለኮት መምህራንን አብሮ ሰጥቶናል፡፡ ቃሉን ሲሰጠን አስተማሪዎችንም አብሮ ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመጻፍ ሰዎችን እንደ ተጠቀመ ሁሉ፣ ቃሉንም ለመተንተን ሰዎችን ይጠቀማል፡፡ እርሱ ሥጋ ሰጥቶ ቢላ የሚከለክል አምላክ አይደለምና፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር አስተማሪዎችን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠ የሚለን፡፡ ዕለታዊ ጋዜጦችን አንብቦ የመረዳት ያህል ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብቦ መረዳት ቀላል ቢሆን ኖሮ፣ አምላክ አስተማሪዎችን መስጠት በጭራሽ አያስፈልገውም ነበር፡፡ ከላይ እንዳልሁት በዚያ ዘመን አምላክ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚጽፉ ሰዎች እንደ ሰጠን፣ ዛሬም ይህን ሐሳብ የሚተነትኑልንን መምህራን ሰጥቶናል፡፡ የበኵረ ጽሑፋቱን ማለትም የዕብራይስጡን፣ የግሪኩን፣ የአረማይስጡን ቋንቋ በሚገባ የሚያውቁ፣ ሥነ አፈታቱን፣ የቋንቋውን ፈሊጣዊ አነጋገር፣ መልከዐ ምድር፣ ታሪክ ወዘተ የሚረዱ ሊቃውንትን አብሮ ሰጥቶናል፡፡ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ እስካሬዋ ቀን ድረስ አንድን የመጻሕፍት ክፍል እንዴት እንደምንተነትን የሚነግሩን በርካታ ድርሳናት በእጃችን አሉ፡፡ እንግዲያው አሁን በፍጹም ትሕትና በእነዚህ ትምህርተ ዘለቅ እግር ሥር ቊጭ ብሎ የመማር ቊርጥ ውሳኔ የማድረጉ ሙሉ ኀላፊነት የእኛው ነው፡፡ አልያ ግን አገልግሎታችን መጽሐፍ ቅዱስን እያነበቡ የራስን ከንቱ ክጃሎት ከማገልገል አዙሪት ሊወጣ በፍጹም አይችልም፡፡ 

 

ይህን ስል ግን ነገረ መለኮትን በኮሌጅ ደረጃ የተማረ ሰው ሁሉ፣ ለሙሉ ጊዜ የማስተማር አገልግሎት ጌታ ጠርቶታል እያልሁ አይደለም፡፡ በአንጻሩ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተጠራ ሰው ሁሉ መማር እንዳለበት ግን አጥብቄ አምናለሁ፣ አሳምናለሁ፣ አጠምቃለሁም! ዛሬ ቅዱሳት መጻሕፍትን በወጉ ሳይማሩ ሙሉ ጊዜያቸውን በመጋቢነት፣ በአስተማሪነት፣ በሰባኪነት ወዘተ ያሰማሩ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ መቼም ትምህርት ቤት ገብቶ ነገረ መለኮትን መማር ከብዙ አንጻር ፈታኝ እንደ ሆነ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃልና ለሙሉ ጊዜ ጥሪ ራሳችሁን እንደ ሰጣችሁት ሁሉ፣ ለቃሉ ትምህርት ራሳችሁን እንድታስገዙ ላበረታታችሁ እወዳሉ፡፡ አገልግሎት ቃሉን ማስተማር ብቻ ሳይሆን፣ መማርም ጭምር ነው፡፡ አልያ ግን እግዚአብሔርን አገለግላለሁ በሚለው ጥሩ ውሳኔ ውስጥ፣ ለቃሉ ባይተዋር የሆኑ ኑፋቄዎችን ቀፍቅፈን ሰዎችን ከመስመር እንዳናወጣ ትልቅ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ 

 

በቅርቡ አንድ ባልንጀራዬ፣ አንድ ሰው ቤተ ክርስቲያን መመገብ እንደ ጀመረ አጫወተኝ፡፡ ይህ መጋቢ ሆነ የተባለው ሰው አንዳችም የነገረ መለኮት ትምህርት ያለመከታተሉ ብቻ ሳይሆን፣ የሚረባ የእምነት ማጽኛ ትምህርት እንኳ እንዳላገኘ እኔ በቅርብ አውቃለሁ፡፡ እንዲያው በእኔ ሞት አሁን ይህ ሰው ምን ለመመገብ ነው መጋቢ የሆነው?

   

መቼም በአገራችን ነገረ መለኮት እንደ ጦር እንደሚፈራ አውቃለሁከጥቂት ዓመታት ወዲህ ይህ አስተሳሰብ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እየለዘበ እንደ መጣ ይታወቃል፡፡ ነገረ መለኮት የተቈላ ገብስ ነው፤ ሲበሉት ይጣፍጣል ቢዘሩት አይመቅልም ወይም ነገረ መለኮት ያደርቃል ወዘተ የሚል አስተሳሳብ እንደ ነበር፡፡ ይህ አባባል በስፋት ይነገርባት የነበረች ቤተ ክርስቲያን፣ ዛሬ ትልቅ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ከፍታ መገኘቷ፣ ለስንፍናው ንግግር የቀረበ አጸፋዊ ንስሓ እንደ ሆነ ገብቶኛል፡፡ ነገር ግን ዛሬም በዚህ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት የሚገቡ የቤተ እምነቱ ተማሪዎች መሪ ጥቅሳቸው ያለህን አጥብቀህ ያዝ የሚለው የምንባብ ክፍል ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የነገረ መለኮት ትምህርታቸው አንዳችም የአስተሳሰብም ሆነ የምግባር ለውጥ እንዳላመጣላቸው በውል ስለሚታይ ነውይህ ግን ሁሉንም አገልጋይ ይወክላል ማለቴ አይደለም፡፡ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ገብቶ ግሪክን፣ ዕብራይስጥን፣ ሥነ አፈታትን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ ደርዛዌ ነገረ መለኮትን፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክን፣ የስብከት ዘዴን፣ ማማከር ጥበብን ወዘተ መማር እንዴት ሊያደርቅ እንደሚችል አይገባኝም፡፡ አንዳንድ የነገረ መለኮት ሰዎች ደረቅ እንደ ሆኑ እኔም ዐውቃለሁ፤ ምስክርም ነኝ፡፡ አንዳንድ ያልተማሩ ሰዎችም ደረቅ መሆናቸው አይካድም፡፡ ታዲያ መድረቁ ከግለሰቡ እንጂ ከትምህርቱ አንጻር መታየት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ነገረ መለኮትን አስመልክቶ አንድ መምህሬ የተናገረው ንግግር በዚህ ቦታ ቢዘከር አግባብነት ይኖረዋል፡፡ ነገረ መለኮት እንደ ቀትር ፀሓይ ነው ይላል ይህ ሰው፡፡ የቀትር ፀሓይ ጭቃውን ያደርቀዋል፡፡ ቅቤውን ደግሞ ያቀልጠዋል፡፡ ፀሓዩ ሙቀት ለጭቃውም ሆነ ለቅቤው አንድ ቢሆንም በጭቃውና በቅቤው ላይ የሚያስከትለው ውጤት ግን ለየቅል ነው፡፡ ደረቅ ሰዎችን አይቶ ነገረ መለኮት ያደርቃል ማለት ፍርደ ገመድልነት ነው፡፡ ነገረ መለኮት ተምረው ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለአገር ትልቅ ነገረ ሠርተው ያለፉትን ሰዎች መቈጠር ይቻላል፡፡ ቢያንስ የምናነበውን መጽሐፍ ቅዱስ ከዕብራይስጥ፣ ከግሪክና ከአረማይስጥ ወደ አፍ መፍቻ ቋንቋችን የተረጐሙልን የነገረ መለኮት ምሁራን መሆናቸው እንዴት ሊሰወርብን ይችላል?

 

አንዳንድ ሰዎች እኔ ኮመንታሪ አገላብጬ አይደለም የምሰብካችሁ፤ በጌታ ፊት ሕይወቴን አገላብጬ እንጂ እያሉ እንደሚናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ የመስኩ ምሁራንን አስተያየት ለማወቅ ኮመንታሪን (የትርጓሜ መጻሕፍትን) ማገላበጥ ቢሆን ብልኅነት እንጂ በምንም መልኩ ስንፍና አይደለም፡፡ ኑፋቄን ከማስተማር የምሁራንን ምክር መጠየቅ በብዙ መልኩ ተመራጭ አካሄድ ነው፡፡ እንዲያውም ሳያማክሩ ለመስበክ መነሣት፣ ብዙ አደጋ እጅግም ብዙ መዘዝ አለው፡፡ ታዲያ ይህን በሚያህል ትልቅ ስንፍና ላይ ይህን ያህል መጓደድ ተገቢ ነው? ሕይወቴን አገላብጫለሁ ብሎ በዐውደ ምሕረቱ ላይ መናገርስ ትዕቢት አይደለምን? የአንድ ቤተ ክስቲያን መጋቢ አንድ ተጋባዥ ሰባኪ ነገረ መለኮትን እያበሻቀጠ ሲናገር ይስማዋል፡፡ በአገልግሎቱ ማብቂያ ላይ ወደ ቢሮው ይዞት በመሄድ፣ አንድ ጠንካራ ምንባብ በማውጣት፣ ይህን ክፍል እንዴት ታብራራዋለህ ሲል ይጠይቀወቀል፡፡ ግለዘቡም ክፍሉን በተለያዩ አማራጭ መንገዶች ሊተጕም ሙከራ ያደርጋል፡፡ መጋቢውም ትንታኔዎቹ ሁሉ መሠረታዊውን የክርስትና ትምህርት እንደሚጣረሱ ይገልጽለታል፡፡ በመጨረሻም የዚህን ምባብ ትርጓሜ እንደማያውቅ ይገልጻል፡፡ መጋቢውም ክፍሉን ለአእምሮ ግቡዕ በሆነ መንገድ ይተነትንለታል፡፡ ግለሰቡም ለትንታኔው አድናቆቱን ይችራል፡፡ መጋቢው ይህን ትንታኔ ያገኘሁት ተንበርክኬ ስጸልይ ሳይሆን፣ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት በምማርበት ጊዜ ነው አለው፡፡ የመድረክ ስንፍናውን ቢሮ ዘግቶ የሸነቈጠው በዚህ መልክ ነው፤ ይህ መቼም የጥሩ መጋቢ ምግባር ነው፡፡ ተማሩ፤ ተመራመሩ፡፡ ቸር ሰንብቱልኝ፡፡

Seen 10577 times Last modified on Thursday, 18 September 2014 11:51
Tesfaye Robele

ዶክተር ተስፋዬ ሮበሌ በኢንተርናሽናል የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የአዲሱ መደበኛ ትርጒም ተርጓሚ ሆኖ ሠርቶአል፡፡ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የቤተ እምነቱ የሥነ ጽሑፍ ክፍል ኀላፊና የ“ቃለ ሕይወት” መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ አገልግሎአል፡፡ ለዐቅብተ እምነት አገልግሎት ካለው ትልቅ ሸክም የተነሣ፣ ተስፋ ዐቃብያነ ክርስትና ማኅበርን መሥርቶአል፤ በዐቅብተ እምነትም ላይ በርካታ መጻሕፍትን አዘጋጅቶአል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪውንም የሠራው ለረጅም ዓመት በሠራበትና ወደ ፊትም በስፋት ሊያገለግልበት በሚፈልገው በክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት (Christian Apologetics) አገልግሎት ነው፡፡

Website: www.tesfayerobele.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 135 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.